Spokesperson of the Ministry of Foreign Affairs of the F.D.R of Ethiopia Nebiat Getachew

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው

ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 20, 2019):- በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብጽ አዲስ ይዛ የቀረበችውን ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥት የማትቀበለው መሆኑን የሚያጠናክር አቋሟን በድጋሚ አሳውቃለች።

ባለፈው ሳምንት በግብጽ ርዕሰ ከተማ ካይሮ ላይ በግብጽ መንግሥት የቀረበውን አዲስ ሐሳብ በመቃወም ኢትዮጵያ በድጋሚ ተቃውሞዋን ይፋ ያደረገችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ነው።

ዛሬ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ፤ ግብጽ ይዛ የመጣችው አዲስ ሐሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ መሆኑንና በምንም ሁኔታ ኢትዮጵያ ይህንን የግብጽ ሐሳብ እንደማትቀበለው አረጋግጠዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጉትን የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ለማጠናከር የተሰጠ መግለጫ ተደርጐ የተወሰደው ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ፤ ከግብጽ የመጣው ሐሳብ ባለፉት ሰባት ዓመታት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ ከነበረው የሦስቱ አገራት የውይይት ይዘት ያፈነገጠ ነው።

ኢትዮጵያ በአባይ ውኃ ላይ ያላት አቋም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎትዋና አቋሟ ስለመሆኑ የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ይካሄድ ከነበረው ውጭ በተናጠል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ግን አትቀበልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር በትብብር እየሠራች ስለመሆኑ ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ አሁን ከግብጽ የቀረበው ሐሳብ እስካሁን እየተሔደበት ካለው አካሔድ ያፈነገጠ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ በሦስትዮሽ ሲካሄድ ያልተቀበለና እስካሁን ከግብጽ የቀረበው ሠነድ እስካሁን በሦስትዮሽ ከነበረውና በሦስትዮሽ አግባብ ሲከተሉት ከነበረው አካሄድ ያፈነገጠ ነው።

ይህንንም ሲያብራሩ “የኢትዮጵያን የአሁንና የወደፊት በውኃው ላይ የመጠቀም መብት የማይቀበል፣ ወደፊት በአባይ ውኃ ላይ ያላትን የልማት እቅዶች የሚያቀርብ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልን በተመለከተ ሒደቱ እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ የሚያደርግ፣ ነው” በማለት አመልክተዋል። “በአጠቃላይ የግብጽ ሰሞናዊ አካሔድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ ስለተገኘ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ እንደገለፁት ይሄ የግብጽ ፕሮፖዛል ከኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም” በማለትም አክለዋል።

የግብጽ የሰሞኑ አጀንዳ የአባይ ግድብ የውኃ አለቃቀቅን ለመቆጣጠር እፈልጋለሁ የሚል አንደምታ ያለው ስለመሆኑ ኢትዮጵየ ይህንን አዲስ ሐሳብ ላለመቀበል የወሰዳቸው ዕርምጃ ተገቢ ነው የሚል አመለካከት በተለያዩ ወገኖች እየተነገረ ነው።

ያልተጠበቀ ነው የተባለው የግብጽ አዲስ ሐሳብ በኢትዮጵያ መንግሥት ቅቡልነት ማጣቱ፤ ሁለቱን አገሮች እሰጥ እገባ ውስጥ ይከታቸዋል የሚለውን አመላካች መሆኑን ብዙዎች ይጋሩታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!