EZ weekly news digest, week 11, 2012 E.C

ከኅዳር 8 - 14 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ አንደኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከኅዳር 8 - 14 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ሳምንቱ በታሪክም ልናስታውሳቸው የሚችሉ የፖለቲካ ክዋኔዎች የተስተናገደበት ነው። ከእነዚህ ውስጥ ረዥም ዕድሜ ካስቆጠሩት ፓርቲዎችና በሥልጣን ላይ ለ28 ዓመታት የቆየው ኢሕአዴግ በአዲስ ፓርቲ የሚተካ መኾኑን ውሳኔ የተላለፈበት ነው። ብልጽግና የሚለው አዲስ ፓርቲ ሆኖ የዚህች አገር ትልቁ ፓርቲ በመሆን በአዲስ አደረጃጀት እንደሚሠራ ይፋ የተደረገበት ሳምንት ነው።

ለኢሕአዴግ መመሥረት በዋና መሐንዲስነት የሚታወቀው ሕወሓት ደግሞ ከዚህ ውሕደት ውጭ በመሆን ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና አምስቱ አጋር ድርጅቶች አዲስ ፓርቲ በመፍጠሩ ታሪካዊ ሒደት ላይ በመስማማት አወንታዊ አሻራቸውን አሳርፈዋል። ሕወሓት ከዚህ ውሕደት ውጭ የመኾኑ ጉዳይ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው። ሕወሓት ከዚህ ውሕድ ፓርቲ በይፋ ውጥቷል፤ አልወጣም? የሚለው አሁንም ጥርት ባለ መንገድ አለየም። ኾኖም ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና አምስቱ አጋር ድርጅቶች በውሕደቱ ላይ ጥርት ያለ አቋም ሲወስዱ፤ ሕወሓት ውሕደቱን ከዳር እየተቸ ነው። ቀጣዩ እርምጃስ ምን ይኾን? የሚለው ጥያቄም መልስ የሚሻ በመኾን የሳምንቱ አነጋጋሪ አጀንዳ ኾኖ ቀጥሏል።

እንዲህ ካለው ፖለቲካዊ ክስተት ባሻገር በሳምንቱ የተስተናገደው ሌላው ዐበይት ክንውን የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ሕዝበ ውሳኔ የተደረገበት፤ የሕዝበ ውሳኔውም ውጤት የተሰማበት ነው። የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ሲዳማ አስረኛዋ የኢትዮጵያ ክልል መኾንዋን የሚገልጽ ዜና ተደምጧል። ከእነዚህ ዐበይት ክዋኔዎች ሌላ በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የተፈጠረው ያለመረጋጋት በዚህ ሳምንት አንፃራዊ የሆነ ሰላም የታየበት ነበር። ችግሮቹን ለመፍታት ብዙ ጥረት የተደረገበት፣ ብሎም የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ በኋላ የሚከሰት ግጭት ተሳታፊ የኾነን አካል ለሕግ ማቅረብ አማራጭ የሌለው መኾኑን ያሳወቀበት ሳምንት ነበር። ትምህርት ያቋረጡ እንደ ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሒደታቸውን መጀመራቸውም የተገለጸበት ነው። ይህ ማለት ግን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ማለት ሳይሆን፤ የተሻለ መረጋጋት የታየበት፣ ችግር በተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም የማስፈን ሥራዎች በተለያዩ መንገዶች የተሠሩበት በመኾኑ፤ ውጥረቱ እየረገበ መኾኑን እያሳዩ ነው።

የኦሮማራ የምክክር መድረኮች እንዳስተናገዱና በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተውጣጡ አካላት ለሰላም መስፈን ድምፃቸውን አሰምተዋል። ከሰኔ 15ቱ የከፍተኛ መኮንኖችና የአማራ ክልል አመራሮች ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ክስ ተመሥርቶባቸው ፍ/ቤት እንዲቆሙ የኾነውም በዚህ ሳምንት ነው። ከሳምንቱ ክዋኔዎች ትኩረት ከሳቡ ለየት ያሉ ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮጵያ ሳተላይት ልታመጥቅ መኾኑ በይፋ መገለጹ ነው። ቀን የተቆረጠለት ይህ ክንውን በቀጣዩ ወር እውን ይኾናል።

