ዮናታን ተስፋዬ | Yonatan Tesfaye
ወጣቱ ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ጽሑፍ 6 ዓመት ከ6 ወር እስር ተፈረደበት

ኢዛ (ኀሙስ ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. May 25, 2017)፦ ዛሬ በአዲስ አበባ ያስቻለው የከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞው የሠማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ ላይ በተመሰረተው የአሸባሪነት ወንጀል ክስ የስድስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት ቅጣት ፈረደበት።

ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የወሰነው የወጣት ዮናታንን ጠበቆችን የቅጣት ማቅለያ በከፊል ተቀብሎ መሆኑን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል የደረሰው ዘገባ ያመለክታል።

ወጣት ዮናታን መንግሥትን የሚተቹ እና ቀስቃሽ ጽሑፎችን በፌስቡክ በማሰራጨት በሚል ከታህሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በማዕከላዊ እስር ቤት ፀረ-ሽብር ሕጉ ለምርመራ ከሚፈቅደው ውጪ ከአራት ወራት በላይ ከስ ሳይመሰረትበት ታስሮ መቆየቱ ይታወሳል። ”የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ መዘጋጀትና ማነሳሳት” በሚል ወንጀል ክስ ከተመሰረተበት ከሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከራከር ቆይቶአል።

ወጣት ዮናታን የቀረበበትን ክስ ለመከላከል በእስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናን እና አቶ በቀለ ገርባን፤ እንዲሁም የፍልሥፍና መምሕሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን፣ የሕግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምን እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ አስር ምስክሮች አቅርቦ ክሱን ሲከላከል መቆየቱ ይታወሳል። ክሱ የተመሰረተበት አንቀጽ ከእስር እስከ 20 ዓመት እስራት የሚያስፈርድ እንደነበረ መዘገባችን አይዘነጋም።

በእስር ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በላይ ከቆየ በኋላ፣ ባለፈው ግንቦት ፰ (8) ቀን ፳፻፱ (2009) ዓ.ም. የዋለው ችሎት ወጣት ዮናታን በተከሰሰበት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 አንቀፅ 6ን በመተላለፍ በሚል ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛነት ብይን ሰጥቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ግንቦት ፲፯ (17) ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ወንጀለኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት የወነጀለው፤ ”መንግሥትን በመቃወም አደባባይ ለወጣው ሕዝብ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ፤ መንግሥት የኃይል እርምጃ ወስዷል” ብሎ በመጻፉ መሆኑ ታውቋል።

የወጣቱ ፖለቲከኛ ጠበቃ ጠበቃ አቶ ሽብሩ፤ የስድስት ዓመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣቱን እሳቸውም ሆኑ ደንበኛቸው ስላልተቀበሉት፤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