Agegnew Teshager

አቶ አገኘው ተሻገር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

የወልቃይት፣ ጠገዴና ራያን ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ዋጋ ያስከፍላል

ወጣቱ ለሚደረግለት የትግል ጥሪ ተዘጋጅቶ ይጠብቅ

ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 7, 2021)፦ የአማራን ሕዝብ ነጥሎ ለማጥቃትና ከአማራ ጋር የምናወራርደው ሒሳብ አለን በሚል ከትሕነግ እየተቃጣ ያለውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችለን ብቃቱም ችሎታውም እንዳላቸው የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ገለጹ።

ይኼ ኃይል (ትሕነግ) የአማራን ሕዝብ የቻለው ሁሉ አድርጎ በድሎታል። በምድር ላይ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን በደሎች በሙሉ በአማራ ሕዝብ ላይ አድርሷል። ስለዚህ አሁን የአማራ ሕዝብ ጠላቴ ነው ብሎ ቢነሳ፤ አዲስ ሊኾንብን አይገባም። ትሕነግ ይዞት የመጣውንና በውስጡ ደብቆት የኖረውን፣ አልፎ አልፎ ብቅ ይል የነበረውን፣ በተግባር ይገለጽ የነበረውን ፀረ-አማራ እንቅስቃሴ፤ አሁን በኦፊሴል ወጥቶ ነው ያወጀው። ስለዚህ ትሕነግ የአማራ ሕዝብ ጠላት ነው ብሎ መያዝና መደምደም ተገቢ ነው።አቶ አገኘው ተሻገር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

ርዕስ መስተዳድሩ አቶ አገኘው ተሻገር ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) የአማራን ሕዝብ በመነጠል ለማጥቃት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አማራ ላይ ያነጣጠረ ቢኾንም፤ ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን አሁን አማራን ነጥሎ ለማጥቃት ቢሞክር በሁሉም ረገድ ዝግጁ ስለመኾናቸው ተናግረዋል።

ትሕነግ ከመነሻው ማኒፌስቶውን ሲያዘጋጅ ጀምሮ “ዋንኛ ጠላቴ የአማራ ሕዝብ ነው” ብሎ መቋቋሙ የራሱ ታሪካዊ ዳር እንዳለው ገልጸዋል። ትሕነግ የአማራ ብቻ ሳይኾን የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ነው ብለዋል። “ይኼ ኃይል (ትሕነግ) የአማራን ሕዝብ የቻለው ሁሉ አድርጎ በድሎታል። በምድር ላይ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን በደሎች በሙሉ በአማራ ሕዝብ ላይ አድርሷል። ስለዚህ አሁን የአምራ ሕዝብ ጠላቴ ነው ብሎ ቢነሳ፤ አዲስ ሊኾንብን አይገባም።” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አገኘው ተናግረዋል።

“ትሕነግ ይዞት የመጣውንና በውስጡ ደብቆት የኖረውን፣ አልፎ አልፎ ብቅ ይል የነበረውን፣ በተግባር ይገለጽ የነበረውን ፀረ-አማራ እንቅስቃሴ፤ አሁን በኦፊሴል ወጥቶ ነው ያወጀው። ስለዚህ ትሕነግ የአማራ ሕዝብ ጠላት ነው ብሎ መያዝና መደምደም ተገቢ ነው።” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አክለውም የትሕነግ ፀረ-አማራነት የቆየና የኖረ መኾኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም ሒሳብ የሚወራረድበት ሕዝብ የለም በማለት፤ ሒሳብ ሲወራረድበት ግን ቆሞ የሚጠብቅ ሕዝብ እንደሌለም አስረድተዋል።

“ሒሳብ እናወራርዳለን የሚሉ የትሕነግ አመራሮች ካሉ፤ የሚወራረደውን ማናቸውንም ሒሳብ አብረን ለማወራረድ ዝግጁ ነን” በማለት የትሕነግን ወቅታዊ ምልከታ አጣጥለውታል።

በትሕነግ አመራሮች ዘንድ እንዲህ ያለው አመለካከት ቢኖራቸውም፤ “እኛ ግን ሒሳብ አናወራርድም። እኛ ሒሳብ የምናወራርድበት ሕዝብ የለም። የትግራይ ሕዝብም ጠላታችን አይደለም” ብለው፤ ትሕነግ ግን ጠላታችን ነው በማለት ፀቡ ከሕዝብ ሳይኾን ከትሕነግ ጋር ስለመኾኑ አስረድተዋል።

ስለዚህ የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋትና ለማዋረድ ትሕነግ ወደኋላ የማይመለስ ቢኾንም፤ አደርገዋለሁ ብሎ እየገለጸ ያለውን ጥቃት ግን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመኾን ለመመከት አስተማማኝ ኃይል መኖሩንና ለዚህም ዝግጁ መኾናቸውን በትናንቱ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