ከቢዝነስንና ክዋኔዎች ውስጥ የሳምንቱ ቀዳሚ ዜና መንግሥት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የግል ባንኮችን በአስገዳጅነት ሲያስፈጽም የነበረው 27 በመቶ የቦንድ ግዥን አስገዳጅ መመሪያ ማንሳቱን ያሳወቀበት የተለየ ሳምንት ሆኗል። (ኢዛ)

ሲዳማ አስረኛዋ ክልል

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የቆየ ነው። ከለውጡ በፊት በነበረው የኢሕአዴግ አመራር ለዚህ ጥያቄ የተሠጠው ምላሽ የክልልነት ጥያቄውን አጉልተው በሚያቀነቅኑ ወገኖች የተመቸ አልነበረም። ጭራሽ ጥያቄውን ያቀረቡ ወገኖች በአደባባይ ሕይወታቸውን ያሳጣም ጭምር ነበር።

በቀደመው አመራር የተወሰደው እርምጃ ክልል እንሁን የሚለውን ጥያቄ አዳፍኖ የቆየ ነበር። በዶክተር ዐቢይ የሚመራው ለውጥ እውን ከሆነ ወዲህ ግን ይህ የክልልነት ጥያቄ እንደ አዲስ ተቀጣጥሎ ወጥቷል። ከለወጡ በኋላ ጎልቶ እንዲወጣ የተደረገው ጥያቄ አጋጣሚውን ለመጠቀም የተደረገ ስለመኾኑ የሚገልጹ ወገኖች አልጠፉም። ጥያቄው አግባብ ቢሆንም ወቅቱ አይደለም የሚል ሙግት ሲደረግበትም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ጉዳይ ላይ ከዞኑ ተወላጆች ጋር በተለያዩ መድረኮች መክረውበታል። ኾኖም ጉዳዩ ኃይል ጭምር የቀላቀለ፤ አሁን ካልሆነ በሚል የተፈጠረው ውጥረት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ደኢሕዴግንም በጉዳዩ ላይ ሳይንሳዊ ጥናት አስጠንቶ በጋራ መኖር የተሻለ ስለመኾኑ ሁሉ የሚያሳይ ትንተና እንዲሰጥበት አድርጓል።

ኤጀቶ በተባለ የወጣቶች ቡድን ክልል እንሁን የሚለውን አቋም በተቃውሞና በተለያዩ መንገዶች እንዲንጸባረቅ በማድረግ፤ በተለይ እንደ ሐዋሳ ያሉ ከተሞች በስጋትና በውጥረት ሲናጡ የነበረበት ተደጋጋሚ ችግሮች ሲፈጠሩም ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ፌዴራል መንግሥት ጥያቄውን በአግባቡ እንደሚስተናገድ ሳይገልጽ ያለፈበት ጊዜ የለም።

የኾነው ኾኖ በዞኑ የክልልነት ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲሠጥ በተወሰነው መሠረት፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይህንን የማስፈፀም ኃላፊነት ተሠጥቶት ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ማከናወን ችሏል። በሕዝበ ውሣኔው ለመሳተፍ 2.3 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበው ኅዳር 10 ቀን ድምፅ መሥጠት ችለዋል። በሰላማዊ መንገድ ምርጫው ተጠናቅቋል። ይህ ታሪካዊ ሒደት የሆነው በዚህ ሳምንት ነው።

ክልል እንሁን የሚለው ድምፅ አሸናፊ ይሆናል የሚለው ግምት የብዙዎች እምነት ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም፤ በሕጉ መሠረት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ይጠበቃልና ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ በኾነው ውጤት የሲዳማ የክልልነት ጥያቄው በምርጫው ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት ውጤቱ ተለይቷል። በዚሁ መሠረት ከ98.51 በመቶ በላይ የሚኾኑት መራጮች ሲዳማ ክልል ይሁን የሚል ድምፅ መሥጠታቸውን የምርጫ ቦርድ ይፋ አደረገ።

