በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለአገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ገለጻ ተደረገ
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድና ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተገኝተዋል
ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 21, 2020)፦ ከሰሞኑ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለአገር መከላከያ የጦር ኃይል አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸው ተገለጸ።
በዚህ የገለጻ ፕሮግራም ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ሲደረጉ የነበሩ የድርድር ሒደቶችን፣ የህዳሴው ግድብን ግንባታ ሒደት፣ የአሞላልና አስተዳደር እቅድ፣ እንዲሁም የግንባታውን ሒደትና ያለበትን ሁኔታ ሚኒስትሩ ለጦር መኮንኖቹ አብራርተዋል።
በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት የተደረጉ ውይይቶች ለምን ስኬታማ መኾን እንዳልቻሉም ለአመራሮቹ የተብራራ ሲሆን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በየትኛውም አገር ላይ ተፅዕኖ እንደማያደርስ ተገልጾላቸዋል ተብሏል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ የኢፌዲሪ መከላከያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ፣ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ ተገኝተዋል። (ኢዛ)