በስዊድን ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጋራ ኀዘናቸውን ገለጡ
“እያንዳንዳችን ወደልቦናችን መመለስ አለብን“ የክርስትና ተወካይ
“ቀዳዳውን አብረን እንድፈን“ የእስልምና ተወካይ
“በሰሃራ በረሃ አካላታቸው ለተበለተ ወገኖቻችን ዝም ማለት የለብንም“ የኤርትራ ተወካይ

Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. April 27, 2015)፡- ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከ10 ሰዓት (16፡00) ጀምሮ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ከ2000 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሰርገልስ አደባባይ በመሰብሰብ በሊቢያ እና በደቡብ አፍሪካ አሰቃቂ ግድያ የተፈጸመባቸውን ወገኖቻቸውን እና በመርከብ አደጋ የሞቱትን በማሰብ ኀዘናቸውን እና ተቃውሟቸውን በጋራ ገለጡ።
በስዊድንኛ “ሰርገልስ ቶሪ” (ሰርገልስ አደባባይ) የሚባለውና ብዙዎች ስደተኞችም ሆኑ ስዊድናውያን ብሶታቸውን፣ ተቋውሟቸውን፣ ደስታቸውን እና ኀዘናቸውን የሚገልጡበት ታዋቂ አደባባይ ነው፤ ልክ እንደ አዲስ አበባው መስቀል አደባባይ (አብዮት አደባባይ)። በተለይ በስደተኛው ማኅበረሰብ ዘንድ “ብሶት አደባባይ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል። በዛሬው ዕለት የተሰበሰቡት ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንደባህላቸው የኀዘን መገለጫ የሆነውን ጥቁር ልብስ ለብሰው እና ጥቁር ምልክት ይዘው ነው ወደ ብሶት አደባባይ የወጡት። ከአገራቸው ባህል የሚለየውንና በስዊድን ለኀዘን መግለጫ በመቃብሮችና የሰው ሕይወት በአደጋ ባለፈባቸው ቦታዎች ላይ የሚበሩትን የኀዘን ሻማዎችን አደባባዩ ላይ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ አሰባስበው አብርተዋል።

