Ethiopia quarantines again four persons over coronavirus

አዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች ተገኙ፤ አንዱ ቻይናዊና ሦስት ኢትዮጵያውያን ናቸው

አንዱ ቻይናዊ ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው

ኢዛ (ሰኞ ጥር ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 3, 2020)፦ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ አንድ ቻይናዊና ሦስት ኢትዮጵያውያን በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተረገላቸው መኾኑ ተገለጸ። እንደ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጻ ከኾነ፤ እነዚህ አራት ተጠርጣሪዎች ከዚህ ቀደም ተጠርጥረው ከነበሩት አራት ግለሰቦች ሌላ አዲስ ተጠርጣሪዎች ናቸው።

በዚሁ መሠረት ሦስቱ አዲስ ተጠርጣሪዎች በቦሌ ጨፌ፣ አንዱ ደግሞ በአክሱም ከተማ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑም ታውቋል። በቫይረሱ በመያዝ የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ናሙና ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይላካል ተብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከቻይና የሚመጡ ተጓዦችን በአገር ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ አድራሻ እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን መዝግቦ በመያዝ እስከ 14 ቀን ድረስ የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ 47 ሺህ 162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ ማድረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

እስካሁን ባለው መረጃ ምርመራ በሚደረግላቸው ኬላዎች ምርመራ ከተደረገባቸው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ተጓዦች ውስጥ 1695 የሚኾኑት ቫይረሱ ተከስቶባቸዋል ከተባሉ አግሮች የመጡ ስለመኾኑ ተጠቅሷል።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኾነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለው ቢሉም፤ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የኾኑ የሕክምና ባለሙያዎች “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስ ወደተገኘባቸው አገሮች የሚያደርገውን በረራ ባስቸኳይ ማቆም አለበት!” ሲሉ ተደምጠዋል። ለዚህም ምክንያታቸው አገሪቱ በቫይረሱ ከተጠቃች የመከላከል አቅሟ ደካማ መኾኑን፤ ኢትዮጵያውያን ተፋፍገን በመኖራችን በቫይረሱ አንዴ ከተጠቃን በቀላሉ በርካታ ሕዝብ ለቫይረሱ ሰለባ እንደሚኾን፤ በተለይም ወደ ቻይና ከሚደረገው ጉዞ ከሚገኘው ትርፍ በበለጠ አገሪቱ በቫይረሱ ከተጠቃች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውና ወደውጭ ከሚላኩ ምግብ ነክ (የእጽዋትና የእንስሳት) ምርቶች አገሪቱ የምታገኘው ገቢ እንደሚቀንስና ወዘተ በመከራከሪያነት እያቀረቡ ይገኛሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