Ethiopians

ኢትዮጵያውያን በ2013 ዓ.ም.

ጦርነት፣ ምርጫ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ዲፕሎማሲ በዘንድሮው ዓመት ምን ይመስሉ ነበር?

ኢዛ (ሐሙስ ጳጉሜን ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 9, 2021)፦ የ2013 ዓ.ም. መጠናቀቂያ የመጨረሻ ቀናት ላይ ነን። ኢትዮጵያና ዘንድሮ በታሪክ በእጅጉ የሚታሰቡ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነው። በይበልጥ ብርቱ ፈተናዎችን ያስተናገደችበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ ክንውኖች የታዩበት ዓመት ቢኾንም፤ በይበልጥ ግን ተደራራቢ ፈተናዎችዋ ጐልተው የታዩበት ዓመት ኾኗል።

በተለይ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ጋር ተያይዞ አገሪቷን የሚፈታተኑ፤ አሁንም እየተፈታተኑ ያሉ ሁኔታዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ ቡድን የፈጸማቸው ፍጹም የማይታመኑ ድርጊቶች የኢትዮጵያን ሕልውና የተፈታተነ ከመኾን አልፎ፤ ኢትዮጵያ ትፍረስ እስከማለት የደረሰው አቋሙ የአገሪቱ የ2013 ትልቁ ፈተና ቢኾንም፤ ይህንን እብሪት ለማስተንፈስ ኢትዮጵያውያን በአንድ የቆሙበት ዓመት ነው። ከዚህ ባሻገር ከዚሁ ቡድን ጋር በተያያዘ ከምዕራብያውያን በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘረ የቆየው በትር፤ የ2013 የአገሪቱ ሌላ ፈተናም ነበር።

እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ቡድኖች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ብሔርን መሠረት ያደረገው ጥቃት እና ይህም ያስከተለው የንጹኀን እልቂት በዓመቱ ከሚታወሱ አሳዛኝ ድርጊቶች ውስጥ አንዱ በመኾን ሊጠቀስ ይችላል። የማይካድራው ጭፍጨፋም የዓመቱ አሳዛኝ ድርጊት ነበር። ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ወረራ መፈጸሟ፣ የአጣዬ ከተማ ውድመት፣ ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች መገደል እና መታሰር በዓመቱ ጉልህ ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው።

የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በ17 ቀናት ጦርነት መቀሌን መቆጣጠር መቻሉም በዓመቱ ትኩረት ካገኙ ዜናዎች መካከል የሚጠቀስ ነው።

ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የነበረው የሦስቱ አገራት ውዝግብም ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷንና በግድቡ ዙሪያ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው ማብራሪያ ያስገኘላት ድል በዓመቱ ትልቅ ስኬት ተደርጐ የተመዘገበ ነው። ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁም የዓመቱ ታላቅ ስኬት ነበር።

የ2013 ሌላው ስኬት ብዙ ተሟርቶበት የነበረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ ይጠቀሳል። ከኢኮኖሚ አንጻር በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ዓመቱን ሙሉ ሳያቋርጥ እያሻቀበ ያለው የዋጋ ግሽበት ነው።

የብር ለውጥና አንደምታውም ከዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ዓመቱ በርካታ ክንውኖች የተስተናገዱበት ቢኾንም ዋና ዋና ከሚባሉት ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ዘንድሮ

2013 በኢትዮጵያ ታሪክ በተለየ የሚታይበት ዓመት ነው። እንደ አገር የተፈተነችበት ታሪካዊ ዓመት ተደርጐም ይወሰዳል። ዓመቱ በርካታ ፖለቲካዊ ክንውኖች ያለፉበት ነው።

ዓመቱ አንድ ብሎ ከጀመረበት ወር ጀምሮ የአገሪቱ ፖለቲካ እየጦዘ ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ መርዘኛ ቀስቶች አገር እንዳትረጋጋ ኾኖ እነኾ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የዘለቀ ነው።

