የአስቸኳይ ጊዜውን አዋጅ ጥሰው የሠረጉት ሕግ አስከባሪ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ሕግ አስከባሪው - ፖሊስ
“ካልሰማህ ሕግ ተፈፃሚ ይኾንብሃል!”
ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 23, 2020)፦ ይህ ዜና የተሰማው ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዲማ ወረም ወረዳ ነው። ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣስ በተፈፀመ ሕግ መተላለፍ አንድ ሰው በቁጥጥር ሥር ውሎ መታሰሩን ያመለክታል። ሕግ ጥሷል ተብሎ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኘው ሰው ደግሞ ሕግ አስከብር ተብሎ ኃላፊነት የተሠጠው ሰው ነው። ፖሊስ።
እንደ አማራ መገናኛ ብዙኀን መረጃ ይህ ፖሊስ በቁጥር ሥር የዋለው የአስቸኳይ አዋጁን ድንጋጌ በመጣስ ሠርግ ደግሶ ልጁን በመዳሩ ነው።
ለዜና ምንጩ ስለሁኔታው ያስረዱት የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ በዞኑ የሚፈፀሙ ሠርጐችን በማጥናት፤ ደጋሾቹ ሠርጐቻቸውን እንዲያራዝሙ፣ እንዲያስቀሩ ካልኾነም አዋጁን ሳይጥሱ በቤተሰብ ብቻ እንዲፈፀም በደብዳቤ ለሁሉም ተነግሮ ነበር።
ዛሬ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ፖሊስም ሠርጉን እንዳይፈጽም በተደጋጋሚ የተነገረው መኾኑንም የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል። እርሱ ግን ድግሴ ይበላሽብኛል በማለቱ የቀረቡለትን አማራጮች ባለማድመጥ አስቸኳይ አዋጁንም ጉዳዬ ባለማለት የልጁን ሠርግ በማካሔዱ፤ “ካልሰማህ ሕግ ተፈፃሚ ይኾንብሃል!” ተብሎ የልጁን ዓለም ሕግ ጥሶ የፈፀመው ፖሊስ ሊታሰር ችሏል።
ከዜና ምንጩ ዘገባ መቋጫው ላይ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጣሱት ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ፤ በርካታ ሠርጐች ተቋርጠዋል።
የዲማ ወረም ወረዳውን ፖሊስ ጉዳይ የተለየ የሚያደርገው፤ ሕግ አስከባሪ ኾነው ሕግ መጣሳቸው ተጠያቂነቱን የሚያጠነክርባቸው መኾኑን ነው።
ይህንኑ በተመለከተ የንዑስ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ገለጹ የተባለውም ይህንኑ የሚያመላክት ነው። “ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ የፖሊስ አባላት ሊኖራቸው የሚገባውን ቁመና ቢኖረውም፤ አዋጁን ጥሶ ድርጊቱን በመፈጸሙ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ይጠየቃል” ነበር ያሉት። (ኢዛ)