Awash Bank

አዋሽ ባንክ

ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ሒሳብ መጠን በማስመዝገብ በግል ባንኮች ታሪክ አስመዘገበ

ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 6, 2021)፦ በተጠናቀቀው የ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት አምስት ነጥብ አምስት ስምንት (5.58) ቢሊዮን ብር ማትረፉን አዋሽ ባንክ በዛሬው ዕለት አስታወቀ። ከግል ባንኮች የተጠናቀቀውን የሒሳብ ዓመት ሪፖርት በማቅረብ ሁለተኛው የግል ባንክ ኾኗል።

አዋሽ ባንክ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ሒሳብ መጠን ማስመዝገቡንና በዚህም በባንኩም ኾነ በግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያ መኾን መቻሉ ተገልጿል። ኤልሲ ማርጅንን ጨምሮ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ሒሳብ 107.7 (አንድ መቶ ሰባት ነጥብ ሰባት) ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 33.8 (ሰላሳ ሦስት ነጥብ ስምንት) ቢሊዮን ብር የጨመረ በመኾኑ፤ የ46 በመቶ እድገት ማሳየቱን ባንኩ ገልጿል።

ባንኩ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት አንድ መቶ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ከ5 ሚሊዮን በላይ ማድረሱ ታውቋል።

እስከ ሰኔ 2021 እ.ኤ.አ ድረስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከ4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞቹን የኤቲኤም፣ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አዋሽ ባንክ በዛሬው ዕለት አስታውቋል።

ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በተጠናቀቀው ዓመት የሰጠው ብድር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ30 ቢሊዮን ብር (53 በመቶ) እድገት በማሳየቱ የሰጠው የብድር መጠን 87.1 (ሰማንያ ሰባት ነጥብ አንድ) ቢሊዮን ብር መድረሱን ባንኩ አሳውቋል።

የውጭ ምንዛሪን በተመለከት ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር ሲታይ የ37 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር ጭማሪ በማሳየት፤ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከ906 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉ ታውቋል። ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶች ብሎ ባንኩ ያስቀመጣቸው፤ የዓለም ኢኮኖሚ ከኮቪድ ተጽእኖ ማገገም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማደግ ከመኾናቸውም በላይ፤ አዋሽ ባንክ የወሰዳቸው የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎች ናቸው።

አዋሽ ባንክ በዓመቱ የተከፈል ካፒታሉን በ2.23 (ሁለት ነጥብ ሁለት ሦስት) ቢሊዮን ብር ያሳደገ መኾኑን ገልጾ፤ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል 8.2 (ስምንት ነጥብ ሁለት) ቢሊዮን መድረሱን አስታውቋል።

ተጨማሪ መረጃ፤

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሚያዝያ 2013 ዓ.ም. ባወጣው አዲስ መመሪያ የባንኮች የተከፈለ ካፒታል 5 ሚሊዮን ብር እንዲኾን ሲወስን፤ በሥራ ላይ ከነበሩት 16 ባንኮች ውስጥ፤ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል የነበረው ብቸኛው ባንክ አዋሽ ነበር።

አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት 566 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ ከ12 ሺህ በላይ በኾኑ ሠራተኞች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ለተለያዩ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች እና በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ከብር 30 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸው ከተወጡ የግል ባንኮች ውስጥ አንዱ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