ከዚህ ውጤት በኋላ ግን ክልል መኾኑ ዞኑን የበለጠ ይጐዳል የሚለው አመለካከት ያለ ቢሆንም ሲዳማ 10ኛዋ የአገሪቱ ክልል ትሆናለች። እንደ አንድ ክልል ለመንቀሳቀስ የሚያስችለው እውቅና ለማግኘት ደግሞ ከዚህ በኋላ በየደረጃው የሚፈጸሙ ሕጋዊ ሒደቶች የሚቀጥሉ ይኾናል። (ኢዛ)

ብልጽግናና ሕወሓት

የሳምንቱ ብቻ ሳይሆን ከግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ እንደ አንድ ታሪካዊ የፖለቲካ ክስተት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ጉዳይ ደግሞ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ለማዋሐድ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና በአጋርነት ይጠሩ የነበሩ አምስት ድርጅቶች ውሳኔ ያሳረፉበት መኾኑ ነው።

አራት ድርጅቶችን በአንድ ግንባር ሥር አድርጐ አገሪቱን ሲመራ የቆየው ኢሕአዴግ የሚለው መጠሪያ ቀርቶ የብልጽግና ፓርቲ የሚል ስያሜ የያዘ አዲስ ፓርቲ ወደመኾን ሊያሸጋገረው የሚችል ስምምነት የተደረሰበት ነው።

በመጀመሪያ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የውሕደቱን በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁ፣ ሕወሓት አባላት የተቃውሞ ድምፅ ሠጥተዋል። በዚህ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ስምንት የሕወሓት አባላት ነበሩ። የሕወሓት ድምፅ አለመሥጠት ብልጽግና ፓርቲን ከመመሥረት የሚገታ ባለመኾኑ፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ የነበረበት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከሥራ አስፈፃሚው የተመራለትን የውሕደት ጉዳይ በሙሉ ድምፅ አጸደቀ። የአዲሱ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብና ሌሎች የምሥረታ ሒደቱን የሚያጠናክሩ አጀንዳዎችን በማጽደቅ የብልጽግና ፓርቲ እውን ለመኾን የሚያስችሉ ውሳኔዎች ተላለፉ። ይህንን ተከትሎም ኢሕአዴግ መግለጫ አውጥቷል። ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶች ውሕደቱን ሲያጸድቁ ሕወሓት ከዚህ ውጭ ሆኗል። የውሕደቱን ሒደት ውሳኔ የተሠጠበትን አካሔድ በቃወም በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ አባላቱ እንደማይሳተፉም በማስታወቁ ውሣኔዎቹ የተላለፉት በቀሪዎቹ ድርጅቶች አባላቶች ነው።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት የሁለት ቀናት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ይፋዊ መግለጫ ባይሠጥም የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ለድምፂ ወያኔ ቴሌቭዥን የሠጡት መግለጫ ነበር። ይህ መግለጫ በውሕደቱ ላይ ሕወሓት ተሳታፊ ያልሆነበት ምክንያት ውሕደቱን በተመለከተ ቀድሞ ሊመከሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሳይወሰን በቀጥታ ወደ ድምፅ መገባቱ አግባብ ካለመኾኑ ጋር የተያያዘ መኾኑን የሚጠቁም ነው።

አቶ ጌታቸው ሕወሓት በዚህ ውሕደት ላይ ልዩነት ያለው መኾኑንም ያመላከቱ ሲሆን፣ በዚህ ውሕደት ውሣኔዎች ላይ ሕወሓት ያለመሳተፉ ትክክል መኾኑንም አንጸባርቀዋል። ኾኖም ጉዳዩ ያለፈ ጉዳይ ነው የሚል እምነት የሌላቸው መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይ ለድምፂ ወያኔ በሠጡት ቃለምልልስ ውስጥ፤ “ኢሕአዴግ ውሕደት የሚለው ቃል ራሱ ስሕተት ነው” ይላሉ። አያይዘውም ኢሕአዴግ ሊዋሃድ አይችልም። የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ናቸው የሚዋሐዱት በማለት የቃል አጠቃቀሙን የተቹት አቶ ጌታቸው፤ “ኢሕአዴግ ግንባር ነው ራሱን ማክሰም ይችላል። ራሱን አክስሞ አባላቱን ሊዋሃዱ ይችላሉ።” ብለዋል።

