Happy Ethiopian Newy Year! መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ!

አቶ ሽመልስ አዱኛ

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አዱኛ

ኢሬቻና አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ኢዛ (ከመስከረም 19 - 25 ቀን 2012 ዓ.ም.) - አገሪቱ በዚህ ሳምንት የተለያዩ ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎችን አስተናግዳለች። በሳምንቱ ውስጥ አየሩን የያዘው በሚዲያዎችም ረገድ ሰፊ ሽፋን የተሰጠው፣ ብሎም አነጋጋሪ ሆኖ ያለፈው የኢሬቻ በዓል አከባበር ነው። የኢሬቻ በዓል አዲስ አበባ ላይ እንዲከበር ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ሒደቱ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡበት የቆየ ቢሆንም በሰላም ተጠናቋል።

ከአከባበሩ ጋር ተያይዞ ግን በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ከኢሬቻ መገለጫ አርማ በቀር የሌላ ፖለቲካ ድርጅቶች አርማ እንዳይኖር ትእዛዝ የተላለፈ ቢሆንም፤ ሾልከው የገቡ ናቸው የተባሉ የኦነግ አርማዎች አልፎ አልፎ ታይተዋል። የፌዴራል ፖሊስ ግን በኢሬቻ ዋዜማ ላይ የኦነግ አርማዎች ወደ አደባባዩ እንዳይገባ በፍተሻ ጭምር እስከመሰብሰብ ደርሶ ነበር። በአዲስ አበባም ይሁን በቢሾፍቱ የኢሬቻ በዓል ላይ ግን ሊቆጠሩ የሚችሉ ጥቂት የኦነግ ባንዲራዎች መታየታቸው ግን አልቀረም ነበር።

ከዚህ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ አነጋጋሪ የተባለው ክስተት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበዓሉ ዋዜማ ላይ ነፍጠኞች በከለከሉን ቦታ ላይ ኢሬቻን ስለማክበራቸው የመግለጻቸው ነገር ብዙዎችን ያነጋገረ፤ እንዲሁም ለምን እንዲህ ይባላል ተብሎ ያከራከረ ነበር። ይህ የምክትል ፕሬዝዳንቱ ያልተጠበቀ ንግግር ከለውጡ አራማጆች አመለካከት ጋር ይገናኛል አይገናኝም የሚል መከራከሪያ እስከ መፍጠር የደረሰም ነበር። ታዋቂው የፍልስፍና ምሁር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ይህንን የአቶ ሽመልስ ንግግር ተከትሎ ከዚህ በፊት ስለእርሳቸው የገለፁትን መልካም ነገር በማስታወስ በሠጠሁት መረጃ ላሳሳትኳችሁ ይቅርታ እስከ ማለት የደረሱበት ነው። ዶ/ር ዳኛቸው ከዚህ ቀደም ስለአቶ ሽመልስ ብቃትና መልካምነት ገልፀው እንደነበር አይዘነጋም።

ቅማንትና አካባቢው

በዚህ ሳምንት ጐልተው ከተሰሙት ዜናዎች መካከል በአማራ ክልል በቅማንት አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ያስከተለውን አደጋ ተከትሎ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ነው። በዚህ መግለጫው በቅማንት አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ከጀርባው ሌላ ኃይል ያለው መሆኑን በማመልከት ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ያስጠነቀቀበት ጭምር ነበር። “አጀንዳው የአማራን ሕዝብ ማዳከም ነው፤ መንገድ የተዘጋውም ባለሀብቶችን በኢኮኖሚ ለማዳከም ነው።” የሚል አንደምታ ያለው መግለጫ ከክልሉ ተሰጥቶበታል። በክልሉ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ከቅማንት ማንነት ጋር የተሳሰረ አስመስሎ በሦስተኛ ወገን የተቀነባበረ ነው የተባለው ግጭት ነው።

በጭልጋና አካባቢው በተጠረው ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ችግሩ እልባት እንዲያገኝ እየጠየቁ መሆኑን የሚያመለክተው የክልሉ መረጃ የጉዳዩን አሳሳቢነትም የሚያመላክት ነበር። የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው አሁን ላይ “በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ችግር አንፃራዊ ሰላም ታይቶበታል” ብለዋል። አክለውም፤ “በአካባቢውና በፀጥታ ኃይሉ ላይ ጥቃት ሊያደርስ የነበረው የጥፋት ኃይልም አልተሳካለትም” ያሉት የቢሮ ኃላፊው አካባቢው በአንፃሩ ተረጋግቷል ብለዋል። ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ በማመልከትም፤ በአካባቢው አሁንም ድንገተኛ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎች መኖራቸውንና የክልሉ መንግሥት ጥፋተኞችን ለመያዝ ጥረት እያደገ እንደሆነም አብራርተዋል።

