TPLF

በትግራይ ክልል ምርጫ አካሒዳለው ያለውና ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ሕወሓት

በክልሉ ለማድረግ ያሰበውን ምርጫ በአስቸኳይ ያቁም ብሏል
የትግራይ ክልል እስካሁን ምላሽ አልሰጠም

ኢዛ (ዓርብ ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. July 31, 2020)፦ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምርጫ ለማካሔድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በአፋጣኝ የማያቆም ከኾነ በሕግ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መኾኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስጠንቅቋል።

በቅርቡ የፌዴሬሽን አፈ ጉባዔ በመኾን በተሾሙት አቶ አደም ፋራህ በተፈረመ ደብዳቤ ለትግራይ ክልል የተላከው ማስጠንቀቂያ፤ ክልሉ ምርጫ አደርጋለሁ ማለቱ ሕጋዊ መሠረት የሌለው መኾኑን ያስገነዘበበት ነው።

በመኾኑም የትግራይ ክልል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር በመኾኑ፤ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ እና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ሥልጣን ለመተግበር የሚገደድ መኾኑን አስታውቋል።

ደብዳቤው በፌዴራል ደረጃም ኾነ በክልል የሚካሔዱ ምርጫዎችን በገለልተኝነት ማካሔድ የሚችለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ መኾኑን በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ በመኾኑ፤ የትግራይ ክልል ምርጫውን ማካሔድ የማይቻል መኾኑንም የተለያዩ የአገሪቱን ሕጎች በመጥቀስ ጭምር አሳውቋል።

ፌዴሬሽኑ በዚሁ ደብዳቤው፤ የትግራይ ክልል የሚያካሒደውን ምርጫ የማድረግ እንቅስቃሴውን በአስቸኳይ እንዲያቆምም አሳስቧል። ይህ ባይኾን፤ ፌዴሬሽኑ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

አዲሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ዛሬ ዓርብ ሐምሌ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገለጹት፤ ይህ የትግራይ ክልል እንቅስቃሴ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መኾኑን ነው።

ፌዴሬሽኑ ለትግራይ ክልል ማሳሰቢያ መስጠቱን ያረጋገጡት አፈ ጉባዔው፤ ሊወሰድ የሚችለው እርምጃ ምን ሊኾን እንደሚችል ባይገልጹም፤ አንድ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ተግባር ከፈጸመ፤ ይህንን ተግባር በመፈጸሙ ሊወሰዱ የሚገባቸውና በሕግም የተቀመጡትን እርምጃዎች ይወሰዳሉ ተብሏል።

ፌዴሬሽኑ ለጻፈው ማስጠንቀቂያ እስካሁን የትግራይ ክልል ምላሽ ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን፤ አቶ አደምም ይህንን አረጋግጠዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