Mai-Kadra massacre

ሕወሓት በማይካድራ በፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ የኾኑና አስከሬናቸው በአግባቡ የተቀበሩ

የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው

ኢዛ (ዓርብ ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 27, 2020)፦ በአገር ውስጥና በውጭ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጨምሮ፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በብርቱ በተወገዘው የማይካድራው ጭፍጨፋ የሟቾች ቁጥር አሁን ከሚገለጸው ከ600 በላይ እንደሚኾን ማረጋገጫዎች እየተገኙ ነው።

በቀጥታ ከሕወሓት ቡድን ጋር በሚገናኘው በዚህ ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመጀመሪያ ደረጃ ምርመራው፤ በማይካድራው ጭፍጨፋ የሟቾች ቁጥር በትንሹ 600 መኾኑን የጠቀሰ ቢኾንም፤ አሁን እየተገኙ ባሉት ተጨማሪ መረጃዎች መሠረት የጭፍጨፋው ሰለባዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ኮሚሽኑ ቁጥር በቤተክርስቲያን የተቀበሩትን ብቻ የያዘም ነው ተብሏል።

ዛሬ በአማራ ክልል ይፋ የኾነው መረጃ እንዳመለከተውም፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በግንባር በቦታው ተገኝቶ ምርመራ ካደረገ በኋላ፤ በአንድ ቦታ ብቻ 18 ሰዎች በጉድጓድ ውስጥ በጅምላ ተጥለው ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ በዚሁ አካባቢ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ደግሞ 57 ሰዎች በጎርፍ ቦይ ውስጥ ተገድለው ተጥለው መገኘታቸውን ጠቅሷል።

Mai-Kadra massacre
ሕወሓት በማይካድራ በፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ የኾኑት አስከሬናቸው ከመቀበሩ በፊት

የማይካድራው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ (ዘር ማጥፋት) ከተጠቀሰውም በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው የሚያመለክተው ሌላው መረጃ ደግሞ፤ በዛሬው ዕለት (ዓርብ ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም.) በማይካድራ ውስጥ በሌላ የገጠር ከተማ 17 ሰዎች በጅምላ ተገድለው በጉድጓድ ውስጥ ተጥለው መገኘታቸው ነው።

አሁንም በማይካድራ ውስጥ በተለያዩ ገጠራማ ቀበሌዎች ፍተሻ እየተደረገ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡና በተመሳሳይ ወደ ጉድጓድ የተወርወሩ ስለሚኖሩ የተጨፈጨፉት ቁጥር ይጨምራል እያሉ ነው።

ጭፍጨፋው ዘርን መሠረት ያደረገና፤ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መኾኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ይህንኑ ያረጋገጠ መረጃ ማግኘቱን በመግለጽ በሪፖርቱ ማካተቱ አይዘነጋም። ዘግናኝ ነበር የተባለው ይኽ ጭፍጨፋ የተካሔደው መታወቂያ ጭምር በማየት እንደነበር ታውቋል።

የአማራ ክልል የመገናኝ ብዙኀን ከዚሁ ጭፍጨፋ ጋር አያይዞ ባወጣው ተጨማሪ መረጃ፤ በወልቃይት ጠገዴ፣ ራያ፣ ሴቲት ሑመራ አካባቢዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ገልጿል።

ይህ መፈናቀል የተፈጸመው በሕወሓት ስለመኾኑ ጠቅሶ፤ ከአስር ሺህ በላይ የሚኾኑ አማሮች መረሸናቸውንም አክሎ ገልጿል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!