National Election Board of Ethiopia (NEBE)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የክልሉ ፖሊስ በዋና መሥሪያ ቤቱ ሊፈጸም የነበረውን የእስር ሙከራ አወገዘ

ኢዛ (ቅዳሜ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 12, 2020)፦ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በዋና መሥሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የፖለቲካ ድርጅት አመራር አባላትን የቤንሻንጉል ክልል ፖሊስ ለማሰር ያደረገውን ሙከራ የቦርዱን ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት እንደሚጋፋና የድርጊቱን አሳሳቢነት አስታወቀ።

ቦርዱ ዛሬ ቅዳሜ ታኅሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ገዥው ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከመጪው ምርጫ (ምርጫ 2013) ጋር በተያያዙ ችግሮች ዙሪያ የሦስትዮሽ ውይይት ላይ ተካፋይ የነበሩ ከቤንሻንጉል የመጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ላይ ወደ ቦርዱ ግቢ በመግባት የእስር ሙከራው የተደረገው ታኅሣሥ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር።

እንዲህ ባለው መንገድ የፖለቲካ አመራሮቹን ወደ ምርጫ ቦርድ በመምጣት ለማሰር መሞከር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ላይ አደጋ ከማጥላቱ ባለፈ፤ ወደ ምርጫ ቦርድ በመምጣት የእስር ሙከራ መደረጉን በእጅጉ ኮንኗል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ከሕጋዊ ወሰኑ ውጭ ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ የፖለቲካ አመራሮችን ለማሰር የተደረገው ጥረት፤ የቦርዱን ተቋማዊ ኃላፊነት እና ሥልጣን ንቀት ማሳየት ጭምር መኾኑንም ቦርዱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሥሥ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ተግባር በተመለከተ ድርጊቱን በማውገዝ ጭምር፤ እንዲሁም ሁኔታውን ያሳየበት መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪው ምርጫ የሚካሔድበትን አውድ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት የሚመለከታቸው አካላት ሊያግዙት ይገባል!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመጪው ምርጫ ዝግጅት በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነሱ አቤቱታዎችን በማሰባሰብ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት ሲደርግ እንደነበር ይታወቃል። ከነዚህም ጥረቶች መካከል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን ለአቤቱታዎቹ ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ፣ ምላሽ ላልተሰጠባቸው አቤቱታዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶችን አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በፓርቲዎች እና ከመንግሥት ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማጠናቀር ያቀረበ ሲሆን፤ ይህንን መሠረት አድርጎ ፓርቲዎች፣ ገዥው ፓርቲ እና ቦርዱ በጋራ በመገኘት ችግሮችን የሚፈቱበት የሦስትዮሽ ችግሮችን እና አቤቱታዎችን የሚፈታ አሠራር እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት የመጀመሪያው የሦስትዮሽ ውይይት ትላንትና ታኅሣሥ 02 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቢሮ የተከናወነ ሲሆን፤ የቤንሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገኝተዋል። በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የመንቀሳቀስ፣ የአባላት እስር እና ሌሎች ችግሮች የተነሱ ሲሆን፤ በገዥው ፓርቲ በኩል የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ኾነው በወንጀል እና በትጥቅ ትግል መሳተፍ ችግሮች አሉ የሚል አቤቱታ ቀርቧል። በውይይቱ ማጠቃለያም በክልሉ ውስጥ ያለውን የፓርቲዎች ችግር ለመፍታት ቦርዱን ጨምሮ ሁሉም አካላት የሚሳተፉበት ቡድን ቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል በመሔድ ለማጣራት ስምምነት ተደርጎ ውይይቱ ተጠናቋል።

ነገር ግን ውይይቱ ተጠናቆ በቤንሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የምርጫ ቦርድ ዋና መሥሪያ ቤት ግቢን ለቅቀው ለመውጣት ሲሞክሩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ አባላት የእስር ሙከራ አድርገውባቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህ ገንቢ እና ችግሮችን ለመፍታት ተስፋ ሰጪ አቅጣጫ ከነበረው በተቃራኒ በተከናወነው እርምጃ ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቶታል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ከሕጋዊ የሥልጣን ወሰኑ ውጪ ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ በር ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን ለማሰር መሞከሩ፤ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያሰናክል እና አሳሳቢም ከመኾኑም በላይ፤ የሕገ መንግሥታዊውን የቦርዱን ተቋማዊ ኃላፊነት እና ሥልጣን ንቀትን ማሳየት ጭምር ነው። ቦርዱ ችግሩን ለመፍታት ከሰዓታት ጥረት በማድረግ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በተገኘ እገዛ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖሊስ ኃይል ከምርጫ ቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በር ላይ ከ3 ሰዓት ቆይታ በኋላ እንዲነሳ ለማድረግ ቢቻልም፤ የተከናወነው የሕግ ጥሰት እና ተቋማዊ ሥልጣንን አለማክበር እጅግ አሳሳቢ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቀጣዩ ምርጫን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት ገዥው ፓርቲም ኾነ መንግሥት በመዋቅሮቹ የሥነሥርዓት ደንብ አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ በይፋ ያረጋገጡትን የሚቃረን በመኾኑ መስተካከል የሚገባው መኾኑን ያምናል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች ላይ የሚደረገው የሦስትዮሽ ችግሮችን መፍታት ሒደት የሚቀጥል ሲሆን፤ መጪው አገራዊ ምርጫ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ደረጃውን የጠበቀ እንዲኾን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዚህ ሒደት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ቦርዱ በአጽንኦት ያስገነዝባል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