የ2013 የአገሪቱ ፖለቲካ ያለመረጋጋት እጅግ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ዋነኛው ከየትኛውም ተግዳሮት በላይ ቀድሞ ሊጠቀስ የሚችለው በአሸባሪነት የተፈረጀውና ይህንንም በተግባር እያሳየ ያለው የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያ ላይ የሰበቀው ጦር በቅድሚያ ይቀመጣል።

ኢትዮጵያ ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ የገባችው ይኸው ቡድን ለሁለት አሥርት ዓመታት አገር ሲጠብቅና የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ከልብ ሲያገለግል በነበረው የሰሜን ዕዝን ከጀርባም፣ ከፊትም፣ ከመኻልም መውጋቱ ነው።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ በዕዙ ውስጥ ያሉ የትግራይ ተወላጆች የመከላከያ ሠራዊት አባላት የገዛ ጓዶቻቸውን በጦር መሣሪያ ብቻ ሳይኾን በስለት ጭምር ወግተው የፈጸሙት አረመኔያዊ ተግባር ኢትዮጵያን ደፈረ። ይህ ነው እንግዲህ በ2013 ከሕወሓት ቡድን ጋር ለተከፈተው ጦርነት ምክንያት የኾነው። አገር የተረበሸው። የታጠቂ ቡድኑ መሪዎች ሲመሩት ጭምር በነበረው የአገር መከላከያ ላይ የፈጸሙት ድርጊት፤ ምናልባትም በዓለም ታሪክ ያልተመዘገበ፤ እጅግ ዘግናኝና አቻ የማይገኝለት ክህደት ነበርና፤ ኢትዮጵያውያንም ተባብረው ለዚህ ጦርነት እንዲሰለፉ አድርጓል።

ከጁንታው ጋር በተከፈተ ጦርነት ሳቢያ የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጐች ተፈናቅለዋል። የአገር ሀብት ላልታሰበ ወጪ ውሏል። ለሰብአዊ ድጋፍ እና ለአንዳንድ መሠረታዊ ለማቶች ጥገና በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ጁንታው አገር ከመድፈር እና ወረራ ከማካሔዱ ባሻገር የአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል። ዛሬ በአገር ደረጃ ለዋጋ ግሽበት መንሥኤ ከኾኑት ምክንያቶች መካከል ይኸው ቡድን የፈጠረው ቀውስ ተጠቃሽ ነው። ለዓመታት አገርና ዜጐችን ሲጠብቅ የነበረው የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በግፍ ሲመታ፤ መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ገብቶ ይህንን ተግባሩን በሳምንታት ያገባደደና ጊዜያዊ አስተዳደር ቢሰይም የሕወሓት ቡድን ሸፍጥ ውጥኑን ሊያራምድለት አልቻለም። ስለዚህ ክልሉን ለቅቆ የተናጠል ተኩስ በማድረግ ውሳኔ ላይ በመድረስ ጦሩን ካወጣ በኋላ፤ ጁንታው የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ወርሮ የፈጸመው እጅግ አሰቃቂ ድርጊት፤ ቡድኑ በትክክል አገር ለማፍረስ ያለውን ውጥን ያመላከተ ኾኖ የታየበትም ነው። ይህንን ጦርነት ለመመከት ግን ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር መንቀሳቀሳቸው የ2013 የኢትዮጵያውያን ትልቅ ገድል ኾኖ እንዲመዘገብ አድርጓል። ኢትዮጵያውያን አንድ መኾናቸውን ያሳዩበት የተለየ ዓመት ተደርጐ ይወሰዳል።

