Ethiopia Zare weekly news digest, week 13, 2012 Ethiopian calendar

ከኅዳር 22 - 28 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ ሦስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከኅዳር 22 - 28 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ባሳለፍነው ሳምንት ቀዳሚ ፖለቲካዊ ክንውኖች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ከብልጽግና ፓርቲ ራሱን ያራቀው ሕወሓት ፌዴራሊስቶች ናቸው ብሎ ያመነባቸውን የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦችን በማሰባሰብ በመቐለ ለሁለት ቀናት ያካሔደው ጉባዔ አንዱ ነው። በዚህ ጉባዔ ላይ የብልጽግና ፓርቲን የሚቃወሙ የበረከቱ አስተያየቶች የተሰነዘሩበትና የተለያዩ ጽሑፎች የቀረቡበት ሲሆን፣ በዋናነት ግን ከብልጽግና ፓርቲ አኀዳዊ ሥርዓትን ለማስፈን እየሠራ ነው የሚለውን አመለካከት ለማንጸባረቅ የተሞከረበት መድረክ ነው ማለት ይቻላል።

አዲሱ ፓርቲ ብሔር ብሔረሰቦችን ሊጨቁን ነው የሚለው መልእክት ጐልቶ እንዲተላለፍ የተፈለገበት መድረክ እንደነበር የሚጠቅሱም አሉ። በጉባዔው መጨረሻ ላይም የአቋም መግለጫ በማውጣትና አንድ ፎረም ለመመስረት የስበሰባው ተሳታፊዎች ስምምነት በማድረግ ተጠናቅቋል። ሕወሓት እንዲህ ባለ ስብሰባ ሳምንቱን ሲጀመር በአንፃሩ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ እውቅና ይሠጠኝ ብሎ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ ያስገባው በዚህ ሳምንት ነው።

ሕወሓት ፌዴራሊስቶች ነን ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦችን በማደራጀት ብልጽግናን ለመገዳደር ዝግጅት እያደረገ ነው የሚለው ወሬ እየተራገበ ባለበት ሰዓት ደግሞ፤ በአብዛኛው ነፃ አውጪ የሚል ስያሜን ያካተቱ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ስለመስማማታቸውና ይህንንም እወቁልን ያሉት በዚህ ሳምንት ነው። የእነዚህን ፓርቲዎች ጥምረት ወይም በጋራ ለመሥራት የመስማማት ዜና ጆሮ እንዲሠጠው ያደረገው፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ዕድሜ ያላቸው እንደ ኦነግና የኦጋዴን ነፃ አውጭ ብሔራዊ ግንባር ከአሥሩ ተጣማሪዎች ውስጥ መካተታቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ሥር ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ሳምንት በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም ላይ ተከታታይ ውይይት እያደረጉ መኾኑ በሰፊው ሲዘገብ የነበረበት ሳምንት ነው። መደመርንና የኢሕአዴግን ውሕደት እንደማይቀበሉ የገለጹት መከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ ወደ አሜሪካ ማምራታቸው፤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ የመጨረሻ ስምምነት ለማድረግ ዋሽንግተን እንደሚገኙ መነገሩም በሳምንቱ ተጠቃሽ ወሬዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ የመጨረሻ ውጤት ይፋ የሆነውም በዚሁ ሳምንት ነው። የዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሸላሚው አካል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥጠት ይኖርባቸዋል ከተባለው ከጋዜጣዊ መግለጫ ጋር ተያይዞ የተነሳው አነጋጋሪ ጉዳይም የሳምንቱ ተጠቃሸ ወሬ ነው። እንዲህ ካሉ ዋና ዋና የፖለቲካ ክስተቶች ባሻገር ቢዝነስ ነክ ዜናዎች ውስጥ ደግሞ፤ የግል ባንኮች ትርፍ አሁንም እያደገ ስለመኾኑ ባንኮቹ በተከታታይ እያወጧቸው ያሉት መረጃዎች እያመላከቱ መኾኑ ነው። በተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ባንኮች አሁንም በይበልጥ እያተረፉ የመኾናቸው ጉዳይ ማነጋገሩ ባይቀርም፤ በ2011 በጀት ዓመት ከመቼውም ጊዜ የላቀ ትርፍ እያገኙ መኾኑን ሰሞኑን ከሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች መረዳት ተችሏል።

