Amhara Region flag

የአማራ ክልል በአዲስ ሰንደቅ ዓላማ

አማራን አይወክልም የተባለው ባንዲራ እንዲቀየር ተወሰነ

ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 13, 2021)፦ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ሲገለገልበት የነበረውንና የክልሉን ሕዝብ አይገልጽም ተብሎ ሲተች የቆየው የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ ለመቀየር የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ አሳለፈ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በዛሬው ዕለት (ቅዳሜ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም.) ነው። ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው እስካሁን ያለው የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ የአማራን ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴት እና ሥነልቦና የማይመጥን በመኾኑ ነው።

በዚሁ መሠረት ለምክር ቤቱ የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ለመቀየር የቀረበውን አዋጅ አጽድቆታል። አሁን ያለው የክልሉ ባንዲራ ጥቅም ላይ የሚውለው ለስድስት ወራት ብቻ መኾኑም ታውቋል። በቀጣይ ስድስት ወሮችም ክልሉን ይመጥናል የተባለውን ሰንደቅ ዓላማ በማዘጋጀት ከስድስት ወር በኋላ በአዲሱ ባንዲራ ይተካል ተብሏል።

ሥራ ላይ ያለው ባንዲራ የአማራን ሕዝብ የማይገልጽ በመኾኑ በተደጋጋሚ መቀየር አለበት ተብሎ ትችት ሲቀርብበት የነበረ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ሕዝብ ሕልውና አደጋ ላይ መውደቁን የሚያመላክቱ ሐሳቦች ቀርበው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት አድርጓል ተብሏል።

አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ባለፉት 27 ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአማራ ሕዝብ ሞት ታውጆበታል፣ በኢትዮጵያዊነቱ በመጽናቱ ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል።

እንዲህ ባለው አስተያየቶችና ጥያቄዎች ዙሪያ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር ማንነትን መሠረት አድርጐ እየደረሰ ያለውን ግፍና ሰቆቃ ከዚህ በላይ እንዳይኾን የክልሉ መንግሥት መሥራት እንደሚገባው ጠቁመው፤ ይህ የ27 ዓመታት የአማራ ሕዝብ ጠላት የኾኑ ቡድኖች ያዘጋጁት ወጥመድ ስለመኾኑም አስታውሰዋል። በጉዳዩ ላይም ከፌዴራል መንግሥት ጋር አጀንዳ ይዞ መወያየት እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!