ፈታኝ የነበረው ምርጫና አስገራሚ ውጤቱ

2013ን በተለየ ከምናስታውስባቸው በርካታ እውነታዎች መካከል አንዱ ብዙ ተሸርቦበት የነበረው አገራዊ ምርጫ አንዱ ነው። በኮቪድና በተለያዩ ምክንያቶች ለአንድ ዓመት ዘግይቶ የተካሔደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጥቂት በማይባሉ ወገኖች ይሳካል ተብሎ ያልታሰበ ነበር። ነገር ግን እንደታሰበው ሳይኾን እስካሁን በኢትዮጵያ ተደረጉ ከተባሉ ምርጫዎች ሁሉ እጅግ በተሻለ መከናወን የቻለ ኾኖ መጠናቀቁ ተነግሮለታል።

የምርጫው ሒደት ችግሮች የነበሩበትም ቢኾን፤ ከፍጻሜው አንጻር የዘንድሮው ምርጫ በበርካታ መመዘኛዎች የተሻለ ብቻ ሳይኾን ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማካሔድ የሚያስችል ተቋም መገንባት ስለመቻሉ ያመላከተ ኾኗል። ነገም የተሻለ ምርጫ ለማካሔድ ተስፋ የፈነጠቀ ስለመኾኑ በምርጫው ዙሪያ ሐሳባቸውን የሰነዘሩ በርካታ ገለልተኛ አካላት ሳይቀር ምስክርነት መስጠታቸውም፤ የዘንድሮው ምርጫ የተሻለ እንደነበር የሚያሳይ ነው። ይህ ምርጫ ነበሩበት እስከተባሉ ችግሮች ሁሉ በሰላም መጠናቀቁ እንደ ስኬት የሚቆጠር ነው።

በተለይ ዜጐች በዚህ ምርጫ ያሳዩት ተሳትፎ በወቅቱ ኢትዮጵያ አሸነፈች የሚል መልእክት አስተላልፏል።

ከዚህ ባሻገር ግን የዘንድሮ ምርጫ ያልተጠበቁ ነገሮችን ያስተናገደ ነበር። ይህም በዚህ ምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪ ኾነው የቀረቡ ፓርቲዎች በብዙዎች ዘንድ ያገኛሉ ተብሎ የተጠበቀውን ውጤት ማግኘት አለመቻላቸው ነው።

እንደ ኢዜማ እና አብን ያሉ ፓርቲዎች ታዋቂ የተባሉ መሪዎቻቸው ሳይቀሩ መሸነፋቸው የገለጸበት ጉዳይ አስደማሚ ነበር። ይህም ለፓርላማ ማስመረጥ የቻሉት ጥቂት እጩዎቻቸውን ብቻ ኾኗል።

ከዚሁ ጋር የተያዘው ሌላው አስደማሚ ጉዳይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያገኙትን ውጤት በጸጋ መቀበላቸውን እና እንዲህ ያሉ የምርጫ ውጤቶች ግርግርና ረብሻ እንዳይፈጠርባቸው ፓርቲዎቹ ራሳቸው የወሰዱት እርምጃ በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ያልታየ፤ ብሎም በብዙዎች ያልተጠበቀ ነገር ነበር። ይህም ምርጫው በሰላም ከመጠናቀቅ አልፎ ፓርቲዎች አሉኝ የሚሏቸውን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዱት ውሳኔ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ መኾን ችሏል።

በምርጫ ቦርድ ውጤት መሠረት የዘንድሮው ምርጫ አሸናፊ ብልጽግና ፓርቲ ኾኗል። በዚሁ ውጤት መሠረት መንግሥት የሚመሠረት መኾኑ ታውቆ፤ ለዚሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ ባይቀናቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን አዲስ በሚቋቋመው መንግሥት የሚያሳትፉ መኾኑን መገለጹም 2013ን ያስታውሰናል።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት

ሕወሓት የከፈተው ጦርነት አደገኛነት ለማንም ግልጽ ነበር። በግልጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መነሳቱን በአደባባይ እስከመናገር መድረሱ ኢትዮጵያውያንን በብርቱ ያስቆጣ ነበር።