ሌላ አነጋጋሪ ጉዳይ የአደንዛዥ እፅ ዝውውር እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ መኾኑ ነው። በዚህ ሳምንትም ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ኮኬይን የተባለው አደንዛዥ እፅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ መያዙ ከሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ የሚካተት ነው።

የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ኢንተርኔት አገልግሎት ለደቂቃዎች እንዲቋረጥ የኾነውም በዚሁ ሳምንት ሲሆን፤ ጥቃቱን የተመለከተ ተጨማሪ መረጃም ተሠጥቷል። እንዲህ ካሉት ሳምንታዊ ክዋኔዎች በተወሰኑት ላይ የተጠናከረው ዘገባ እንደሚከተለው ይቀርባል።

የመቐለው ስብሰባና አንደምታዎቹ

ከሰሞኑ እንደዋነኛ ዜና ተደርጐ ሲናፈስ የነበረው ዜና በሰሜናዊቷ ኢትዮጵያ መቐለ ከተማ የተካሔደው አንድ ስብሰባ ነው። የስብሰባው አዘጋጅና አስተባባሪ ሕወሓት ነው። በስብሰባው የተሳተፉ ደግሞ የፌዴራል ሥርዓትን ያቀነቅናሉ የተባሉ ወይም ስም የተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ናቸው። “ሕገ መንግሥቱንና ፌዴራል ሥርዓቱን እናድን” የሚል ጥቅል መልእክት ኖሮት በተሰናዳው በዚህ የመቐለ ስብሰባው ላይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ የተላለፈላቸው ቢሆንም፤ በስብሰባው ላይ መሳተፍ የቻሉት የተወሰኑ ናቸው። በአብዛኛውም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ይሄ ነው የሚባል ሚና የሌላቸው ናቸው የሚባሉ ፓርቲዎች ስለመኾናቸው የሚገልጹም አሉ። ስብሰባው የተከፈተው በሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ነው።

ንግግራቸው ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መሆንዋን በሚገልጹ ቃላቶች የታጨቁም ነበሩ። ስብሰባው ከተከፈተ በኋላ ወቅታዊው የአሪገቱ የፖለቲካ ጉዳዮች የተመለከቱ ጽሑፎችና ውይይቶች ተደርገዋል። የስብሰባው ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች የተለያዩ የአስተያየቶች የሠጡበትም መድረክ ነበር።

በመድረኩ ጐልቶ እንዲታይ የተፈለገውም የብልጽግና ፓርቲና የነዶክተር ዐቢይ አሕመድ አዲሱ አካሔድ ብሔር ብሔረሰቦችን ለመጨፍለቅ የተነሣ መኾኑን፣ አኀዳዊ ሥርዓትን ለመዘርጋት ታስቦ እየተሠራ ስለመኾኑ የሚገልጽም ነው። እንዲያውም አንድ ተሳታፊ የብልጽግና ፓርቲ የምኒልክን አገዛዝ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው በማለት በስሜታዊነት ሲናገሩ የተሰማበት ነው። “ምኒልክ ልብሱን ቀይሮ መጥቷል” በማለት እስከመግለጽ የደረሱበት ነው።

በሕወሓት መሪነት በተካሔደው የዚህ ስብሰባ ሒደት ግን የሚዲያዎችን ትኩረት ያላገኘ ነበር ማለት ይቻላል። ከትግራይ ሚዲያዎች ሌላ ሌሎች ሚዲያዎች ለጉባዔው የሠጡት ሽፋን የታሰበውን ያህል ያለኾሆኑ ሲገለጽም ነበር።

በመቐለው ስብሰባ ዘገባ የሠሩም ቢኾኑ እንደ ትግራይ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ያለመሥጠታቸውም ወሬው በተቀነጫጨበ መንገድ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ብቻ እንዲወሰን አድርጓል። መንግሥትም ቢሆን በመቐለው ስብሰባ ላይ አስተያየት አልሠጠም። ከዚያ ይልቅ በዚህ ስበሰባ ዙሪያ የተሠጡ አስተያየቶች ጐልተው ታይተዋል። የተለያዩ ሚዲያዎች የፖለቲካ ሰዎችን በመጋበዝ ውይይት አድርገውበታል። ከዚህ ውስጥ ዋልታ ቴሌቪዥን የትግራይ ዴሞክራቲክ ትብብር ፓርቲ አመራሮችን በመጋበዝ ያደረገው ውይይት አንዱ ነው። በመቐለው ስብሰባ እንዲሁም በአጠቃላይ በሕወሓት አካሔድ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በአብዛኛው ከመቐለ ስብሰባው ጋር የተገናኘ በመኾኑ ትኩረት ሊስብ ችሏል።

