መጠሪያው ”የኢትዮጵያ አደራ ድምፅ ራዲዮ” ተብሏል

በማትያስ ከተማ

Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም. November 5, 2008)፦ "የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረክ" (Ethiopian Current Affairs Discussion Fourm) የሚባለው የፓልቶክ መድረክ አባላት ለኢትዮጵያና ለአካባቢው ሀገሮች በቀጥታ የሚተላለፍ ራዲዮ ለማስተላልፍ ዝግጅት መጨረሳቸውን አሳወቁ። ራዲዮው ሥርጭቱን ዛሬ ይጀምራል።

 

ይኸው “የኢትዮጵያ አደራ ድምፅ” የተሰኘው የራዲዮ ጣቢያ ከዛሬ ከጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም (November 5, 2008) ጀምሮ ዘወትር ረቡዕ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ድረስ በ13790 ኪሎ ኸርዝ ወይም በ22 ሜትር ባንድ አጭር ሞገድ እንደሚያስተላልፍ ታውቋል።

 

በዚህ ራዲዮ ሥርጭት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና ልዩ ልዩ ጉዳዮች እንደሚተላለፍ ሲገለጽ፤ ለሥርጭቱ የሚያስፈልገውን ወጪ የሸፈኑት የውይይት መድረኩ አባላት ናቸው። ወደፊትም ከሌሎች ሀገር ወዳዶች ጋር በመሆን ለሥርጭቱ የሚያስፈልገውን ክፍያ ለማሰባሰብ ማቀዳቸው ተገልጿል።

 

ራዲዮው የሚመራው በቦርድ አባላት ሲሆን፣ የቦርድ አባላቱ የተመረጡት ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረክ (Ethiopian Current Affairs Discussion Fourm) መሆኑ ታውቋል። የራዲዮ ዝግጅቱን የሚያስተላልፉት ከመድረኩ የተመረጡ ባለሙያዎች እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ አደራ ድምፅ ራዲዮን በተመለከተ ባለፈው እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. ገለጻና ማብራሪያ ለየኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረክ ተሳታፍዎች የቀረበ ሲሆን፣ የራዲዮኑን መከፈቱንም አስመልክቶ ልዩ ልዩ ግጥሞችና ጽሑፎች ቀርበዋል።

 

ስለራዲዮኑም ሆነ ስለ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረክ የበለጠ ለመረዳትና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የመድረኩን ድረ ገጽ በhttp://www.ecadforum.com/  ያገኙታል። (ወደ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መነጋገሪያ መድረክ ድረ ገጽ ውሰደኝ)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!