“የአማራ ሕዝብ ምን አደረገ? ምን ፈጸመ? ምን በደለ? ለምን በየቦታው ይገደላል?” የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር
በአገረ መንግሥቱ እጣ ፈንታ ላይ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 13, 2021)፦ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያዳምጠን ይገባል፤ የአማራ ሕዝብ ምን አደረገ? ምን ፈጸመ? ምን በደለ? ለምን በየቦታው ይገደላል?” ያሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር፤ የሕግ የበላይነት ካልተከበር አገሪቱ ወደሌላ ችግር ልታመራ እንደምትችል ገልጸው፤ በአገረ መንግሥቱ እጣ ፈንታ ላይ መነጋገር እንደሚያሻ አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አገኘው ይህንን የተናገሩት የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ቅዳሜ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው 5ኛ ዙር፤ 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ ሲሆን፤ በዚሁ ጉባዔ ላይ፤ አገሪቱ እንድትቀጥል ከተፈለገ የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው የመሥራትና የመኖር መብት ሊረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ በአገረ መንግሥቱ እጣ ፈንታ ላይም መነጋገር እንደሚገባም አሳስበዋል።
አቶ አገኘው አክለው እንደተናገሩት፤ “ከክልሉ ውጭ ያለ አማራ፤ ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር ኾኖ የሚሠራ እንደኾነ እየታወቀ፤ ማንነቱን ብቻ መሠረት አድርጎ ለሚፈጸምበት ግድያ መፍትሔው ተጨባጭ ትግል ነው። መፍትሔው ፊት ለፊት መግጠም ነው።” ብለዋል።
አቶ አገኘው፤ “በአጠቃላይ የክልሉን ሰላም ለማተራመስ፣ የሞት የግድያ ዜና እንድንሰማ ለማድረግ የሚደረግ ነገር አለ” ብለዋል። አብዛኛው ከክልሉ ውጭ ያለን የአማራ ሕዝብ በመጠበቅ፣ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ ክልሎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየደገፍን፤ ጉድለታቸውን ደግሞ ማስረዳት መቻል አለብን በማለት አክለው ተናግረዋል።
የሕግ የበላይነት ካልተከበረ አገሪቱ ወደሌላ ችግር እየገባች ነው ያሉት አቶ አገኘው፤ “በወሳኝነት ኦነግ ሸኔ፣ ትሕነግ (ወያኔ/ሕወሓት) ጠላቶቻችን ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ናቸው ግድያ የሚፈጽሙት። እነዚህ ኃይሎችን መታገል አለብን። እነዚህ ኃይሎች እስካሉ ድረስ ግድያ አይቆምም።” በማለት በጉባዔው ላይ ያላቸውን አመለካከት አንጸባርቀዋል። (ኢዛ)