ባንኮች 155 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ
ከ110 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነውን የግሉ ዘርፍ ወስዷል
ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 27, 2021)፦ ሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች ባለፉት ስድስት ወሮች ከ155 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እንዳሰጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተናገሩ።
ዶክተር ይናገር ደሴ የዳሸን ባንክ 25ኛ ዓመት በዓል ላይ እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 19ኙ ባንኮች ከሰጡት ብድር ውስጥ 72 በመቶ የሚኾነው ለግል ዘርፍ የተሰጠ ነው።
በእርሳቸው መረጃ መሠረት ከተሰጠው 155 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ110 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነውን በተለያዩ ዘርፎች ለሚንቀሳቀሱ የግል ኩባንያዎችና ግለሰቦች የተሰጠ ነው።
ይህም የመንግሥት ብድር እየቀነሰ መኾኑን የሚያመለክትና ለግሉ ዘርፍ እየተሰጠ ያለው የብድር መጠን ከፍ እያለ መምጣቱን ነው።
ዶክተር ይናገር እንደገለጹትም በስድስት ወር ውስጥ ከተሰጠው ብድር 72 በመቶ የሚኾነውን የግል ዘርፍ መወሰዱ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው የብድር መጠን ማደጉን ከማሳየቱም በላይ፤ ውጤቱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው እሳቤ እንደኾነም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የባንኮች የተከማቸ የብድር መጠን ከ1.1 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱን ያመለከቱት ዶክተር ይናገር፤ በአንጻሩ ግን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ባንኮች የብድር አሰባሰብ ዝቅተኛ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል። ባንኮች የብድር አሰባሰባቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ አሳስበዋል። (ኢዛ)