Protest in Amhara region over student abductions

“እኅቶቻችን ይፈቱ!” በማለት በአማራ ክልል የተካሔደው ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ (ማክሰኞ ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 28, 2020)

“መንግሥት በእነዚህ ተማሪዎች እገታ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ይሠጥ!”

ኢዛ (ማክሰኞ ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 28, 2020)፦ ወደ ሁለት ወራት ለተጠጋ ጊዜ በእገታ ላይ መኾናቸው ሲገለጽ የቆዩትን የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በተመለከተ እስካሁን ምንም ዐይነት መፍትሔ ባለመወሰዱ በአማራ ክልል ባህር ዳርን ጨምሮ በሃያ ዘጠኝ ከተሞች ዛሬ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ።

ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ለተቃውሞ ሰልፍ የውጡት የክልሉ ነዋሪዎች መንግሥትን የሚወቅሱና የሚቃወሙ መፈክሮችን በመያዝ ጭምር ሲሆን፣ የሰልፉ መሪ መፈክር “እኅቶቻችን ይፈቱ!” የሚል ነበር።

እስካሁን አልታወቁም በተባሉት ታጋቾች 54 ቀናት ያስቆጠሩት እነዚህን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማስለቀቅ ባለመቻሉና ያሉበትን ሁኔታ እንኳን ባለማሳወቁ ሰልፈኞቹ ቁጣቸውን በተለያየ መንገድ ገልጸዋል።

የእነዚህ ተማሪዎች ጉዳይ አስመልክቶ ዛሬ ከተካሔደው ሰልፍ ባሻገር የተለያዩ ተቋማትም ድምፃቸውን በተለያዩ መንገዶች እያሰሙ ናቸው።

በባህርዳሩ ሰልፍ ምክንያት በከተማዋ ያሉ የመንግሥትና የግል ተቋማት እስከመዘጋት እንደደረሱ ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ መነጋገሪያ በኾነው ወቅታዊ ጉዳይ መንግሥት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጨባጭ መረጃ ባለመሥጠቱ ግፊት እንደተደረገበት መኾኑን ተከትሎ፤ በሰላም ሚኒስትሯ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ደንቢዶሎ በማቅናት ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር መነጋገሩ ይታወሳል።

ከውይይቱ በኋላ የወጡ መረጃዎች ታግተዋል ከተባሉት ተማሪዎች 12ቱ የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መኾናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።

ከዚህ የሰላማዊ ሰልፍ ሌላ የታጋች ተማሪዎች ወላጆችም ስለልጆቻቸው መንግሥት ግልጽ መረጃ ይሠጣቸው ዘንድ እየተማጸኑ ነው።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በሰሜን አሜሪካም ተመሳሳይ ሰልፍ በመካሔድ ላይ ነው። ሠልፈኞቹም፤ “መንግሥት ስለታገቱት ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ይንገረን”፣ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብኢይ የታሉ?” የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሣት ሠላማዊ ሠልፉ ላይ እያንጸባረቁ መኾኑ ታውቋል።

ሰላማዊ ሰልፉ ከባህር ዳር ሌላ በወልዲያ፣ በደብረማርቆስና በደብረ ብርሃን ከመካሔዱም በተጨማሪ በአማራ ክልል በድምሩ በሃያ ዘጠኝ ከተሞች መካሔቱ ተገልጿል። መንግሥት ከኢትዮጵያዊነት ባህል ውጭ እንዲህ ባለ ተግባር የተሰማሩትን ለሕግ ያቅርብልን የሚል ጥያቄ ሰልፈኞቹ አቅርበዋል።

በጉዳዩ ላይ መንግሥት ዝምታ መምረጡን በፅኑ የኮነኑ የተለያዩ ተቋማት፤ ጉዳዩ ግልጽ ይሁን ብለዋል።

እስካሁን የአጋቾች ማንነት ያልተለየ ቢሆንም፤ ይህንን ጉዳይ የፌዴራል ፖሊስ እያጣራ ነው ተብሏል። ትናንት በሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል የተመራው የልዑካን ቡድን ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ምርመራ እየተደረገ መኾኑን አሳውቋል። የጉዳዩ አሳሳቢነት ከግምት ገብቶ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟልም ተብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በእነዚህ ተማሪዎች እገታ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ይሠጥ በማለት ጠይቋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሠጡ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ድርጊቱ ለውጡን ለመገዳደር የተደረገ ቢኾንም መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ መሥጠት አለበት ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!