EZ weekly news digest

ከጥቅምት 10 - 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

ከ67 በላይ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው ክስተት ዙሪያ ልዩ ጥንክር

ኢዛ (ከጥቅምት 10 - 16 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ በመልካም አላሳለፈችም። ከሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ የነበረው ድባብ ከወትሮው የተለየ ነበር። ሰዎች በአደባባይ ሞተዋል፣ ቆስለዋል ንብረት ወድሟል። የአገሪቱን ሰላም የሚያናጉ የተለያዩ ተግባራት የተፈፀሙበት ነበር።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች መንገድ ተዘግተው እንቅስቃሴዎች የተገቱበት፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉበትም ሳምንት ነበር። ይህ አገሪቱን በተለየ ስጋት ውስጥ የከተተው ግርግር የተፈጠረው፤ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ የለቀቀው አንድ የፈስቡክ መልእክት ነው። ከዚህ መልእክት በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ለሰላማዊ ሰልፍ ተጀመረ የተባለ እንቅስቃሴ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ግርግር በመግባቱ፤ ክቡሩ የሰው ልጅ ተቀጠፈ። ቆሰለ። ንብረት ወደመ። ግርግሩ በተፈጠረባቸው ከተሞች እስካሁን በትክክል የሞተውን ሰው ቁጥር የሚያመላክት ይፋዊ መረጃ አልተሠጠም። ነገር ግን በሐረር፣ ደብረዘይት፣ ዱከም፣ ድሬዳዋ፣ በናዝሬት፣ በአርሲ ነገሌ፣ በባሌ ሮቤ፣ ዶዶላና በሌሎች ከተሞች የተገደሉ ኢትዮጵያውያን የቀብር ሥርዓታቸው ተፈጽሟል። በተለይ በዶዶላ ቀብር ለመፈፀም ያልተቻለበት ሁኔታ ገጥሞ እንደነበርም ሲገለጽ ነበር።

ከንብረት አንፃርም ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል። የመኖሪያ ቤቶች ነደዋል። ፋብሪካ ሳይቀር እሳት ተለቆበታል። ይህ ውድመት በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ በእሳት እንዲበላ አድርጓል። ሰዎች በጥይት፣ በቆንጨራና በመሳሰሉት ተወግተውና ተወግረው ተገድለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ ግርግር ቀዳሚ የሆነው ክስተት በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ መዘጋቱ ነው። ይህ ደግሞ የዜጐችን የመንቀሳቀስ መብት ከመገደቡ ባለፈ፣ የንግድ ልውውጥ እንዲቋረጥ፣ የሚበላሹና የማይበላሹ የተለያዩ ምርቶችን የያዙ ተሽከርካሪዎች፤ በድንጋይ የታጠሩ አውራ ጐዳናዎችን ለመሻገር ተስኗቸው ባሉበት እንዲቆሙ ተገድደዋል። አንዳንዱም ወደመጣበት ሲመለስ ታይቷል።

ይህ ሁሉ ሲደማመር በዚህ አንድ ሳምንት አገር ያጣችው ብዙ ነገር መሆኑን ያሳያል። በዚህ ግርግርና ውጥረት ውስጥ ሰዎች ችግር ውስጥ ሲገቡ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል እርምጃ አልወሰደም በሚል ቅሬታ የቀረበባቸው አካባቢዎች አሉ። በአብዛኛው መረጋጋቱ የታየው የመከላከያ ኃይል እንዲገባ ከተፈቀደ በኋላ እንደሆነም ተገልጿል። ድርጊቱ የዚህን ያህል ቢከብድም፤ ከኦሮሚያ ክልል አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች የተደመጡት መግለጫዎች ግን በብርቱ ሲያነጋግሩ ነበር። በተለይ ጃዋር ዓይናችን ነው የሚል ቃላትን ያዘሉ ድምፆች፤ ምን እየሆነ ነው የሚል ጥያቄ በማስነሳት ላይ ነው። የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትም ንግግር ከዚሁ አንጻር የሚታይ ኾኖ መነጋገሪያ መኾኑ አልቀረም።

ተጠያቂው ማነው? ጉዳዩ በሕግ መታየት አለበት!

