ፓልም የምግብ ዘይት

በአዲስ አበባ አንበሳ ጋራዥ በሚባለው ቦታ በሕገወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ ከሁለት ሚሊዮን ጄሪካን በላይ ፓልም የምግብ ዘይት

በየደረጃው በመንግሥት አካል ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ተባባሪ የኾኑበት ተግባር ነው የሚል ግምት አሳድራል

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 15, 2021)፦ በኢትዮጵያ ሕገወጥ ተግባራት ምን ያህል ደረጃ ላይ እንደደረሱ በርካታ ማሳያዎች በየዕለቱ እየወጡ ነው። የመሬት ዘረፋና ወረራ አንዱ ሲሆን፤ ሌሎችም አንዳንዴ ሊገመቱ የማይችሉ ሕገወጥ ተግባራት በተከታታይ እየተሰሙ ነው። ቅዳሜ ዕለት የተሰማው አንዱ ዜና ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ እና እየተፈጸሙ ያሉ ሕገወጥ ተግባራት በየዘርፉ መኖራቸውን ያሳያል።

ይህ ዜና በአዲስ አበባ አንበሳ ጋራዥ በሚባለው ቦታ በሕገወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ ከሁለት ሚሊዮን ጄሪካን በላይ ፓልም የምግብ ዘይት በአንድ መጋዘን ተሸሽጎ መያዙ ነው። በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ በተባባሰበትና በተለይም እንደ የምግብ ዘይት ዐይነት ያሉ መሠረታዊ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ፤ ሕብረተሰቡን በእጅጉ ባማረረበት ወቅት፤ ይህንን ያህል ዘይት ተሸሽጎ መገኘቱ አስገራሚ ኾኗል። ነገሩን የበለጠ አስደማሚ የሚያደርገው ደግሞ፤ የዘይት አቅርቦት አጥረት ተፈጠረ ተብሎ ባለፈው አንድ ወር የዘይት ዋጋ አሻቅቦ፤ ገበያው ሲታምስ የሰነበተ ከመኾኑ አንጻር በሕገወጥ መንገድ የተከማቸ ሁለት ሚሊዮን ጄሪካን ዘይት ታሽጎበት መገኘቱ በአገሪቱ ሕገወጥ ተግባር ምን ያህል ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ኾኗል።

በሕዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር የዋለው የምግብ ዘይት ጉዳይ በብርቱ አነጋጋሪ የሚያደርገው ደግሞ፤ ፓልም የምግብ ዘይት ከውጭ አገራት በውጭ ምንዛሬ የሚገባና ሌሎች ሕጋዊ አሠራሮችን ተክትሎ አገር ውስጥ የመደረሰ በመኾኑ፤ እንዴት በድብቅ ሊቀመጥ ቻለ የሚለው ነው። የዜና ዘገባው ዘይቱን ሸሽጎ ያስቀመጠው ማነው የሚለውንና እንዴት እንደገባ ባይመልስም፤ እንዲህ ባለ መንገድ የተፈጸመው ውንብድና ግን፤ ዘይቱን ባስመጣው አካል ብቻ ሳይኾን በየደረጃው በመንግሥት አካል ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ተባባሪ የኾኑበት ተግባር ነው የሚል ግምት አሳድራል።

ከዘይቱ ብዛት አንጻር በአንድ መጋዘን እንዲቀመጥ መደረጉ እና ነገሩ በምስጢር ተይዞ መቆየቱም፤ ድርጊቱ በትብብር እና በቅንጅት መሠራቱን ያሳያል። ይህ ተከማችቶ የተያዘው ሁለት ሚሊዮን ጄሪካን ዘይት፤ አንዱ አምስት ሊትር ቢይዝ በአነስተኛ ግምት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!