የኑሮ ውድነቱን ያባሰው የነዳጅ ጭማሪ

በአገሪቱ ከሚገኙት ነዳጅ ማደያዎች አንዱ
የትራንስፖስት ዋጋ እና የምርት አቅርቦት ዋጋ ላይ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀሬ ነው
ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 11, 2021)፦ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ በኾነበትና ሊቀንስ ባልቻለበት በዚህ ወቅት፤ የነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ የኑሮ ውድነት ሊያባብሰው እንደሚችል ተጠቆመ።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በነዳጅ ዋጋ መንግሥት ባደረገው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ በአንድ ሌትር ናፍጣ ላይ የ2.10 (ሁለት ብር ከአሥር ሳንቲም) ጭማሪ የተደረገ በመኾኑ፤ ይህ ጭማሪ የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ መኾኑን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እየሰጡ ያሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።
በተለይ በናፍጣ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ አጠቃላይ በትራንስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያስከትልና ይህም ደግሞ አጠቃላይ የምርት አቅርቦት ላይ ዋጋ የሚያስከትል መኾኑ የማይቀር በመኾኑ፤ ወትሮም እየከበደ የመጣውን የኑሮ ውድነት ያብሰዋል የሚል ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው።
መንግሥት የነዳጅ ምርት ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር የተያያዘ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጭማሪ አጠቃላይ ገበያውን የቀየረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችንና የሸቀጣሸቀጥ ምርቶች ዋጋ እየተሰቀለ መኾኑ አሳስቧል። (ኢዛ)