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የተለኮሰው ግርግር፣ ለጠፋው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ተጠያቂው ማነው? የሚለውም ጥያቄ መልስ የሚሻ ነው። የሕግ ጉዳይም እዚህ ላይ የሚነሳ ነው። ንፁኀን እንዲገደሉ፣ ንብረታቸው እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑ መጠየቅ አለባቸው የሚል ድምፅ እየተሰማ ነው። ጉዳዩ በሕግ መታየት አለበት የሚለው ጥያቄ እየገፋ ሲሆን፣ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ለሰው ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን፣ ግርግሩን በማነሳሳትም ተሳታፊ ናቸው የተባሉትን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ ስለመሆኑ ቢገለጽም፤ አሁን ያለበት ደረጃ በይፋ አልተገለጸም።

ሰሞናዊው ድርጊት አሁን እየበረደ የተዘጉ መንገዶችም እየተከፈቱ ቢሆንም፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው ድባብ ግን የአገሪቱን ፖለቲካ ትኩሳት ከፍ አድርጐታል። ከዚህስ በኋላ የሚለውም ጥያቄ መልስ የሚሻ ነው። የሕግ ጉዳይም እዚህ ላይ የሚነሣ ነው። ንጹሐን እንዲገደሉ፣ ንብረታቸው እንዲጠፋ ምክንያት የኾኑ መጠየቅ አለባቸው የሚል ድምፅ እየተሠማ ነው።

ጉዳዩ በሕግ መታየት አለበት የሚለው ጥያቄ እየገፋ ሲሆን፣ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ለሰው ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን፣ ግርግሩን በማነሳሳትም ተሳታፊ ናቸው የተባሉትን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ ስለመኾኑ ቢገለጽም፤ አሁን ያለበት ደረጃ በይፋ አልተገለጸም።

የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የአገር መከላከያ ሚኒስቴር

የጠቅላይ ሚኒስትሩን እግር መውጣት ተከትሎ የተፈጠረው ግርግር ሌላው መገለጫው፤ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሠጡ የተባለው መግለጫ ወጣ ያለ ሆኖ መገኘቱም ከሰሞናዊ ዘገባዎች መረዳት ይችላል።

ለዚህም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ላይ ተንፀባርቋል። ወቅታዊውን ጉዳይ አስመልክቶ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ኢንዶክትሪሽኔሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሜጀራ ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እንደገለፁት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አንዳንድ አመራሮችም የተሳሳቱ መግለጫዎችንና መልእክቶችን ሲሰጡ እንደነበር አመልክተዋል። ይህ ደግሞ ከእውነት የራቀ ስለመሆኑም ገልጸው፤ አክለውም አንዳንድ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች መከላከያ ሠራዊቱ ከሻሸመኔ እንዲመለስ ያደረግነው እኛ ነን ማለታቸውን ፈጽሞ ስሕተት ነው ብለዋል።

“እነዚህ አንዳንድ የተባሉት የተቃዋሚ መሪዎች ኹከትና ብጥብጡን ለማረጋጋት ሠራዊቱ ታዞ እያለ እንዲመለስ ያደረግነው እኛ ነን። ለመከላከያ እንዳትገቡ ተመለሱ ብለን ትእዛዝ የሠጠነው እኛ ነን። ትእዛዝ ስለሠጠን ሠራዊቱ እንዳይገባ ብለው ያስተላለፉት መልእክት ስሕተት ነው” ማለታቸው ይጠቀሳል።

አዳማ ላይም በተመሳሳይ ሠራዊቱ እንዳይገባ አድርገናል የሚልም መልእክት ስለመተላለፉ ጀኔራሉ ገልጸዋል። ሠራዊቱ ወደ ሻሸመኔ ያልገባው ችግሩ በክልሉ የፀጥታ ኃይል ሊፈታ ስለሚችል ነው ብለዋል። መከላከያ ከማንም ወገንተኛ ያለመሆኑንም ያመላከቱት ጀኔራሉ፤ ፓርቲዎች ሠራዊቱን የማዘዝ ሥልጣን እንደሌላቸውም ገልጸዋል። እንዲህ ዐይነት መግለጫዎች በሳምንቱ ውስጥ የተፈጠረው ችግር ምናልባትም ከዚህም በላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር ነው። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ችግሩ ጐልቶ የታየባቸው ከተሞች ውስጥ መከላከያ ገብቷል።

“መንግሥት ሕግ ያስከብር” ኢዜማ

በሰሞኑ አሳዛኝ ድርጊት ዙሪያ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ያሰባሰቡት አስተያየቶች ጐልቶ ሲቀርብ የነበረው አንኳር ሐሳብ፤ “መንግሥት ሕግ ያስከብር” የሚለው ነው።