የትግራይ ዴሞክራቲክ ትብብር ፓርቲ አመራሮች፤ ሕወሓት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ወደ መቐለ ጠርቶ ያካሔደው ስብሰባ የሕወሓት አካሔድ አሁንም ለመታረም ያልፈቀደ ስለመኾኑ የሚያመላክት ነው ብለውታል። አካሔዱ የትግራይን ሕዝብ በሰበብ በአስባቡ ለመነጠል በማሰብ፤ የሕወሓት አመራሮች ዕድሜያቸውን ለማራዘም የተጠቀሙበት መድረክ ነውም ብለውታል። በተለያዩ ሰበቦች የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል የሚደረግ ሙከራ ስለመኾኑም አስረድተዋል። ነገር ግን በምንም መልኩ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻልና የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር በመኾኑ፤ በሕወሓት በኩል የሚደረጉ አፍራሽ አካሔዶች የማይሳካለት መኾኑንም ጠቅሰዋል። ይህም የሚያሳየው ሕወሓት ግራ መጋባት ውስጥ መኾኑን ነው ይላሉ። ሕዝብ ሕዝብ ነውና አንድ ቀን መነሳቱ የትግራይን ሕዝብ የሚገነጥል ሳይሆን የማያገል አሠራር እየሠሩ ነው።

የሕወሓት አካሔድ ግራ መጋባቱን ያመለክታል ያሉት እኒሁ የፓርቲ አመራሮች እንደ ምሳሌ የጠቀሱት፣ ሕወሓት በአንድ በኩል ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርስና ሕገ መንግሥቱን መጠበቅ አለብን በማለት እየተናገረ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ዲፋክቶ ስቴት” እንመሠርታለን በማለት እያስተጋቡ ያሉት ነገር ግራ መጋባቱን ያሳያል በማለት ይገልጻሉ።

ዲፋክቶ ስቴት እንመሠርታለን የሚለውን ፍላጐታቸውን በሕወሓት ልሳን ላይ እያንጸባረቁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አገር እናድናለን የሚሉት ነገር ፈጽሞ የማይጣጣሙ መኾናቸውን የትግራይ ዴሞክራቲክ ትብብር ፓርቲ አመራሮች ሰፊ ማብራሪያ ሠጥተዋል። በመቐለው ስብሰባ ላይ ተገኙ የተባሉት የግለሰብ ፓርቲዎች አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚቀበሉ አለመኾናቸውንም በማስታወስ፤ ሕወሓት ደግሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኝ ነው። ከዚህ አንጻር የተስማማ ነገር የሌላቸው አካላት ናቸው ብለዋል።

ስለዚህ ሕወሓት የመጨረሻ ሙከራ እያደረገ ስለመኾኑ የሚያሳይ ስብሰባ ነው ብለዋል። “ፌዴራሊስት ናቸው የተባሉትን ሰዎች መቐለ ያሰባሰቡት እኛም ደጋፊ አለን ለማለትና የትግራይ ሕዝብን ለማደናገር የተደረገ ሙከራ ነው” በማለት የትግራይ ዴሞክራቲክ ትብብር ፓርቲ አመራሮች አመለካከታቸውን አንጸባርቀዋል።

