President Shalework Reaffirms The Governments Commitment To Hold Free And Fair Elections In 2020

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ዛሬ በይፋ በተከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ

ኢዛ (ሰኞ መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 7, 2019):- በዚህ ዓመት የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በተቻለ መጠን ባለፉት ምርጫዎች ያጋጠሙ ግድፈቶችን በሚያርም መልክ እንዲከናወን፣ የሚደረግ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

ፕሬዝዳንቷ ይህንን የገለፁት ዛሬ በይፋ በተከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።

በ2012 መንግሥት በትኩረት ከሚሠራባቸው በርካታ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ነው። በዚሁ ረገድ ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው የሚካሄደው ምርጫ በተቻለ መጠን ያለፉትን ግድፈቶች እንዳይደግም የሚሠራ ሲሆን፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆንና የፖለቲካ ልሒቃንና የምእላተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።

2012 ዓ.ም. የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል ያሉት ፕሬዝዳንትዋ፤ ጉዞውም መሠረት ያደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የ“መደመር” እሳቤ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። የ“መደመር” እሳቤው ደግሞ በሦስት ዋነኛ አገራዊ ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል። እነርሱም፤ በአገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፤ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና፤ የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት ናቸው ብለዋል።

ፕሬዝዳንትዋ አክለው፤ “የእነዚህ ዓላማዎች ዋነኛው ማጠንጠኛ ሦስቱን ግቦች ለማሳካት መቻል ነው። እነዚህም፣ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት ማስጠበቅ፤ የሕዝቧን ክብር ከፍ ማድረግና፤ ብልጽግናን ማምጣት ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

ምርጫው ሦስት እሴቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠራም ባመለከቱበት በዚህ ንግግራቸው፤ ሦስቱ እሴቶች የቀደመውን የምርጫ ግድፈት በሚያርም መልክ እንዲከናወን ማድረግ አንዱ ነው።

ሦስቱን አስፈላጊ ጉዳዮች ለማሳካት የመንግሥት ቁርጠኝነትና ዝግጅት ብቻውን በቂ ያለመሆኑንም ገልፀው፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ልሒቃኑና የሲቪክ ድርጅቶች ቀናነት፣ ተሳትፎና ለአንድ አገራዊ ዓላማ መሥራት ወሳኝ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ንግግራቸው፣ “ኢትዮጵያ ዛሬ አልተጀመረችም፤ የሺ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ናት። በዚህች አገር ታሪክ ውስጥ ያከማቸናቸውና ለዛሬና ለነገ ሊጠቅሙን የሚችሉ መነሻ ሀብቶች አሉን። ካከማቸናቸው ሀብቶችና ፀጋዎች መካከል ነፃነትን አስከብረን መኖራችን፣ የረዥም ዘመናት የታሪክና የቅርስ ሀብቶችን ማከማቸታችን፣ እርስ በርስ የተቆራኘ ሕብረ ብሔራዊነትን መፍጠራችን፣ በውጭ ግንኙኘት መስክ ያዳበርነውን ተሰሚነት፣ በአፍሪካውያን እኅቶቻችንና ወንድሞቻችን ዘንድ ያለን የነፃነት አጋርነት ታሪካችን፣ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የገነባናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ያስመዘገብነው የኢኮኖሚ እድገት፣ እያዳበርነው የመጣነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ወዘተ … መጥቀስ ይቻላል። እነዚህን ሀብቶቻችንን አካብተን ለዛሬና ለነገ ብልጽግናችን በመጠቀም የጀመርነውን ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።” ብለዋል።

አክለውም፣ “ያለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎቻችን መልካም ጸጋዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስህተቶችም አሉት። እኩልነትን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን፣ አካታችነትን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ የፍትሕ ሥርዓት መዛነፍን በተመለከተ የተፈጸሙ ስህተቶች አሉ። በቅርቡ ታሪካችን እንኳን ልዩነቶቻችን ላይ የሠራነውን ያህል አንድነታችን ላይ አልሠራንም፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በሚገባው ልክ አላረጋገጠም፣ በሰብአዊ መብት አያያዛችንና በፖለቲካዊ መብቶቻችን ላይ ሰፊ ጉድለቶች ተመዝግበዋል። እነዚህ የተወዘፉ ዕዳዎቻችን ናቸው። ውዝፍ ስህተቶቻችንን ያለ ምሕረት ማረም ይኖርብናል።” በማለት ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በእርጋታው፣ በአርቆ አስተዋይነቱና ስንዴውን ከእንክርዳዱ በመለየት ብቃቱ ነው፡፡ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ይመዝናል፤ ከዕለት አልፎ ዘላቂውን አርቆ ያስባል፤ የሚሰማውንና የሚያየውን እየመዘነ ምርቱን ከገለባ ይለያል፡፡ ይህንን ታላቅ ሕዝብ እዚህም እዚያም የሚወረወሩ አሉባልታዎች ሊፈትኑት አይገባም፡፡ ስሜት አርቆ አሳቢነትን፣ ግብታዊነትም እርጋታን ሲተኩ ዝም ብሎ ማየት የለበትም፡፡ የሐሰት መረጃዎችን ሳይመዝኑ መነሣትና ግብታዊ እርምጃዎችን መውሰድ የዚህ ታላቅ ሕዝብ መገለጫዎች እንዳይሆኑ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ ምትክ የለሽ አንዲት አገራችንን በጋራ ጥረት ሰላማዊ ለማድረግ በአርቆ አስተዋይነት ነገሮችን ሁሉ መጠየቅ፣ መመዘን የሚገባ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መልእክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ።” በማለት ፕሬዝዳንትዋ ተናግረዋል።

“በምናያቸውና በምንሰማቸው አስደሳች ነገሮች እንደምንደተው ሁሉ፤ በዚህ አገር የሚሆነውን ክፉ ተግባር መጠየፍ፤ ተመልሶም እንዳይደገም አስተዋጽኦ ማበርከት የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የግድ ልንሳተፍበት የሚገባ የአገር ግንባታ ጉዞ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የአገራችን ሰላምና መረጋጋት የሁላችንም ራስ ምታት መሆን አለበት፡፡”

“አልፎ ሂያጅነት ማለትም በሁሉም ነገር አይመለከተኝም ብሎ ማሰብ፣ እንግድነት፤ ባይተዋርነት እና ምንአገባኝነት ለአገር እድገት አይበጁም፡፡ ችግር ሲከሠት ሁላችንንም አይምርም፡፡ የሚሻለው በባለቤትነት ስሜት በተነሣሽነት መሥራት ነው፡፡ ማንም አያገባኝም ሊል፤ ማንም ባይተዋር ሊሆን አይገባውም፡፡”

“የአንዱ ሕመም ሌላውንም ሊሰማው ይገባል፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ያስተማሩን የሰብአዊነት፤ የመደጋገፍና ችግርን በደቦ የማሸነፍ መልካም እሴታችን ነው፡፡ ሁላችንም የአገራችን ባለቤቶች ነን፡፡ ምትክ ለሌላት አገራችን እውቀታችንን፣ ጉልበታችንን፣ ሀብታችንንና ቀና ልቡናችንን ሁሉ ይዘን እንነሣ፡፡” በማለት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!