ወቅታዊውን ችግር በተመለከተ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያዩ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን፣ እንደ ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎችም መግለጫ አውጥተዋል። በተለይ ኢዜማ ባወጣው መግለጫ “አገር የማዳን ጥሪ” በሚለ ርዕስ “በሥርዓት አልበኞች በተወሰደ የጥፋት እርምጃ የማይተካ የዜጐቻችንን ሕይወት አጥተናል። የብዙዎች አካል ጐድሏል። ዜጐች ያፈሩት ንብረት ወድሟል። እንዲሁም በተዘጉት መንገዶች ምክንያት ዜጐች ተንገላተዋል። የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል” በማለት ሁኔታውን ገልጿል። ፓርቲው ለደረሰው ጥፋት ጥልቅ ኀዘኑን በመግለጽ መጽናናትን ተመኝቷል።

የተፈፀመውን ሕገወጥና አሳፋሪ ተግባር አጥብቆ እንደሚያወግዝ ኢዜማ በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። በመግለጫው መቋጫ ላይም አገራችንን ከተደቀነባት አደጋ እንድንታደግ በአደራ ጭምር ጥሪ እናስተላልፋለን ብሏል።

ግርግሩን ተከትሎ የተስተዋሉ ለየት ያሉ ክስተቶች

እንደ ናዝሬት ያሉ ከተሞች የተዘጉ መንገዶችን እንዲህ ማድረግ አግባብ አይደለም በሚል ነዋሪው ራሱ እስከመክፈት የደረሰበት አጋጣሚ ነበር። ይህ ሌሎች ከተሞች ላይ የታየ ነው። በብዙ ቦታዎች የደረሰው ጥፋት በዋናነት በቡድን በተደራጁ ወጣቶተ የተፈፀመ ነው። ብዙ ቦታም ከሌላ ቦታ የመጡ ናቸው።

በሰሞኑ ግርግር ለየት ባለ ሁኔታ በመንገድ መዘጋት አምቦን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ያልቻሉ ተሽከርካሪዎች ወደየመጡበት ሲመለሱ፤ ተሳፋሪዎችን የያዙት ተሽከርካሪዎች ማረፊያ ካደረጉዋቸው ከተሞች አንዷ ወልቂጤ ነበረች።

በችግር ከተማዋ የደረሱትን እነዚህን መንገደኞች የወልቂጤ ነዋሪዎች የማረፊያ ቦታ ሠጥተው እንደ እንግዳ ተንከባክበው ሸኝተዋል። ግርግሩ ካሳየን አሳዛኝ ድርግት በዘለለ እንዲህ ዐይነት መልካም ምግባር ታይቷል።

ከሰሞኑ ግርግር እና ይህንኑ ተከትሎ በደረሰው ጥፋት የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎች እና የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ግርግሩ ወደ ሰላም እንዲመለስ የየራሳቸውን ጥረት አድርገዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ከሃይማኖት ተቋማት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት “በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ሁሉንም በጋራ የሚጐዱ፣ ቀውሶች የሁሉንም ዜጋ መስተጋብር የሚፈታተኑና ማኅበራዊ ትስስሮችን የሚበጣጥሱ በመኾናቸው፤ አላህ የሠጠን ጸጋ አካል የሆነችው ውድ እናት አገራችን ወደተባባሰ ችግር አዘቅት እንዳትገባ መጠንቀቅ ሃይማኖታዊም ዓለማዊም ግዴታ ነው” ብሏል።

ሕገወጠነትና ሥርዓት አልበኝነት እንዳይሰፍን፣ አላህ ክብር የሠጠው የሰው ልጅ ነፍስ እንዳይጠፋ ፖለቲከኞች ወደስክነት እንዲመጡ ሁላችንም አላህን እንለምናለን በማለት የሚገልጸው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ ቀውሱን ከሚያሰፉ ማናቸውም ተግባራት መቆጠብ እንደሚገባ ለመላው ሙስሊም ጥሪውን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እንድሪስ፤ “ሰው ኹኑ! ቅድሚያ ሰውነት ይቀድማል! ከሃይማኖት ሰው ይቀድማል! ከዘርም ሰውነት ይቅደም! አላህ ሰውን ከሁሉ በላይ አልቆታል” በማለት ከምንም በላይ ሰው ክቡር መሆኑን ገልጸው ነበር።

