ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. April 17, 2019)፦ በአክቲቪስትና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ቅዳሜ ሚያዚያ 5 ቀን 2011 ከሕዝብ ጋር ሊያደርግ የነበረውን ስብሰባ በደረሰበት ጫና ለመሰረዝ መገደዱ ታወቀ። ይኼንኑ በተመለከተ ሚያዚያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ”የጋጥ ወጦች ድርጊት ትግላችንን እንድናጠናክር ያደርገናል" በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል።

የባለአደራው ምክር ቤት ያወጣው መግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይገኛል።

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት 

አዲስ አበባ

ሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም.

ጋዜጣዊ መግለጫ

የጋጥ ወጦች ድርጊት ትግላችንን እንድናጠናክር ያደርገናል

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ከሕዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈፀም ላለፉት 35 ቀናት ደፋ ቀና እያለ ይገኛል። በዚህ ጊዜ 3  ሕዝባዊ ስብሰባዎችና አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሞክሮ፣ ሁሉም በአዲስ አበባ መስተዳድር ተፅዕኖ ተደርጎባቸው፣ ሁለቱን ለመሰረዝ ተገዷል። አንዱ ጋዜጣዊ መግለጫም ቢሆን፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክልከላ ተደርጎበታል። 

ይህ ሁሉ መንግሥታዊ ሕገ ወጥነት አግባብ እንዳልሆነ፣ የምክር ቤቱ ሰብሳቢና ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በተገናኙበት ጊዜ ተማምነዋል፤ በቀጣይነትም፣ መስተዳድሩ ከሕገ ወጥ ተግባራቱ ተቆጥቦ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ያለምንም ተፅዕኖ እንዲደረጉ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። 

ይህ ስምምነት ሰኞ ዕለት ተደርሶ፣ በማግስቱ፣ ማክሰኞ፣ ለመስተዳድሩ በገባ ደብዳቤ፣ በቀጣዩ ቅዳሜ ሚያዚያ 5/2011 ዓ.ም. በ24/መገናኛ በሚገኘው ኮከብ አዳራሽ የቦሌና አቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ እቅድ መያዙን፣ ለዚህም የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግ ተጠይቋል።  ሆኖም፣ እስከ ዓርብ ድረስ የመስተዳድሩ ምላሽ በመጥፋቱ፣ ለራሳቸው ለምክትል ከንቲባው በቴክስት እንዲያውቁት  ተደርጓል። በመጨረሻም፣ ዓርብ ዕለት በተሰጠ የቃል ምላሽ፣ በሕጉ መሰረት ስብሰባ ለማድረግ እንደማይከለከል፣ የፖሊስ ጥበቃ ለማድረግ ግን መስተዳድሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ ተገልጿል።
 
በዚህ ተስፋ ባለመቁረጥ፣ አዳራሽ ስብሰባውን በራሳችን ኃይል እያስጠበቅን ለማከናወን ወስነን በቦታው ላይ የተገኘን ቢሆንም፣ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በመኪና ተጭነው የመጡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣቶች፣ በቡድን በቡድን ተደራጅተው በአካባቢው ከመሰማራታቸውም በላይ፣ ወደ ስብሰባው  በመምጣት ኹከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል። ይህንን ለፖሊስ ብናሳውቅም፣ በመጨረሻ ላይ፣ “ጥበቃ አይደረግላችሁም” የሚል እጅግ አሳፋሪና ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ ተሰጥቶናል። በዚህ የጋጥ ወጦች ስልት ስብሰባ እንዳናደርግ በእጅ አዙር ጋሪጣ ተደቅኖብን፣ ራሳችንን ለመከላከል በቂ ኃይል ቢኖረንም፣ የሕዝብ ደህንነትንና የአገረን ሰላም በማስቀደም ስብሰባውን ሰርዘናል። 

እንደዚህ ዐይነቱ ጋጥ ወጥ አካሄድ፣ በባለአንጣነት እየተፈረጀ ላለው ለአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የዴሞክራሲ ሽግግር አደገኛ በመሆኑ፣ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አጥበቀን እንጠይቃለን።

የማስተካከያው እርምጃ ቢወሰድም ባይወሰድም ግን፣ ሰላማዊ ትግላችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለወዳጆቻችንም ሆነ ለተቀናቃኞቻችን ማሳሰብ እንወዳለን። ቁርጠኝነታችንንም በቀጣይነት በምንወስዳቸው ሰላማዊ የተግባር እርምጃዎች እናሳያለን። 

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት

ሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!