ከአዲሱ ፓርቲ ምሥረታ በኋላ የአገሪቱና የትግራይ ክልል ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? የሚል አንደምታ ላለው ጥያቄ የሠጡት ምላሽ “የአዲሱ ፓርቲ ምሥረታ የሚባለው፣ በመጀመሪያ ደረጃ ፓርቲ የአገር ዕጣ ፈንታን እንዲወስን መፈቀድ የለበትም። ፓርቲ የአገር ዕጣ ፈንታ እንዲወስን ሳይሆን አገሪቱን የተሻለ ቦታ ለማድረስ ነው መንቀሳቀስ ያለበት። እኔ አሁን እንደማየው ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በትግራይ ሕዝብ ነው። አሁን ባለን ደረጃ በትግራይ አመራር በያዘው ሕወሓት፣ ትግራይ ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ በሌሎች ጐረቤቶቻችን ወንድሞቻችን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች አገራችንን የማዳን ጉዳይ እንደተጠበቀ ኾኖ፤ ዕጣ ፈንታችን የሚባለው ግን ከአንድ ፓርቲ መክሰም ከአንድ ፓርቲ መቀጠል ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም።

“እንደ አለመታደል ኾኖ ብዙ ጊዜ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ከአንድ ፓርቲ መኖር አለመኖር ጋር ሰፍተን ስላመጣነው ነው ብዙ ጭንቀት እየተፈጠረ ያለው። ስለዚህ ከዚህ ባሻገር (ቢዮንድ) መውጣት የምንችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። አሁን ባለው ሁኔታ ማንነትን የጨፈለቀ ድርጅቶችን በሙሉ አክስሞ ሁሉንም ከአራት ኪሎ የሚመራ አስተዳደር የሚሞከረው እንቅስቃሴ፤ አገሪቱ ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል። ሕወሓት ነገሩን ገምግሞ የወሰነው ውሳኔ እንደተጠበቀ ኾኖ በግላቸው ግን ከአራት ኪሎ ላይ አመራር ለመሥጠት የሚደረግ አካሄድ ችግር ያስከትላል የሚል እመነታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ይህን ይበሉ እንጂ ውሕድ ፓርቲውን ለመፍጠር ሕጋዊ የኾኑ አካሔዶችን ተከትሎ የተፈጸመ መኾኑን የተለያዩ የሕግና የፖለቲካ ሰዎች በተለያዩ ሚዲያዎች አስረድተዋል።

ከሥራ አስፈፃሚውና ከምክር ቤቱ ስብሰባና ውሳኔዎች በኋላ የወጣው መግለጫም፤ አዲሱ ፓርቲ ዋና ዋና ዓላማዎቹንና የፖለቲካ አካሔዱን ያሳየ ነበር። ለዚህም አገራዊ እሳቤው ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደተባበሩት የጠየቀበት ነው። ሕወሓት ግን ውሕደቱን ባይደግፍም ይፋዊ መልስ ስላልሠጠ ከውሕደቱ ውጭ ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ ምላሽ እስካሁን እየተጠበቀ ነው።

አቶ ጌታቸው ቃለምልልስ ላይ ግን አሁን ባለው ሁኔታ የውሕደቱ አካሔድ የትግራይን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም የሚል አንደምታ ያለው ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያቋቋሙትን ድርጅት ዘጠኝ ሰዎች ሔደን እንዲፈርስ ወስነናል ለማለት የሚያስችል ሞራልና ብቃት ከየት ነው ሊመጣ የሚችለው? በማለት ሕወሓትን አክስሞ ውሕደቱን ለመቀበል የማይችል ስለመኾኑ ጠቁመዋል። 

ከዚህም ሌላ ሕወሓት ውሕደቱ አኀዳዊ ሥርዓት ይፈጥራል የሚለው ምልከታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲቀነቀን ቆይቷል። በአንፃሩ ሕወሓት ወደዚህ ውሕደት ላለመግባት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአንዳንድ የክልሉ ነዋሪዎች ሳይቀር እየተተቸው ነው።