ኦቢኤን ቴሌቪዥን

የኦሮሚያ ግጭት እንዲፈጠር የሚሠሩ አካላት ሕብረተሰቡ እንዲያጋልጥ የጠየቁት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ከፍያለው ተፈራ በብሔርና በሃይማኖት ለማጋጨት የሚደረግን ሥራ መከላከልና ማጋለጥ እንደሚገባም ለኦቢኤን ቴሌቪዥን ተናግረዋል ተብሏል። በሌላ በኩልም ከሰሞኑ ግርግር ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ የአገር ሽማግሌዎች በሰጡት መግለጫ ወጣቶች ከሰሞኑ ከተከሰተው ግጭት እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ጥሪ ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

የቢቢሲ የአማርኛ አገልግሎት

የቢቢሲ የአማርኛ አገልግሎት እንደዘገበው ግርግሩ በተፈጠረ ማግስት የተደረገው የኦሮሞ የአገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ ሰዎች መግለጫውን የሰጡት በጃዋር መኖሪያ ቤት ነው። ጃዋር በዚህ መግለጫ ላይ አሁን ያለን አማራጭ ውይይት ብቻ ነው ማለቱን ይኸው የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በበኩልዋ፤ ጥያቄውን ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ የማቅረብ ባህሉን ማሳደግ እንዳለበት አሳስባለች። “ባለፉት ቀናት በተፈጠሩ ሁኔታዎች ምክንያት የተፈጠረው የእምነት ተቋማት ሥጋት የእኛም ስጋት ነው” በማለት የገለፁት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳትና የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብርሃነየሱስ፤ ወጣቱ ምንም ዐይነት ጉዳት ሳያደርስ ሐሳቡን መግለጽ አለበትም ብለዋል። የፀጥታ አካላትም ብቁ ዝግጅት በማድረግ ሕጋዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን በንቃት በመቆጣጠር የማስቆም ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

በጥቅል ሲታይ የሰሞኑ ግርግር የአገሪቱን የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ከትቶታል። አገር ባልተጠበቀ ሁኔታ በታመሰበት ወቅት በአገር ውጭ የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ አገር ከተመለሱ በኋላ የሚወስዱት እርምጃ ምን ይሆን? ከሚለው ጥያቄ ጐን ለጐን በጉዳዩ ላይ መግለጫቸውም ሲጠበቅ ነበር። ቅዳሜ ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ በላኩት መግለጫቸው፤ ሰሞኑን በተከሰተው እጅግ አሳዛኝ ግጭት በዜጐቻችንና በንብረታቸው ላይ በደረሰው ሁሉ ማዘናቸውን ገልጸዋል። የመግለጨቸውንም መቋጫ “ከዚህ የከፋ እንዳይገጥመን መንግሥትና ሕዝብ የሚጠበቅባቸውን ማድረግ አለባቸው። መንግሥት ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሁሉ ያደርጋል። ሕዝቡም ባለመለያየት ለአጥፊዎች አጀንዳ ባለመመቻቸት፣ አንዱ ለሌላው ጋሻና መከታ በመሆን ወንጀለኞችን አሳልፎ ለሕግ በመሥጠት፣ የተጐዱ ወገኖችን በመርዳት ታላቅነቱን ሊያስመሰክር ይገባል” ብለዋል። የጠቅላይ ሚንስሩን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን

ቀጣይ እርምጃው ምን ይሆናል የሚለው ግን አሁንም የሚጠበቅ ነው። ሌላው የሳምንቱ አበይት ክስተት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰሞኑን ግርግር ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን እግዚኦ ለአገር፣ እግዚኦ ለሰላም በሚል ምህላ እንዲደረግ ያወጀችበት ሳምንት ነው። ይህ የምህላ ጥሪ የተላለፈው ደግሞ ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በዚህ ሳምንት የምህላ ጥሪ ከማስተላለፍ ባለፈ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሲኖዶሱ ጉባዔ የተቀመጠበትም ነበር። ሲኖዶሱ ስብሰባውን ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ግን 12 ነጥቦች ያሉትን ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ በመወያየት መግለጫ አውጥቷል። ይህ መግለጫ በኦሮሚያና በተለያዩ አካባቢዎች ግርግር እየተፈጠረ በነበረበት ወቅት ነው።

