Tekleberhan Ambaye Construction Plc

ተክለብርሃን አምባዬ ኮንትራክሽን

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላ ከሌሎች የግል ባንኮችም ተበድሯል

ኢዛ (ሰኞ ነኀሴ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. August 23, 2021)፦ ከተለያዩ ባንኮች ቢሊዮኖች የሚገመት ብድር በመውሰድ እና ዕዳዎቹን ባለመክፈል በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከአምስት በላይ በማስያዣነት ያቀረባቸው ሕንፃዎች ለጨረታ መቅረባቸውን ምንጮች ገለጹ።

እንደ ምንጮች ገለጻ ተክለብርሃን አምባዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከሌሎች የግል ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር የወሰደ ሲሆን፤ እነዚህን ብድሮች በአቶ ተክለብርሃን አምባዬ እና በሌሎች ግለሰቦች ባለቤትነት የተመዘገቡ ሕንፃዎች ለብድር ማስያዣ ተደርገው ነበር።

ኾኖም ባንኮቹ የሰጡት ብድር በወቅቱ ሊመለስ ባለመቻሉ በዚህ ዓመት ብቻ ተክለብርሃን አምባዬ ለብድር ማስያዣነት ካቀረባቸው ሕንፃዎች ወደ አምስት የሚኾኑ ሕንፃዎች ለጨረታ መቅረባቸውን እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ለጨረታ ከቀረቡት ውስጥ “ኢድና ሞል” የተባለው ሕንፃ አንዱ ሲሆን፣ ይህንን ሕንፃ ለመሸጥ በቀረበ ጨረታ መሠረት አንድ የቻይና ኩባንያ 810 ሚሊዮን ብር ዋጋ በመስጠት ሕንፃውን ለመግዛት መቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል።

ባጠናቀቅነው ሳምንት ተክለብርሃን አምባዬ በዋና መሥሪያ ቤትነት የሚጠቀምበት የነበረው እና ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘውን ሕንፃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመሸጥ ባወጣው ጨረታ ሕንፃውን ለመግዛት ሃያት ሪልስቴት 610 ሚሊዮን ብር ዋጋ አቅርቧል።

ከኢድና ሞል እና ከዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ባሻገር ተክለብርሃን አምባዬ በዕዳ ምክንያት ጨረታ የቀረበበት ሌላው ሕንፃ ደግሞ ከጥቂት ዓመታት በፊት አኪር ከተባለ የኮንስትራክሽን ድርጅት በሽያጭ ሲጠቀልል የተረከበው ሕንፃ ነው። ይህ ሕንፃ አኪር ኮንስትራክሽን በዋና መሥሪያ ቤት ሲጠቀምበት የነበረ ሲሆን፣ ቃሊቲ ውኃ ልማት አካባቢ የሚገኝ ሕንፃ ነው።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይህንን ሕንፃ ለመሸጥ በወጣ ጨረታ አሸናፊው ኩባንያ ሕንፃውን ለመግዛት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ እንደሰጠ ምንጮች አስታውቀዋል።

ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላ ከሌሎች የግል ባንኮችም ብድር የወሰደ መኾኑን የሚገልጸው የምንጮች መረጃ፤ ከነዚህ ባንኮች ውስጥ ዳሽን ባንክ አንዱ ነው።

ዳሽን ባንክ ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ለሰጠው ብድር ማስያዣ የነበረውን የአንድ ግለሰብ ሕንፃ በዚህ ዓመት ጨረታ አውጥቶ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ሸጧል። ይህ ሕንፃ ቦሌ ሃያት ሆስፒታል አካባቢ የሚገኝ ነው ተብሏል።

ከተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ብድር ጋር በተያያዘ በተመሳሳይ በማስያዣነት ባንኮች የተረከቡዋቸው ሌሎች ሕንፃዎች መኖራቸውን ምንጮች ጠቁመው፤ በዚህ ዓመት ብቻ አምስት የሚኾኑትን ባንኮች በጨረታ እንዲሸጡ ውሳኔ የሰጡባቸው ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