ዶ/ር ዐቢይ በበኩላቸው ውሕድ ፓርቲው አኀዳዊ ሥርዓት ለመፍጠርና ጨፍልቆ ለመግዛት ነው የሚለውን እሳቤ ፍጹም የተሳሳተ መኾኑን ኅዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዴፓ 39ኛ ዓመት በዓል ላይ ገልጸዋል።

አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር በመኾኑ ከጨፍላቂነት ይልቅ አቃፊነቱ የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል። ምሁራንንና አርብቶ አደርን ያላካተተ ፓርቲ ጨፍላቂ ሳይባል፤ አካታቹ ጨፍላቂ ሊባል የሚችልበት አመክንዮ አለመኖሩንም ጠቅሰዋል። አያይዘውም የሲዳማን ሕዝብ ራሱን ለማስተዳደር እንዲወስን የፈቀደ ፓርቲ ጨፍላቂ ሊኾን እንማይችልም ገልጸዋል። (ኢዛ)

የሰኔ 15ቱ ግድያ የተመሠረተው ክስ

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን፣ የአገሪቱ ጠቅላይ አታማዥር ሹምና ሌላ ከፍተኛ መኮንኖች ግድያ ጋር ተያይዞ ምርመራ ሲደረግባቸው ከነበሩ ተጠርጣሪዎች ውስጥ 13ቱ ክስ ተመሥርቶባቸው ፍ/ቤት የቀረቡት በዚህ ሳምንት ነው።

በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተፈጸሙት ግድያዎች ጋር በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት ከተጠረጠሩትና ኅዳር 12 ቀን 2012 ፍ/ቤት ከቀረቡት 13ቱ ተከሳሾች የተመሠረተባቸው ክስ ዋነኛ ጭብጥ ሕገመንግሥትን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ነው።

ከ3ቱ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የጀኔራል ሰዓረ ጥበቃ የነበረው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ አንዱ ነው። ከዚህም ሌላ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ይገኙበታል።

በፍ/ቤቱ የመጀመሪያ ቀጠሮ ተከሳሾቹ ለደኅንነታችን እንሠጋለን በማለት ለችሎቱ የገለጹ ሲሆን፣ በምርመራ ወቅት ተወሰደብን ብለው ያሉት ንብረት እንዲመለስላቸው ጥያቄ ስለማቅረባቸው ታውቋል።

ፍ/ቤቱ ተከሳሾቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ እንዲሠጡ ለታህሳስ 1 ቀን 2012 ቀጠሮ ሠጥቷል።

ተከሳሾቹ ለችሎቱ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረትም በማረሚያ ቤት ጥብቅ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ትእዛዝ ተሠጥቷል። በምርመራ ወቅት ተወሰደብን ስላሉት ንብረትም በዝርዝር እንዲቀርብለት አዟል።

በዚህ ችሎት ላይ በቀዳሚነት ከተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የኾነው መቶ አለቃ ጥጋቡ ከችሎቱ የሚቀርብለትን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እንዳልቻለ ተገልጿል። ተጠርጣሪው ምላሹ አዎና እሺ የሚል ብቻ ነበር ተብሏል። በጽሑፍ ሐሳቡን እንዲገልጽ የተሠጠውንም እድል ለመጠቀም እንዳልቻለም ተጠቁሟል።

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በባህር ዳር በተፈጸሙት ሕይወታቸውን ያጡ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል ሜጀር ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ ይገኙበታል። በባህር ዳሩ ጥቃት ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እዘዝ ዋሴ በዋናነት የሚጠቀሱ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። (ኢዛ)

የግል ባንኮችን ሲደቁስ የነበረው መመሪያ መሻር

የሳምንቱ ዐቢይ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ዜና፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በግል ባንኮች ላይ ጭኖ የቆውን የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ መመሪያ ማንሳቱ ነው።