በዚህ መግለጫ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉትን የሰላም እጦቶችና ግጭቶች በዝርዝር በማተት፤ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ንብረት መውደሙን ዜጐች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ሁሉ አትቷል። ጊዜ የማይሰጣቸው አሳሳቢ የሆኑ ችግሮችን ከግምት በማስገባት ከሌሎች አጀንዳዎች ሁሉ ቅድሚያ የሚሠጠው ሰላም ነው ብሎ ስለሚያምን አስቸኳይ መግለጫ ወጥቷል ብሏል። በዚህ መግለጫው በተለይ የተለያየ አመለካከት ያላቸው አካላት አገርን ሰላምና አንድነት ማዕከል ባደረገ መልኩ በሠለጠነ መንገድ ልዩነታቸውን ይፍቱ የሚለው ይገኝበታል። እንዲህ ያሉ ይዘቶች ያሉት መግለጫ ከተሠራጨ በኋል ስብሰባው የተጀመረ ቢሆንም፤ ከሰሞኑ ግርግር ተያይዞ በተለይ በዶዶላ በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰ ጥቃትና የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች መሞት በመሰማቱ፤ የሲኖዶሱ ስብሰባ እንዲቋረጥ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

ጥቃቱ በቤተክርስቲያኗ ላይ ብቻ ሳይሆን አገልጋዮችዋንም ሕይወት ያሳጣ ሆኖ መገኘቱ፤ ሲኖዶሱ በእጅጉ በመረበሹ መደበኛ ስብሰባው ተቋርጦ እየሆነ ያለውን ጸያፍ ተግባር በማውገዝ እንደገና መግለጫ ለውጭ ሚዲያዎች ጭምር ይሠጥ በማለት የሲኖዶሱን ጳጳሳት እስከማነጋገር ጉዳዩ ደርሶ እንደነበር ይጠቀሳል።

ጳጳሳቱ ስብሰባ ተቋርጣ አቋማችንን ማስተጋባት አለብን ብለው፤ በተለያዩ ወቅቶች በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና አገልጋዮቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ይቁም የሚል ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ በሚጠበቅበት ሰዓት፤ በድጋሚ አዲስ ጥቃት መከሰቱ “እኮ ለምን?” ማሰኘቱ ሲሆን፤ ይሠጥ የተባለው አስቸኳይ መግለጫ ግን እንዲዘገይ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቷ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከመግለጫው በፊት ከሲኖዶሱ ጋር እንመክራለን በማለታቸው ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ይፋ እንዳደረገውም፤ በብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓርትሪያክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት በጋራ ኾነው ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያየተዋል። ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር የተወያዩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ የሰላም ሚንስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልና የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ናቸው። ሰዓታት የወሰደ ነው የተባለው ይኸው ውይይት ምን ይዘት እንዳለው እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።

ይህ በዝግ የተደረገው ውይይት የተነሱ ጉዳዮች በዝርዝር አልቀረበም። ነገር ግን ከሥርጭት ድርጅቱ ዘገባ መረዳት እንደተቻለው በውይይቱ ጠንከር ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ አቋሞች የተገለጹበት መኾኑን ነው።

ከዚሁ ዘገባ ጋር ተያይዞም በሰሞኑ በቤተክርስቲያን ላይ እየደረሱ ካሉ ጥቃቶች በተለይ በዶዶላና አካባቢው እስከ ቅዳሜ ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ጥቃቱና ማስፈራሪያው እንዳልቆመ የሚገልጽ ነበር። በዶዶላና በአካባቢው ሕይወታቸው ያለፉ ቤተሰቦቻቸውን እንኳን ለመቅበር እንዳልቻሉ አመልክቷል። በዕለተ እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች በሃይማኖታቸው ምክንያት በግፍ ለተገደሉ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ፀሎተ ፍትሐት ተከናውኗል። (ኢዛ)

የግብጽና የኢትዮጵያ ፍጥጫ

በኢትዮጵያ የተከሰተው ይህ ከ67 በላይ ሰዎችን ሕይወት እስከማጥፋት የደረሰው ግርግር፤ ሁሉም ዓይንና ጆሮውን ወደዚህ ጉዳይ አደረገ እንጂ ቀዳሚ ዜና ተደርጐ ይወሰድ የነበረው በህዳሴ ግድቡ እሰጥአ ገባ ውስጥ የገቡት ግብጽና ኢትዮጵያ በመሪዎቻቸው ተወክለው ያደረጉት ውይይት ውጥረቱን ማርገብ የሚችል ስለመሆኑ መሰማቱ ነው።

በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና በግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ መካከል በግድቡ ዙሪያ የመከሩት በሩሲያ ሞሥኮ ላይ ነበር። ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋ በኾነው መረጃ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ውይይቱን በተመለከተ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት፤ ግብጽ ወደ ቀድሞው የሦስትዮሽ መድረክ እንደምትመለስ ፕሬዝዳንት ሲሲ አረጋግጠውልኛል ብለዋል።

