አቶ ሲራክ አስፋው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዘውዱን ሲያስረክቡ፣ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.

አቶ ሲራክ አስፋው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዘውዱን ሲያስረክቡ፣ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.

ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በሁለተኛ ዓመቱ ነበር የተሰረቀው

ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 20, 2020)፦ ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በሁለተኛ ዓመቱ በ1985 ዓ.ም. ተሰርቆ የነበረውና ከ400 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ዘውድ በዛሬው ዕለተ ለኢትዮጵያ ተመለሰ። ዘውዱ የተዘረፈው መቀሌ አካባቢ ከሚገኘው የሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስቲያን እንደኾነ ታውቋል።

ዘውዱን በኔዘርላንድ ሮተርዳም ከተማ በ2011 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ ያገኙት አቶ ሲራክ አስፋው ሲሆን፣ ይኽ ከአራት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውና የ18ኛው ክፍለ ዘመን ዘውድ እንዲመለስ ግለሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ታውቋል።

የኔዘርላንድ መንግሥትም ዘውዱ የኢትዮጵያ መኾኑን በማመን፤ የውጭ ንግድና የልማት ትብብር ሚኒስትር በኾኑት በወ/ሮ ሲግሪድ ካግ የቡድን መሪነት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አስርክቧል። ዘውዱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በእጅ ያስረከቡት አቶ ሲራክ አስፋው ሲሆኑ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቅርሱ እንዲመለስ ጥረት ላደረጉት ለአቶ ሲራክ፣ ለኔዘርላንድ መንግሥትና በማስመለስ ሒደቱ ላይ ለተሳተፉ ወገኖች ምስጋና ማቅረባቸው ታውቋል።

ወደ አገሩ የተመለሰው ዘውድ በብሔራዊ ሙዚየም ይቀመጥ ዘንድ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተራቸው ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ካሳው አስረክበዋል። ዘውዱ በዛሬው ዕለት በብሔራዊ ሙዚየም የተቀመጠ ሲሆን፣ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት እንዲኾን ተደርጓል። ለሕዝብ ዕይታ ከበቃ በኋላ ወደ ቦታው እንደሚመለስ ተገልጿል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!