Jawar Mohammed and Hachalu Hundessa

አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ) እና አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ (በቀኝ)

“የአርቲስት ሐጫሉ ግድያ የተቀነባበረ ሴራና ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት የታቀደ ነው” አቶ ሽመልስ

ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 30, 2020)፦ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተቀነባበረ ሴራ መኾኑንና ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት ያቀዱ ኃይሎች የፈጸሙት ድርጊት መኾኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። ፖሊስ በበኩሉ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል።

የፌዴራሉና የኦሮሚያ ፖሊስ በጋራ በሰጡት መግለጫ አቶ ጃዋርን ጨምሮ ሰላሳ አምስት ሰዎች መታሰራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የአርቲስት ሐጫሉ አስከሬን በቤተሰቦቹና በወዳጆቹ ታጅቦ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ወደ ትውልድ ስፍራውና ወላጆቹ ወደሚገኙበት አምቦ ከተማ ሲሸኝ፤ ቡራዩ ላይ በአቶ ጃዋር የሚመራ ቡድን አስከሬኑን ከቤተሰቦቹ በመንጠቅ አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኘው የኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በመኪና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ከነጃዋር ወገን በተተኮሰ ጥይት አንድ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ መገደሉንና፣ በወቅቱ ከአቶ ጃዋር አጃቢዎችና ተከታዮች ላይ ስምንት ክላሾች፣ አምስት ሽጉጦችና ዘጠኝ የሬድዮ መገናኛዎችም መያዛቸውን ጠቁመዋል።

በአቶ ጃዋር መሐመድ እንደተመሠረት የሚነገርለትና ኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) በመባል የሚታወቀው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች በዛሬው ዕለት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን ትርምስና ግጭት በቀጥታ ሥርጭት በቦታዎቹ በመገኘት ሲያስተላልፉ በነበረበት ወቅት፤ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ በአዲስ አበባ የሚገኘው የቴሌቭዥን ጣቢያውም በመንግሥት ኃይሎች ተከብቦ የነበረ ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ የሚያደርገውን ሥርጭት እንዲያቋርጥ በመገደዱ፤ ሥርጭቱን ከምድረ አሜሪካ መቀጠሉ ተደምጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉ መልእክት፤ በተለይም በሰኔ ወራቶች የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮች ጋር እንዲባላ፣ እንዲጋደል፣ ደም እንዲቃባ በተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል። አክለው “በግልጽ ጦርነቱ አዲስ አበባ ጀምረን፤ አዲስ አበባ እንጨርሰዋለን” ያሉ ወገኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ሦስቱ ሰኔዎች የተለያዩ ግድያዎችን በመፈጸም የተጀመረውን ጉዞ ለማደናቀፍ ጥረት መደረጉን በመጥቀስም፤ “ከሁለቱ ሰኔዎች በተለየ መንገድ በዚህኛው ሰኔ በተለየ መንገድ ጉዳዩ የማይመለከተው ሰው እንዲገደል ተደርጎ፤ ከፍተኛ ድንጋጤ፣ ከፍተኛ ጥርጣሬና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር ሙከራ ተደርጓል” ብለዋል።

አክለውም፤ “መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘበው የሚፈለገው፤ ሐጫሉ የእኛ መታወቂያ ባይኖረውም፤ ዩኒፎርም ባይለብስም ታጋይ ነው። ታጋይ መኾኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል” በማለት፤ በሐጫሉ መሥዋእትነት የኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና አጠቃላይ ጉዞ በአንጸባራቂ መንገድ ዳግም የሚመዘገብ እንጂ የሚቆም እንዳይኾን ጥሪ አስተላልፈዋል።

የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች መንግሥታት፣ ባለሥልጣናትና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በሐጫሉ ግድያ የተሰማቸውን ኀዘን የገለጹ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። ለአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትንም ተመኝተዋል። በተለይም የክልል መንግሥታትና ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ሕዝብና ወጣቶች የአገሪቱን መረጋጋት የማይፈልጉ ወገኖች በሚፈጥሯቸው የተቀነባበሩ ሴራዎች እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ አሳስበዋል።

የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ከአዲስ አበባ በሔሊኮፕተር ወላጆቹ ወደሚገኙበት አምቦ ከተማ ተሸኝቶ፤ አስከሬኑ በቤተሰቦቹ ቤት ያረፈ ሲሆን፤ እስካሁን የቀብር ሥነ ሥርዓቱ መቼ እንደሚፈጸም በይፋ አልተነገረም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!