ባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ኤርፖርት

“ባሕር ዳር ግንቦት 20 ኤርፖርት” የሚለው መጠሪያ ቀድሞ ይጠራበት ወደነበረው “ባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ኤርፖርት” ሊቀየር ነው

የተቋረጠው የባሕር ዳር በረራ ነገ ይጀመራል

ኢዛ (ዓርብ ታኅሣሥ ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 18, 2020)፦ ቀድሞ ይጠራበት የነበረውን ስያሜ በመቀየር “ግንቦት 20 ኤርፖርት” በሚል ሲጠራ የነበረው የባሕር ዳር ኤርፖርት ስያሜ ወደቀደመው መጠሪያ እንዲመለስ ተወስኗል።

የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ዛሬ እንዳስታወቀው፤ “ባሕር ዳር ግንቦት 20 ኤርፖርት” የሚለው መጠሪያ ቀድሞ ይጠራበት ወደነበረው “ባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ኤርፖርት” በሚል እንዲጠራ ውሳኔ ተላልፏል።

“ግንቦት 20 ኤርፖርት” የሚለው ስያሜ እንዲቀየር ሕብረተሰቡ ውይይት ሲያደርግበት እንደነበር የሚያመለክተው መረጃ፤ ዛሬ ታኅሣሥ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የከተማዋ ከንቲባ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ አዲሱን ስያሜ እንዲይዝ ሊወስን ችሏል።

“ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ኤርፖርት” የሚለው ስያሜ ከ1983 ዓ.ም. በፊትም ይጠራበት እንደነበር ተጠቅሶ እና የከተማውን ወካይ ስያሜ ይኾናል ተብሎ በመታመኑ፤ የኮሚቴው አባላት ስያሜውን በሙሉ ድምፅ አጽድቀውታል።

“ባሕር ዳር ግንቦት 20 ኤርፖርት” የሚለውን ስያሜ ለመለወጥ የባሕር ዳር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አማራጭ ስያሜዎችን ይፋ አድርጎ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። ባለፈው ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ለአዲሱ ስያሜም የሚኾን እንደመነሻ አራት አማራጮችን ማቅረቡ ይታወሳል። በወቅቱ ለአውሮፕላን ማረፊያው የቀረቡት መነሻ ስሞች “ባሕር ዳር”፣ “በላይ ዘለቀ”፣ “ዓባይ” እና “ጣና” ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሉ ነበሩ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ በነገው ዕለት ቅዳሜ ታኅሣሥ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚጀመርም ታውቋል።

በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የሚደረጉ በረራዎች የተጀመሩ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ ወደ መቀሌ በረራ መጀመሩ አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!