የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ድርቤ አስፋው ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ድርቤ አስፋው ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት (ዓርብ ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም.፤ ፎቶ የባንኩ ፌስቡክ)

በባንኩ ታሪክ ይህ ከፍተኛው ያስመዘገበው ትርፍ ነው
የውጭ ምንዛሪ ገቢው 6 በመቶ ቀነሰ

ኢዛ (ዓርብ ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 2, 2021)፦ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ ሦስት ዘጠኝ (2.39) ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታወቀ። የውጭ ምንዛሪ ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 6 በመቶ መቀነሱን ባንኩ ገልጿል።

ዛሬ ዓርብ ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ድርቤ አስፋው በሰጡት ጋዜጣዊ፤ ከታክስ በፊት ባንኩ ካገኘው የትርፍ መጠን ከ2012 ዓ.ም. አንጻር 42.26 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በባንኩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 2.39 ቢሊዮን ብር (ከፕሮቪዥን እና ዲፕሪሴሽን በፊት) ማትረፍ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህ የትርፍ መጠን ለባንኩ ከፍተኛው መኾኑ እንዳለ ኾኖ በአገሪቱ ካሉ የግል ባንኮችም ከቀዳሚዎቹ አትራፊ ባንኮች ተርታ እንዲሰለፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

ባንኩ ከባለፈው ዓመት የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በብቸኝነት ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳየው በውጭ ምንዛሪ ገቢው ብቻ መኾኑን አሳውቋል። ባለፈው ዓመት (2012 ዓ.ም. በጀት መዝጊያ ላይ) 363 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የነበረው ሲሆን፤ በ2013 ደግሞ ወደ 343 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ በመኾኑ፤ በገንዘብ መጠን 20 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ቅናሽ አሳይቷል። ይህም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 6 በመቶ ቀንሷል።

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ድርቤ አስፋው
የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ድርቤ አስፋው

ይህንን አስመልክተው የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ደርቤ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ምንም እንኳን ጊዜው የኮሮና ቢኾንም፤ የአገሪቱ የውጭ ገቢ ንግድ ያደገ በመኾኑ፤ ኮሮናን ምክንያት ማድረግ የለብንም፤ ይሄንን የባንኩን የአፈጻጸም ችግር እንፈትሻለን ብለዋል።

የባንኩ አጠቃላይ የብድር መጠን 56 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ ከትርፉም ባሻገረ በ2012 ዓ.ም. ከነበረው 52.92 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት የ28.62 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት በ2013 በጀት ዓመት 81.54 ቢሊዮን ብር አድርሷል።

ከዚህም ሌላ የተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰብ ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ጥረት ብቻ 27.18 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ አጠቃላይ የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 72.69 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉ ታውቋል።

ባንኩ በ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት 49 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 469 ከፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 24 ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ በሸሪዓ ሕግ ላይ የተመሠረተ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።

በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት 1.48 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን በማፍራት ከግል ባንኮች ቀዳሚ መኾኑን የገለጸው ባንኩ፤ የደንበኞቹን ቁጥር 7.73 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን አስታውቋል።

“ኮፔይ ኢብር” (COOPay E-Birr) የተሰኘ ዲጂታል ኢኮሲስተምን በማስተዋወቅና የባንኩን አገልግሎት አሰጣጥ ከማዘመኑም በላይ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራት መቻሉን ይፋ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅት (በተጠናቀቀው የ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት መዝጊያ ላይ) የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 4.65 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃጸር የ55 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ባንኩ አስታውቋል።

ብሔራዊ ባንክ በያዝነው ዓመት ሚያዝያ ላይ ባወጣው መመሪያ ባንክ ለማቋቋም ይጠየቅ የነበረውን የተከፈለ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ መወሰኑን ያስታወሱት የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ድርቤ አስፋው፤ የብሔራዊ ባንክ የሚጠይቀውን አምስት ቢሊዮን ብር ለመሙላት ባንኩ የቀረውን 350 ሚሊዮን ብር በአንድና በሁለት ወር ውስጥ እንደሚያሟላ ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ የብሔራዊ ባንኩን አዲስ መመሪያ ተከትሎ፤ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 10 ቢሊዮን ከፍ ለማድረግ መወሰኑን የጠቀሱት አቶ ድርቤ፤ የባንኩን የተከፈለ ካፒታል በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 10 ቢሊዮን ብር እንናደርሰዋለን ብለዋል።

ተጨማሪ መረጃ፤

ባንኮች የበጀት መዝጊያቸውን በፈረንጆች አቆጣጠር ጁን 30 ቀን እንዲያደርጉ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ያገኙ ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትለው ከሚሠሩት ባንኮች ውስጥ የተጠናቀቀ የበጀት ዓመት ሪፖርት ካቀረቡት የግል ባንኮች ውስጥ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ የመጀመሪያው ኾኗል። የበጀት ዓመቱ ከትናንት ወዲያ ረቡዕ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር።

የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ የዛሬ 16 ዓመት (መጋቢት 1997 ዓ.ም.) በ111.5 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል እና 300 ሚሊዮን ብር በተፈቀደ ካፒታል ሥራ መጀመሩ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!