የሁሉም ፊት በኀዘን ድባብ ተሸፍኖአል፤ የሚስቅ አይታይም። በአገር ቤት በየኀዘን ቤቱ ሳቅና ጨዋታ አይታጣም፤ ጨዋታ አዋቂ አስተዛዛኞች በየመንደሩ አይጠፉምና፤ በዚኽኛው የአደባባይ ኀዘን ግን ሁሉም ለቀስተኛ ነበር፤ ጨዋታ አዋቂዎቹም፣ ሕፃናቱም፣ ወጣቶቹም፣ አዛውንቶቹም፣ ... ልባቸው ተሰብሮአልና፤ የኀዘኑ ቀጥተኛ ባለቤቶች ኹነዋልና። ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የዚኽ ሪፖርት አጠናካሪ በብሶት አደባባይ ካናገራቸው ውስጥ አብዛኞቹ በተለይ ባለፈው ሣምንት ከሰኞ እስከ ረቡዕ ድረስ ሥራ እንዳልገቡ አረጋግጠውለታል፤ አንዳንዶችም በተለይ የሊቢያውን ቪዲዮ የተመለከቱ ያለፈውን ሣምንት ሙሉ ሥራ መግባት እንዳቃታቸው ገልጠውለታል። ያለፈው ሣምንት ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን የጨለማ ሣምንት ኹኖ ቢያልፍም፤ በዚኽኛውም ሣምንት ጨለማው አለመገፈፉን ብሶት አደባባይ የወጣው ሕዝብ ፊት ያሳብቃል።
ለወትሮው በቀጠሮ ሰዓት በማርፈድ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በዛሬው ዕለት የጥሪውን ሰዓት አክብረው ነው የተገኙት። ልክ በሰዓቱ የዝግጅቱ አስተባባሪ ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ የዝግጅቱን መርኀ ግብር ያስተዋወቁ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አንድ ላይ በመሆን የወገኖቻችንን ነፍስ ይማር ለማለትና መሪር ኀዘናችንን ለመግለጽ ነው የተሰበሰብነው ብለዋል። በመቀጠልም የኃይማኖት መሪዎች ሻማ እንዲለኩሱ ተጠይቀው ከክርስትናው አባ ወልደሥላሴ እና ከእስልምናው አቶ ሶፊያን የኀዘን መግለጫ ሻማዎቹን ለኩሰዋል።
በአባ ወልደሥላሴ መሪነት የፀሎት ሥነሥርዓት ከተካሄደ በኋላ፣ አባ ወልደሥላሴ “... የሞቱት ወገኖቻችንን ዘመዶች ማሰብ ይገባናል። በተለያዩ አገሮች የሞቱ ሙስሊም እና ክርስቲያን ወገኖቻችንን በማሰብ፤ እያንዳንዳችን ወደልቦናችን መመለስ አለብን“ በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል።
በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሰብሳቢ አቶ አበረ አዳሙ በመቀጠል ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ “አሁን ስለማልቀስ ሳይሆን ይሄን ለቅሶ እንዴት እናቁም ብለን መጠየቅ ያለብን ወቅት ነው። በንግግር ሁሉም ነገር ሊፈታ ስለሚችል፤ መበታተን ትተን በአንድነት ተሰባስበን እንምጣና እንነጋገር። የርስ በርስ ችግር የሚፈታው በመነጋገር ነው። ወገኖቻችን የታረዱት በዘርና በኃይማኖት ተከፋፍለው ሳይሆን በአንድ ኢትዮጵያዊነት ነው። ካልተደራጀን ሥራችን ማልቀስ ብቻ ነው የሚሆነው። በመሃከላችን ሊኖር የሚገባው አብሮነት ተቀብሯል። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተባብረን አብረን እንሥራ፣ የፖለቲካ ወገናዊነት ሳይኖረን አብረን እንሥራ“ ብለዋል።
ኤርትራውያንን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ግርማይ ሲሆኑ፣ በመጀመሪያ በትግርኛ በመቀጠልም በአማርኛ ተናግረዋል። ”ለተቃጠሉና በካራ ለተገደሉ ወገኖቻችን፣ በሰሃራ በረሃ አካላታቸው ለተበለተ ወገኖቻችን፣ በባህር ለሞቱ ወገኖቻችን ዝም ማለት የለብንም፤ እነሱን በማሰብ ነው እንዲህ የተሰባሰብነው። በሊቢያና በማንኛውም ቦታ ወገኖቻችን በሰይጣኖች ቢገደሉም፤ ወገኖቻችን አልሞቱም፤ ኃይማኖታችንም አይጠፋም። ይሄ ፖለቲካ ሳይሆን የኀዘን ቀን ነው። ሁሉም ስለተሰዋበት። በኛ የወረደ ግፍና መከራ ማንም ሰው የማይቀበለው ነው፤ የተገደሉት ወገኖቻችንን ነብስ በገነት ነው ያለው፤ ነፍሳቸውን ሊያጠፉ አይችሉም። በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ መካከል ምንም ፀብ የለም፤ እግዚአብሔር ነፍስ ይማር“ ብለዋል።
የእስልምናው ማኅበረሰብ ተወካይ የሆኑት አቶ ሶፊያን በበኩላቸው “የፍትህና የመሪ ደሃ እንጂ ሁሉ ያለን ነን። እስልምናን እና ክርስትናን የሚያገናኙዋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ሁሉም አገሮች ለታረዱት ወገኖቻችን ምላሽ ሰጥተዋል። ለእኛም ምላሽ የሚሰጥልን ፈጣሪ ነው። ... በአንድ አገር ያለ ህዝብ በአንድ መርከብ እንደሚሄድ ህዝብ ነው። መርከቧ ውስጥ ውሃ ከገባ ሁሉም ይሰጥማሉ። ስለዚህ ቀዳዳውን አብረን መድፈን አለብን።“ በማለት የሕብረት ጥሪ አስተላልፈዋል።
በዚህ የኀዘንና የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከስዊድን የሶሺያል ዴሞክራት ፓርቲ ወ/ሮ ካሪና ሄግ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የ16 ዓመቱ ታዳጊ ወጣት ዳግም ሻረው ሁለት ግጥሞች በራሱ እና በአንዲት ወጣት ተነበዋል። በስተመጨረሻም ተሰብሳቢው ኀዘኑን ወደመድረክ በመምውጣትም ኾነ በጩኸት እንዲያሰማ ዕድል የተሰጠው ሲሆን፣ ሁሉም በአንድ ላይ ረዘም ላሉ ሰኮንዶች “ኡኡ“ በማለት የዋይታ ድምፅ አሰምቷል። በተለይ ሴቶች ረዘም ላለ ጊዜ ሲያለቅሱ ነበር። ጥቂት የማይባሉና ሙሉ ለሙሉ ጥቁር የለበሱ ሴቶች ዝግጅቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሲያለቅሱ እንደነበር የዚህ ዜና አጠናካሪ ተመልክቷል።

“ማተቤን ከምበጥስ አንገቴ ትበጠስ ብለው ነው የተሰዉት፣ በያለንበት ከመከራ ያውጣን ብለን ልንጸልይ ይገባናል” በማለት የማሳረጊያ ጸሎቱን የመሩት አባ ገብረማሪያም ነበሩ።
በርካቶች የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ባንዲራዎች በትከሻቸው ላይ አስረው ጥንድ ጥንድ ኹነው የሁለቱን አገራት ትስስር አመላክተዋል። ይኽንን ዝግጅት የጠራው የኢትዮ-ስዊድን ታስክ ፎርስ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።
በደቡብ አፍሪካ ሦስት፣ በሊቢያ 28 ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ወደ ጣሊያን ትጓዝ የነበረች መርከብ ላይ የነበሩ ከ350 የሚበልጡ ኤርትራውያን ሕይወታቸው በቅርቡ ማለፉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ሕይወታቸውን ላጡት ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወገኖችና ለመላው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል!
ተጨማሪ ፎቶግራፎችና ቪዲዮ ከዚህ በታች ያገኛሉ!
ቪዲዮ
ፎቶግራፎች