ከ2003 ዓ.ም. ጀምር ሁሉም የአገሪቱ የግል ባንኮች ከሚሠጧቸው እያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ በማስላት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዥ እንዲያውሉ በሚያስገድደው በዚህ መመሪያ መሠረት ከ110 ቢሊዮን ብር በላይ ቦንድ ገዝተዋል።

ይህ መመሪያ የአገሪቱን ባንኮች የማበደር አቅም በመፈታተን ብዙ የጐዳቸው በመኾኑ፤ መመሪያው እንዲሰረዝላቸው በማኅበራቸው በኩል በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩ ቢሆንም ሰሚ ሳያገኙ ቆይተው ነበር።

ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ግን የኢትዮጵያ ብሔራራዊ ባንክ ይህንን መመሪያ ማንሳቱንና ባንኮቹ ላለፉት ሰባት ዓመታት ለቦንድ ግዥ ያዋሉት ገንዘብ ቀደም በነበረው መመሪያ መሠረት በየዓመቱ የሚመለስላቸው መኾኑን አስታውቋል።

ይህ ዜና በግል ባንኮች ዘንድ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክም በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለው ሪፎርም አንድ አካል ተደርጐ የሚወሰድ ነው። በሌላ በኩልም አዲስ አገራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመቅረጽ እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ የዚህ መመሪያ መሻር አስፈላጊ ኾኖ የተደረገ እርምጃ እንደሆነም ተጠቅሷል።

ኾኖም ባንኮቹ በአስገዳጅነት እንዲፈጽሙ ባስገደደው መመሪያ ከ110 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን የቦንድ ግዥ የፈጸሙበትን ገንዘብ በእጃቸው ኖሮ ቢያበድሩት ኖሮ፤ አሁን ባንኮቹ ካሉበት ደረጃ የበለጠ ያጠነክራቸው እንደነበርና ትርፋማነታቸውንም በበለጠ ያሳደጉበት እንደነበር ሲገልጹ ቆይተዋል።

በተለይ ባንኮቹ ከደንበኞቻቸው ለሚሰበስቡት የቁጠባ ገንዘብ ቀደም ብሎ በአምስት በመቶ ከዚያም ሰባት በመቶ እየከፈሉበት ለብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዥ ሲያውሉ የሚታሰብላቸው ወለድ ሦስት በመቶ ብቻ የነበረ በመኾኑ፤ ባንኮችን ችግር ውስጥ ከትቶ እንደነበር የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ብሔራዊ ባንከ መመሪያውን መሻሩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ መረዳት እንደሚችለው ባንኮቹ ቦንድ የገዙበት ገንዘብ የሚመለሰው የቦንድ ግዥው ከተፈጸመ አምስት ዓመት የሞላውን በየዓመቱ በማስላት ነው።

ይህም ከዛሬ አምስት ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ ቦንድ የተገዛበት ገንዘብ ከዘንድሮ ጀምሮ የሚመለስ ሲሆን፣ አምና የተፈጸመ የቦንድ ግዥ ደግሞ ከአምስት ዓመት በኋላ የአንድ ዓመቱ ታስቦ ይመለሳል እንደማለት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

16ቱ ባንኮች ባለፉት ሰባት ዓመታት የገዙት ቦንድ ከ110 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሲሆን፣ አምስት ከመቶ ሞልቶት የተመለሰው ከ25-30 ቢሊዮን ብር ይገመታል። በመኾኑም ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘባቸው በየዓመቱ ተሰልቶ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ባንኮቹ የማበደር አቅማቸውን የሚያሳድግላቸው ሲሆን፣ ኢኮኖሚውንም በማረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 16ቱ የግል ባንኮች ለቦንድ ግዥው ያዋሉት ገንዘብ ከፍተኛ እንደነበር የሚያመላክተው ባንኮቹ በአሁኑ ወቅት ካላቸው ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል ከእጥፍ በላይ መኾኑ ነው።

በጊዜ ሒደትም የማበደሪያ ወለዳቸውን እንዲቀንሱ እድል የሚሠጥ ነው። ይህ መመሪያ መንግሥታዊ የኾኑትን ባንኮች የማይመለከት እንደነበር አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!