Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት ፩-1 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 11, 2008)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ወራቶች ክፍት ለነበሩት ሁለት የምክትል ፕሬዝዳንት የኃላፊነት ቦታዎች ሹመት ሰጠ።

 

ዩኒቨርሲቲው ሰሞኑን የሰጠው ሹመት ለአካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንትነት ዶ/ር ተካልኝ ወልደማርያምን ሲሆን፣ ለቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ምክትል ፕሬዘዳንትነት አቶ እስጢፋኖስ ገ/ሐዋሪያትን ነው።

 

ለአዲስ ተሿሚዎች የተሰጠው የኃላፊነት ቦታ ተጠባባቂ የም/ፕሬዝዳንትነት ሹመት መሆኑ ታውቋል። ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ቀጥሎ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የሆነው የሁለት የምክትል ፕሬዝዳንቶች የኃላፊነት ቦታ ለበርካታ ወራቶች ክፍት ሆኖ የቆየ ነበር።

 

ከዚህ በፊት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ቡቴ ጎቱ ባለፈው ሐምሌ 2000 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው ከተነሱ ጀምሮ፣ ለሦስት ወራት ክፍት ሆኖ ቆይቶ የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የቢዝነስና ዴቨሎፕመንት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ደምሶ ገመዳ መሞት በኋላ ከአምስት ወራት በላይ ክፍት ሆኖ ቆይቷል።

 

ሁለቱ የኃላፊነት ቦታዎች ለበርካታ ወራቶች ክፍት ሆኖ በመቆየቱ፣ በዩኒቨርሲቲው የዕለት ተዕለት የአካዳሚክና የአስተዳደራዊ ጉዳዮች መጓተት ሰፊ ክፍተት እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል።

 

በአዲሱ ሹመት የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ተካልኝ በማስተማርና በዲፓርትመንት ሊቀመንበርነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።

 

ዶ/ር ተካልኝ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ኃላፊነትን መረከብ፣ በዩኒቨርስቲው ለተጋረጡት የትምህርት ጥራት፣ የሥርዓት ትምህርት፣ የጥናትና የምርምር ሌሎች በርካታ የአካዳሚክ ችግሮች እንዲፈቱ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ መታመኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