Birtukan Mideksa

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ

በኦሮሚያ ክልል በነገሌ በእነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው በድጋሚ ይካሔዳል

ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 24, 2021)፦ በኦሮሚያ ክልል በነገሌ ምርጫ ክልል ከ100 በላይ በሚኾኑ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው እንዳይካሔድ የተላለፈን መመሪያ በመጣስ በመካሔዱ በእነዚህ ጣቢያዎች የተደረገው ምርጫ 2013 ተቀባይነት እንደማይኖረው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። ይህ የተፈጠረበት ምክንያት ምርጫ ቦርድ ድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ በግል የተወዳደሩትን ግለሰብ ባለማሳተሙ ነው።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ከምርጫው ጋር በተያያዘ በሰጠው መግለጫ፤ ትልቅ ግድፈት ብለው በጠቀሱት ምክንያት የአንድ የግል ተወዳዳሪ የድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ባለመካተታቸው ነው።

በዚህም ምክንያት ምርጫው ከ100 በላይ ጣቢያዎች ላይ እንዳይካሔድ ቢወሰንም፤ በክልሉ አንድ ኃላፊ ወይም በቦርዱ ኃላፊ ምርጫው እንዲካሔድ መደረጉ ሕገወጥ በመኾኑ፤ ይህንን ጉዳይ በሕግ እንዲታይ የሚደረግ መኾኑንም ወይዘሪት ብርቱካን አመልክተዋል።

በዚህ ጉዳይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ “አንዱ ትልቅ ግድፈት የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል የታተመው ድምፅ መስጪያ ወረቀት በሕግ ተመዝግቦ የነበረን የግል ተወዳዳሪ ያላካተተ እንደኾነ በመረዳታችን የግል ተወዳዳሪው ደግሞ ይህንን ለማወቅ የሚያስችል ብቸኛ እድል ያገኘው ዝርዝር ስናወጣ በመኾኑ በነገሌ ምርጫ ክልል ምርጫ መካሔድ የለበትም ብለን ከላይ እስከ ታች ትእዛዝም መመሪያም አስተላልፈን ነበር” ብለዋል።

አያይዘውም “ነገር ግን አንድ የመንግሥት ኃለፊ ወይም የእኛ ኃላፊ ሊኾን ይችላል፤ መቀጠል አለበት በማለቱ ከ100 በላይ በሚኾኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ምርጫውን ሲያስመርጡ ውለዋል። ይህ ፍጹም ሕገወጥ ተግባር ነው” ብለው ተፈጠረ የተባለውን ችግር አስረድተዋል።

ይህን ጉዳይ ለፌዴራል ፖሊስ አሳውቀው ጥፋቱ የማን እንደኾነ በመለየት የድርጊቱ ፈጻሚዎች በሕግም እንዲጠየቁ እንደሚያደርጉም ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል። ይህ የምርጫ ሥርዓት ግን ምንም ዐይነት የሕግ ውጤት የሚኖረው ስላለመኾኑም ሳያመላክቱ አላለፉም። ከወ/ት ብርቱካን ማብራሪያ ለመረዳት እንደሚቻለው በእነዚህ ከ100 በላይ በሚኾኑ የምርጫ ጣቢዎች ምርጫው በድጋሚ እንደሚካሔድ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