የጥፋት ኃይሉ ዋና ዓላማው የመተማ - ጎንደር መንገድን ዘግቶ ባለሀብቶች ምርታቸውን በወቅቱ እንዳይሰበስቡና ለገበያ እንዳያደርሱ በማድረግ በኢኮኖሚ ማዳከም መሆኑን ጭምር ያብራሩት የቢሮው ኃላፊው፤ “በዚህ ደግሞ አንደራደርም፤ በአጭር ጊዜ መንገዱ ክፍት ይሆናል” በማለት የገለፁ ሲሆን፤ እንደተባለውም መንገዱ ክፍት ሊሆን ችሏል። ይሁንና አሁንም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሁሉም ሕብረተሰብ የበኩሉን እንዲሠራና አካባቢውን ከጥቃት እንዲጠብቅ በክልሉ ሚዲያዎች በተለያዩ መልኮች በኩል ተደጋጋሚ መልእክቶች ሲተላለፉ ሰንበተዋል። በጥፋት ኃይሉ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ለመያዝ እየተሠራ እንደሆነና የሕዝቡን ጥያቄም በሰላማዊና በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም በማብራራት በወቅቱ የነበረውን ችግር የገለፁበት ነበር።

አጀንዳው የአማራን ሕዝብ የማዳከም ነው በሚል የገለፁት አቶ አገኘሁ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህን አውቆና አጀንዳ ከመቀበል ወጥቶ ሕዝቡን ከአጀንዳም ነፃ እንዲያደርግም የጠየቁበት ነበር። የክልሉ መንግሥት ባወጣው ይፋ መግለጫም ክልሉን ወደ ግጭትና ኹከት እንዲገባ እየሠሩ ያሉ አካላትና ጽንፈኛ መገናኛ ብዙኀን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ባለፉት ዓመታት ተነስቶ የክልሉ መንግሥትና ምክር ቤቱ ተገቢ ምላሽ የተሰጠበት መሆኑን የሚያመለክተው መረጃ፤ ይሁን እንጂ በምላሹ ያልተካተቱ ቀበሌዎች አሉ በሚል ከኮሚቴዎቹ አባላት ቅሬታ በማንሳት አሁን ለተፈጠረው ግጭት ቀዳዳ ፈጥሯል ይባላል።

እንደ አቶ አገኘሁ ተጨማሪ ማብራሪያ በአካባቢው ግጭቱ እንዲፈጠር ከኋላ ሆነው የሚደግፏቸው ኃይሎች አሉ ብለው የክልሉ ፖሊስና ተራ የመከላከያ ወታደር የማይታጠቃቸውን እንደ ስናይፐር፣ መትረየስና ሌሎች መሣሪያዎችን በመያዝ ጥቃቱን ለማድረስ የሚጥሩ ስለመሆናቸውም ተገልጿል። ስማቸውን ያልጠቀሷቸውና ከኋላ አሉ የሚባሉ ኃይሎች አማራን ለማዳከም የተፈጠሩ ናቸውም ብለዋል።

እንዲህ ያለ ይዘት ካለው መግለጫና ማብራሪያ በኋላ በክልሉና ግጭቱ በተከሰተበት አካባቢ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የኢሕአዴግ ውሕደት በአቶ ሙስጠፌ

ባሳለፍነው ሳምንት ሌላው እንደ አበይት ጉዳይ የሚጠቀሰውና በተለያዩ አቀጣጫዎች አስተያየት ሲሠጥባቸው ከነበሩ አገራዊ ወሬዎች አንዱ የኢሕአዴግ ውሕደትን የሚመለከቱ ናቸው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰሞኑ አስተያየታቸውን ከሰነዘሩት ውስጥ በአሁኑ ወቅት የለውጡን እንቅስቃሴ በመደገፍና አገራዊ አንድነትን በማቀንቀን የሚታወቁት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ናቸው።

በጥናት የተደገፈው የኢሕአዴግ የውሕደት ጉዞ በደንብ ውይይት ተደርጎበት ወደ ተግባር የሚገባ በመሆኑ የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጥ እንደሚሆን እምነታቸውን በማንፀባረቅ ስለ ውሕደቱ ጠቀሜታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የውሕደቱ ጉዳይ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተጠጋ መኾኑን ያስታወሱት አቶ ሙስጠፌ፤ የኢሕአዴግ ውሕደት ከብዙኀኑ በጎ ምላሽ እየተንጸባረቀበት ቢሆንም፤ ለመቃወም የሚሞክሩ አካላትም አሉ ብለዋል። ተቃውሞ የሚያቀርቡት አካላት ለተቃውሟቸው እንደመከራከሪያ ከሚቀርቡ ነጥቦች አንዱ “የመጨፍለቅ ዓላማን ያነገበ ነው” የሚል እንደሆነም ገልፀዋል። እርሳቸው ግን ኢሕአዴግ ይተች ከተባለ በግንባር ባለበት አቋሙ የአጋር ድርጅቶቹን ሕልውናም ሆነ መብት እንደተቋም እየገደበ ያለ በመሆኑ ነው።