አካባቢዎች በጉልበት ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ ማንኛውም ዋጋ የሚከፈል መኾኑን አስገንዝበዋል። እነዚህ አካባቢዎች ድሮም የማን እንደነበሩ እንደሚታወቁ ገልጸዋል። ራያ የወሎ ጠቅላይ ይዛት የነበረ ሲሆን፣ ጸለምት፣ ወልቅይትና ጠገዴ የጎንደር (ቤገምድር) አካባቢዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ ይሔ የረዥም ጊዜ ሳይኾን የሠላሳ ዓመት ታሪክ በመኾኑ ጠቅሰው፤ “በእኛ ዕድሜ የተወሰደ ነው” ብለዋል።

አክለውም እነዚህ አካባቢዎች በማጭበርበር ተወስደው የነበሩ መኾኑን፣ እንዲያውም ሕዝብ ሳይወስን የተወሰዱ መኾናቸው ያስረዱት አቶ አገኘው፤ ሕዝብ ለዚህ ጥያቄ ዋጋ መክፈሉንም አስረድቷል።

አሁን መታወቅ ያለበት ሌላው ጉዳይ ያሉት ደግሞ የወልቃይት፣ ጠገዴና የራያ ጉዳይ የአማራ ጉዳይ ሳይኾን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። ስለዚህ እነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚደረግ ማናቸውም ጉዳይ በሕግና በሥርዓት ብቻ የሚፈጸም ነው ብለዋል።

“ከዚህ ውጭ ራያን፣ ጸለምትን፣ ወልቃይትና ጠገዴን በጉልበት እንወስዳለን የሚባለው ነገር አይቻልም” በማለት ጠንከር ያለ አቋማቸውን ያንጸባረቁት አቶ አገኘው፤ በእነዚህ አካባቢዎችን በጉልበት ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ ዋጋ የሚከፍሉ መኾኑ መታወቅ አለበት ብለዋል።

በተለይ ሒሳብ የሚወራረድ ተልእኮ ተቀብሎ የሚንቀሳቀስ ሕዝብና ወጣት ካለ ከዚህ ራሱን ያቅብ በማለት አስጠንቅቀዋል።

ሕዝብን በርበሬ፣ ድንጋይ ቆንጨራ አስይዞ ወደ አማራ ክልል ማዝመት እንደማይቻል ያስጠነቀቁት አቶ አገኘው፤ ያኔ የምናወራርደው ሒሳብ የከፋ ይኾናልም ብለዋል።

ስለዚህ ሒሳብ እናወራርዳለን የሚለው አገላለጽ ፀረ-ሕዝብ መኾኑንና ንቀት የተሞላበት እብሪት ስለመኾኑም ገልጸዋል።

“የትሕነግ አሸባሪ ቡድን የትግራይን ሕዝብ ይወክላል የሚል ግምገማ የለንም” ያሉት አቶ አገኘው፤ አሸባሪ ቡድኑና ሕዝቡ በጣም የተለያዩ ናቸው። የትግራይ ሕዝብ በትሕነግ እየተጨቆነ የሚኖርና የተበደለ መኾኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ትሕነግን የሚቃወሙ በርካቶች መኾናቸውን፣ ይህ ማለት ግን ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ደግሞ ትሕነግን አይደግፍም ማለት እንዳልኾነ ግን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ውስጥ ስላሉ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጉዳይ ለቀረበ ጥያቄም፤ በአማራ ክልል በርካታ የትግራይ ተወላጆች ስለመኖራቸው አረጋግጠው፣ እነዚህ ተወላጆች ከአማራ ሕዝብ ጋር የተሳሰሩ በመኾኑ እንደቀደመው ጊዜ በሰላም መኖር ይችላሉ። በገዛ አገራቸው ማንም ሊነካቸው አይችልም ብለዋል። ነገር ግን የትሕነግ ጁንታ ተላላኪና ተልእኮ ፈጻሚ በመኾን የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከተገኙ ግን እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

የሕወሓት ጁንታ ቡድን በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ ስለመኾኑ የተናገሩት አቶ አገኘው፤ ይህ ኃይል ሥርዓት መያዝ ይኖርበታል በማለት ተናግረዋል።

በመግለጫ ማጠቃለያቸው ላይም ይህንን ኃይል ለመታገል በሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉም ከጐናችን ይኹን የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል። የአማራ ወጣቶችም ሒሳብ ሲወራረድባቸው ቆመው የማይጠብቁ በመኾኑ፤ ለማንኛውም የትግል ጥሪ ዝግጁ ኾነው እንዲጠባበቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ በኋላ ትሕነግ ጠላት ስለኾነ እንደ አመጣጡ ለመመለስ የክልሉ መንግሥት በሚያደርገው ጥሪ ዝግጁ ኾናችሁ ጠብቁን በማለት አሳስበዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!