ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ሽልማት ሥነሥርዓት ተካሄደ
Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 8 ቀን 2002 ዓ.ም. March 17, 2010)፦ ባለፈው እሁድ መጋቢት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. (ማርች 14 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ በተካሄደው የኖርዌይ ደራሲያን ማኅበር ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የእ.ኤ.አ. 2009 ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ሽልማት ሥነሥርዓት ተካሄደ።
ይህ ሥነሥርዓት ተደረገው ቀደም ብሎ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት ሲሆን፣ በዚሁም ጊዜ የሽልማቱ አሸናፊ የሆነው ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ባለቤት ወ/ሮ ሶፍያ ብርሃነ ከማኅበሩ ፕሬዝዳንት ከወ/ሮ አና ኦተርሆልም እጅ ሽልማቱን ተቀብለዋል።
አና ኦተርሆልም ሽልማቱን ሲሰጡ ባደረጉት ንግግር ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ይህን ሽልማት በማግኘቱ ደስታቸውን ገልጸው፤ ለቤተሰቡም እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ጋዜጠኛው በቅርቡም በመፈታት ከቤተሰቡ ጋር ለመቀላቀል እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ሽልማቱን የተቀበሉት ወ/ሮ ሶፍያ ብርሃነ በበኩላቸው ይህ ሽልማት ለተሸላሚው ባለቤታቸውና ለቤተሰቡ ታላቅ ክብርና ደስታ እንደሆነ ገልጸው፤ የልጆቻቸውን አባት በቅርቡ በአካል ለማግኘት እንደሚችሉም ሽልማቱ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።
ደራሲ ዳዊት ይስኃቅ በኤርትራ እስር ቤት እንደሚገኝና ለዚህ ሽልማት እጩ ሆኖ እንዲቀርብ በማድረግ ለሽልማት እንዲበቃ ያደረገው ደራሲ አበራ ለማ መሆኑን እና ሽልማቱ ከዲፕሎም በተጨማሪ ሁለት መቶ ሺ የኖርዌይ ክሮነር (ወደ 34 ሺህ የአሜሪካ ዶላር / ወደ 25 ሺህ ዩሮ የሚጠጋ) እንደሚያካትት መዘገባችን አይዘነጋም።