አያይዘውም የእንጨፈለቃለን ሐሳብን የሚያነሱት ለምን የበላይ አንሆንም ከሚል ስሜት የመጣ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሙስጠፌ፣ ምንግዜም ወደተሻለ ምዕራፍ ጉዞ ሲጀመር ጥቂቶች ሊያጡ የሚችሉትን ጥቅም ብቻ በማሰብ እንቅፋት መሆናቸው የለመደ እንደሆነም አብራርተዋል። እነዚህ ወገኖች የሚያቀርቧቸው የመቃወሚያ ነጥቦች ይኖራሉ ያም፣ አያስገርመኝም ብለዋል አቶ ሙስጠፌ።

አሁን ግንባሩን ወደ ውሕደት አምጥቶ ፓርቲ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ በተለይ አጋር በሚል ስያሜ የተገደበው የሕዝቦች መብት ዋስትናን የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የኢሕአዴግ አባል መሆን ግድ ነበር የሚሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአራቱ ፓርቲዎች አባል ያልሆነ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ከዚህ ሐሳብ ተገልሎም ነበር በማለት፣ ይህም በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ዜጎች እንዲኖሩ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ የውሕደቱ ጉዳይ ጠቀሜታው ሰፊ እንደሆነም አብራርተዋል።

“በጥናት የተደገፈው የኢሕአዴግ የውሕደት ጉዞ በደንብ ውይይት ተደርጎበት ወደ ተግባር የሚገባ በመሆኑ የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል። በዚህ የውሕደት ጉዳይ የሐረሬ ክልል መስተዳደርም ተመሳሳይ አቋም ያለው መልዕክት የተሠራጨው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ውሕደቱ እውን ይሆናል የሚለው መረጃ በተደጋጋሚ መነገር እያስነሳ ካለው ጥያቄ ውስጥ ሕወሓት የውሕደቱ አካል ይሆናል ወይ? የሚለው ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ያለመስማማት እያለ እንዴት ውሕደቱ ይካሄዳል የሚለው ነው። በተለይ የትግራይ የመገናኛ ብዙኀን ውሕደቱን የሚፃረሩ ትርክቶች ያሉዋቸው ዘገባዎችን ማሠራጨታቸው ጉዳዩን የበለጠ አነጋጋሪ እያደረገው ነው።

ተቃዋሚዎችና የረሃብ አድማ

በሳምንቱ ሽፋን ከተሰጣቸው ዘገባዎች ውስጥ 70 የሚሆኑ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅርቡ ተሻሽሎ የፀደቀውን የምርጫ ሕግ በመቃወም ያሰሙት ድምፅ ነበር። እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሰባስበው በወጣው ሕግ ላይ የተካተቱ አንዳንድ አንቀፆች ሕጉ ከመጽደቁ በፊት ረቂቅ ውይይት ሲደረግ ካቀረብነው ሐሳብ በተቃራኒ እንዲካተት ተደርጓል የሚል ነው። ፓርቲዎቹ በብርቱ ተቃውሞ ያነሱበት የሕጉ አንቀፆች በምርጫ የሚወዳደር ፓርቲ ሊያስፈርም ይገባዋል የሚል ነው። ይህንኑ ጥያቄያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያስገቡ ሲሆን፣ ሕጉ መሻል ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

ማሳረጊያ ያደረጉትም ፓርላማው ሥራ ሲጀምር በዚህ ጉዳይ ላይ ሊመክር መቻል አለበት ብለዋል። ይህ ባይሆን ግን ፓርቲዎቹ መሪዎች የረሃብ አድማ እንመታለን በማለት አሳውቀዋል።

ፓርቲዎቹ ይህንን ቢሉም አንዳንድ ወገኖች ግን ይህንን ያህል ፊርማ ማሰባሰብ ካልቻሉ እንደ ፓርቲ ሊቆጠሩ ይችላሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ይሰነዝራሉ። በተለይ ደግሞ በእርግጥ እነዚህ 70 ነን ያሉ ፓርቲዎች በትክክል በተጠቀሰው ቁጥር ልክ የተሰባሰቡ ስላለመሆናቸው እየተነገረ ነው።

እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት የተሰማ ነገር ባይኖርም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ግን በጉዳዩ ላይ በደንብ ስለመመከሩ የሚያመለክቱ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶች ገልጿል። እስከ ረሃብ አድማ የሚደርስ እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸው የተሰማው የ70ዎቹ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃዎቻችንም እናሳውቃለን ብለዋል።

በ70ዎቹ ፓርቲዎች ስብስብ ውስጥ እንደ ኢዜማ፣ ኦፊኮ፣ ኦነግና የመሳሰሉት በርካታ አባላት እንዳላቸው የሚመገቱ ፓርቲዎች ከ70ዎቹ ፓርቲዎች ውስጥ የሌሉበት ሲሆን፣ የአገሪቱ ፓርቲዎችን በሙሉ በማካተት የተደራጀው የፖለቲካ ድርጅት መድረክም ስለጉዳዩ ምንም ዐይነት እውቅና እንደሌለው ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!