“ኢትዮጵያ ለአልጀርሱ ስምምነት ያለመገዛት መብት አላት” ሜ. ጄነራል አበበ ተ/ኃይማኖት
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፳፬-24 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 4, 2008)፦ኤርትራ የደህንነት ቀጠናውን በመጣሷ የተነሳ የአልጀርስ ስምምነት በመፍረሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስምምነት አልገዛም የማለት ሕጋዊ መብት እንዳለውና፣ ሀገሪቱ የባህር በር የማግኘት መብቷ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ጥያቄ መጠየቅ እንደምትችል አንድ የቀድሞ የኢፌዲሪ አየር ኃይል ጄኔራል ገለጹ።
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄነራል አበበ ተክለኃይማኖት፣ በትግርኛ ለሚታተመው “ደሃይ” ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ወደብ የማግኘት መብቷን ጨምሮ ሌሎች ሕጋዊ ጥያቄዎችን ማንሳት የምትችልባቸው በርካታ ዕድሎች አሉ።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ፋካልቲ ሕግ በማስተማር ላይ የሚገኙት ሜጀር ጄነራል አበበ፣ የአልጀርሱ ስምምነት በችኰላ የተገባበትና ወራሪውንና ተወራሪውን በእኩል ያስቀመጠ ነው ብለዋል። ስምምነቱ የኢትዮጵያን ድል ለኤርትራ የሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጄነራሉ እንደገለጹት የአልጀርሱ ስምምነት ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መድፈሯን የሚያረጋግጥ፣ ዳግመኛ ጥቃት እንዳትሰነዝር የሚያስጠነቅቅ፣ ካሣ እንድትከፍል የሚያስገድድና የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት መብት የሚያስከብር መሆኑን አስታውሰዋል።
በአሜሪካ ጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ሕግ የተማሩት ጄነራሉ፣ የአልጀርሱ ስምምነት እንዳይፈረም ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርና የስምምነቱ መፈረም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ያላገናዘበ በመሆኑ የአላዋቂነታችን መገለጫ መሆኑን ስናገር ነበር ብለዋል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዕውቀት ውሱን መሆኑን የጠቀሱት ጄነራል አበበ፣ የፖሊት ቢሮ አባላት የሚያወጡትን ሕግና ትዕዛዝ እጅ አውጥቶ በማጽደቅ የተገደቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደብ የማግኘት መብቷ ፖለቲካዊ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ሕግ ድጋፍ ያለው መሆኑን የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ1952 ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሃድ ሲወስን፣ የኤርትራን ህዝብ ፍላጐት እና የኢትዮጵያን ወደብ የማግኘት መብት አገናዝቦ እንደሆነም አብራርተዋል።
ኤርትራ እንደምትወረን ባለመጠበቃችን ድንገተኛ ሆኖብን ነበር ያሉት ጄነራል አበበ፣ የሀገር ድንበርን በጀግንነት እንዲያስከብሩ ለኢህአዴግም ሆነ ለቀድሞ የአየር ኃይል አባላት ማሳሰባቸውን ያስታውሳሉ።
በጦር ኃይሉና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል በወቅቱ የነበረው አለመተማመን፣ ጄነራሉ ሥልጣን እንዲለቁ እንዳደረጋቸው ይነገራሉ።