በብሔር ፖለቲካ እንዲከፋፈል ሲሠራበት የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕወሓትን ጥቃት ተባብሮ ለመመለስ ይቸግረዋል የሚል እሳቤ የነበረ ቢኾንም፤ ይህ ሊኾን ሳይችል ቀርቶ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ተነስተው “አገሬን አላስደፍርም!” በማለት ከመቼው ጊዜ በላይ አንድ መኾናቸውን ያሳዩበት ዓመት ቢኖር 2013 ነው።

ሕዝቡ ብቻ ሳይኾን አገር ለመታደጉ ተግባር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ፤ “ችግራችን ይደርሳል፤ አሁን ኢትዮጵያን እናድን!” ብለው፤ የፓርቲ መሪዎች ግንባር ድረስ በመሔድ ያሳዩት አንድነት፤ ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን አደጋ ለመመከት ብሎም በአሸናፊነት ወጥታ ችግሯን ለመቅረፍ ብርሩ ክንድ ለመኾን በቅቷል።

በፍላጐት የጸጥታ ኃይሉን ለመቀላቀልና ለመዝመት የታየው ተነሳሽነት ከዘመናት በኋላ የታየ አገር ለማዳን የታየ በጐ ተግባር ለመኾንም በቅቷል።

የውጭ ኃይሎች እና ዲፕሎማሲ

ከሕወሓት ጋር በነበረው እሰጥ አገባ የሕወሓት ቡድን ትልቅ ሥራ የሠራው በውዝግቡ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ለመምታት ያደረገው ዘመቻ ተጠቃሽ ነው። ይህ ዘመቻ ሐሰትን መሠረት ያደረገ ቢኾንም፤ በተሳሳተ መረጃና ዳጐስ ባለ የገንዘብ ጉርሻ ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ኢትዮጵያ ላይ ጣቱን እንዲቀስር ያደረገ ነበር። ሕወሓት የተጓዘበትን መንገድ ያህል ይህንን በሐሰት ላይ የተመሠረተ ዘመቻ ከኢትዮጵያ ወገን ለመመከት የተደረገው ጥረት ዝቅተኛ ስለነበር፤ በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ እንዲበረታ አድርጓል።

ይህ ሰፊ ዘመቻ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እስከ መጣል የደረሰ ሲሆን፤ በሚደረገው ጫናም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ለመነጋገር የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ስምንት ጊዜ ስብሰባ እስከ መጥራት መድረሱ፤ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ከፍተኛ ዘመቻ አመላክቷል።

ይሁን እንጂ እንደ ቻይና፣ ሩስያ፣ ሕንድ እና ኬንያ ያሉ አገሮች የኢትዮጵያን እውነታ ይዘው፤ ምክር ቤቱን በመሞገታቸው የታሰበው ሁሉ እንዲከሽፍ ኾኗል። ዛሬም ግን ይህ ጫና እንደቀጠለ ነው። አሁን አሁን በተወሰነ ደረጃ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን በኩል እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ለውጦች እያመጣ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የከፈቱት ዘመቻም ዓለም እውነታውን እንዲያውቁ ያገዘ ኾኖ እየታየ ነው።

ዘንድሮ አስደማሚ ከሚባሉ መረጃዎች ውስጥ ሳይጠቀስ የማያልፈው ሕወሓት ወደ መቀሌ በመሔድ እስከመሸገበት ጊዜ ድረስ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ከ50 – 80 በመቶ የሚኾነው በትግራይ ተወላጆች እጅ መኾኑ መነገሩ ነው።

ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው የመከላከያ ሠራዊት የኃይል አሰላለፍና የአመራር ቦታዎች በምን ያህል ደረጃ በትግራይ ተወላጆች እንደተያዙ ያስቀመጡት አኀዝ አጀብ አሰኝቶ ነበር። መከላከያ ሙሉ ለሙሉ በሕወሓት ቡድን አባላት መሞላቱ በግልጽ የታወቀበት መረጃም ነው። ይህንን ለመቀየር የተደረገው ጥረት ፈታኝ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!