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እያሻከረ ያለው የግብጽ ሚዲያዎች ዘገባ መሆኑ ተነስቶ፤ በዚህም ጉዳይ ስለመነጋገራቸው በሁለቱ መሪዎች ውይይት ተንተርሶ የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ግብጽ ከዚህ ቀደም ይፋ እንዳደረገችው የሦስትዮሽ የውይይት መድረኩን ለማቋረጥና በሦስተኛ ወገን የሚለውን ሐሳብ እስከማቅረብ ደርሳ የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው መቅረቷ ይታወሳል።

ግብጽ ይህንን ሐሳብ ከማቅረቧ በፊት ግን (ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ግብጽ) የውይይት መድረክ ላይ የህዳሴ ግድብን የተመለከቱ አዲስ አጀንዳ ይዛ በመቅረቧ፤ ውይይቱ በመደነቃቀፉ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ልዩነቶቻቸውን ያሰፋ አመለካከቶች ተንፀባርቀው ነበር። የሰሞኑ የዶ/ር ዐቢይና የአልሲሲ ውይይት ውጥረቱን በማርገብ በተለመደው የሦስትዮሽ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ ለመወያየት ተስማምተዋል። (ኢዛ)

ሕወሓትና የኢሕአዴግ ውሕደት

ሌላው የዚህ ሳምንት መሪ ዜና ሆኖ የሚጠቀሰው በኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ ዳር ይዞ ሲሞግት የነበረው ሕወሓት የቀደመውን ግትር አቋሙን በማርገብ ውሕደቱን አንቀበልም አላልንም በማለት መግለጫ መሥጠቱ ነው።

ይህ መግለጫ የተሰጠው ደግሞ በሕወሓት ሊቀመንበርና በትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ነው። በአንዳንዶች ዘንድ መግለጫው አገም ጠቀም ነው ቢባልም፤ ሌሎች ደግሞ መግለጫው ስለ ውሕደቱ ከቀድሞ በተለየ የተለሳለሰ ሐሳብ የሰጡበት ነው ቢሉም፤ ስለውሕደቱ ቁርጥ ያለ ምላሽ ያልሠጡበት መሆኑን ግን ቁርጥ አድርገው ያላመለከቱም ተደርጐ ተወስዷል።

የዶ/ር ደብረጽዮን መግለጫ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሕወሓት በፓርቲዎች ውሕደት ዙሪያ ኢሕአዴግ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች የተለየ አቋም እንደሌለው የሚገልጽ ነው።

የኢሕአዴግ ጉባዔ በሐዋሳ በተደረገበት ወቅት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች (ኦዴፓ፣ ሕወሓት፣ አዴፓ እና ደኢሕዴግ) የቋንቋ ልዩነት እንጂ የፕሮግራምና የይዘት ልዩነት ስላልነበራቸው አራት ሆኖ ከመቀጠል ይልቅ ውሕድ ፓርቲ እንዲኖር ጥናት እንዲደረግ መወሰኑን ያስታወሱት ዶክተር ደብረጽዮን፤ በሙከራ ደረጃ የተሠሩ ሥራዎች አሉ ብለዋል።

ይህንም “በሙከራ ደረጃ በፌዴራል በሚተዳደሩ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የነበሩ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሥር ያሉ የወጣቶችና ሴቶች ሊጐች በኢሕአዴግ አደረጃጀት ተግባራዊ ሆኗል” በማለትም ያከሉበት መግለጫ ነበር። ይሁን እንጂ ዶ/ር ደብረጽዮን በአሁኑ ወቅት ያለው የአባል ድርጅቶቹ አሰላለፍና ፕሮግራም ሲታይ ግን በሐዋሳ ተላልፎ ከነበረው የኢሕአዴግ ውሳኔ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ፣ የድርጅቶቹ በፕሮግራምና ይዘት መለየታቸውን የሚያሳይ መደምደሚያ መሥጠታቸው ውሕደቱን ይቀበሉታል አይቀበሉትም የሚለውን ጥያቄ አሻሚ አድርጐታል።

ሌላው ለውሕደቱ ዋነኛው ልዩነት የተፈጠረው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መቀጠል አለመቀጠል ላይ ነው የሚልም ተጨማሪ ሐሳብ ያከሉበትን መግለጫ ነበር በዚህ ሳምንት የሰጡት። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