የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሾመ

አዲሱ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ (ግራ) እና የቀድሞው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የአሁኑ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር (ቀኝ)
አቶ አብርሃም አለኸኝ አዲሱ ተሿሚ ኾነዋል
ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 11, 2020)፦ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘው ተሻገር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኾነው መሾማቸውን ተከትሎ፤ የክልሉን የብልጽግና ጽሕፈት ቤት እንዲመሩ አቶ አብርሃም አለኸኝ ተሾሙ።
አቶ አብርሃም አለኸኝ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኾነው በዛሬው ዕለት (ረቡዕ ኅዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም.) መሾማቸውን ያስታወቀው የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ነው።
አቶ አብርሃም አዲሱን ሹመት ከመረከባቸው በፊት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ኾነው ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው።
አቶ አገኘው ተሻገር ባለፈው እሁድ ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. አቶ ተመስገን ጥሩነህን ተክተው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኾነው በክልሉ ምክር ቤት መሾማቸውን መዘገባችን አይዘነጋም። አቶ ተመስገን ጥሩነህ ደግሞ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳርነታቸው ለቅቀው፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመኾን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው እሁድ መዘገባችን ይታወሳል። (ኢዛ)