መቐለ “ሕገ መንግሥትንና ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለማዳን” በሚል በተካሔደው ስብሰባ መጨረሻ ላይ ግን፤ ተሳታፊዎች የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው አይዘነጋም። ከመግለጫው መረዳት እንደሚቻለው በቀደሙት ዓመታት ሕገ መንግሥታዊነትንና ሕብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ሥርዓትን ቀስ በቀስ እግር እየተከሉ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ረገድ ብዙ ለውጦች የተመዘገቡበት እንደነበር በማስታወስ ይጀምራል። ሆኖም በመንግሥት ውስጥ እየገነነ በመጣው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የፀረ ዴሞክራሲ አሠራርና የመልካም አስተዳደር ችግር የተጀመረውን መልካም ሥራ በተለይም ሕገ መንግሥቱንና ሕብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ሥርዓቱን ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ መኾኑንም መግለጫው ይጠቅሳል። ኢሕአዴግ በሕብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ሥርዓት እንዲመራት በአደራ የተቀበላት አገርና የተሠጠውን የፖለቲካ ሥልጣን መንገድ ስቶ አገሪቷን ወደ መበታተን እያመራች መኾኑን የሚገልጸው ይኸው መግለጫ፤ አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብቶችና ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው አደጋ ላይ ስለመውደቁ የሚያትትም ነው።

የሕግ የበላይነት፣ ሰላምና የዜጎች ደኅንነት የማይከበርበት፣ የዜጎች መሠረታዊ ጥያቄዎች በማዳፈን ሥልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች ያለ ገደብ ያሻቸውን እያደረጉ ስለመኾኑ፤ እነዚሁ በሥልጣን ላይ ያሉት ኃይሎች ሕግ የማይገዛቸው በሚመስል መልኩ የሚጓዙበት፣ የተጀመሩ መልካም ውጤቶች ወደኋላ የተመለሱበት ሁኔታዎች ስለመፈጠራቸው ይገልጻል። ይህንን ሁኔታ መግለጫው አገሪቷ በጣም አስጊ በኾነ መንገድ እየተጓዘች ነው ብሏል። ይህ ስጋት ባለንበት ሁኔታ ኢሕአዴግ እንዲህ ያሉ ተጨባጭና አንገብጋቢ አገራዊ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ በለውጥና ሌሎች አማላይ ቃላት እየተንቆለጳጰሰ በውሕደት ስም ወደ ቀደሙት ሥርዓቶች ለመመለስ ጫፍ ላይ ደርሷል በማለት ውሕደቱን ይኮንናል። አያይዞም ሚዲያዎችን የሚኮንን አንቀጽ ያካተተው የመቐለው መግለጫ ይህንንም፤ “የመንግሥትም የግልም ሚዲያዎች አገርን የማዳን ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ፤ ሐቆችን በማዳፈንና ችግሮችን በማባባስ ተጠምደዋል” በማለት ሚዲያዎችን ነቅፏል።

የመቐለው ተሳታፊዎች አንድ መደምደሚያ ላይ ስለመድረሳቸው በመግለጽ፤ ሊወሰዱ ይገባቸዋል ያላቸውን እርምጃዎች በዝርዝር ገልጿል። “እኛ የመድረኩ ተሳታፊዎች ባካሔድነው ሰፊ ውይይት በሕገ መንግሥታችንና በሕብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ሥርዓታችን የተደቀነው አደጋ በብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የጋራ ትግል ካልተገታ አገርን ወደ መበተታተን፣ ሕዝቦችን ወደ የእርስ በርስ እልቂት ሊያስገባን እንደሚችል መደምደሚያ ላይ ደርሰናል።” በሚል ሰፍሯል።

“በመቐለው ስብሰባ የተሳተፉ የፌደራሊዝም ኃይሎች በተጨባጭ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የቀረቡት ጥናታዊ መነሻ ጽሑፎች አድምጠን ባደረግነው ሰፊ ውይይትና ተሳትፎ የጋራ መግባት ላይ ደርሰናል” የሚለው መግለጫ፤ በዚሁም መሠረት ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ብሎ ያመነባቸውን አምስት ነጥቦች ዘርዝሮ ጠቅሷል። ከእነዚህም ውስጥ፤ ፀረ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምና አኀዳዊ ኃይሎች ባለ በሌለ አቅማቸው በሕገ መንግሥታችንና ሕብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ሥርዓታችን የከፈቱት ጥቃት ለመመከት የሚያስችለን ሕብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ኃይሎች ፎረም በመፍጠር የሚል አንዱ ነው።

በዚህ አገርን የማዳን መድረክ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ወደ ተግባር ለመግባት ሕብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ኃይሎች የምናደርገው እንቅስቃሴና ትግል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ያልቆጠበ ድጋፍና ላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን ብሏል። ቀጣዩ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ ይካሔድ የሚል አቋም እንዳለው በዚሁ መግለጫው ላይ አንጸባርቋል።

ሕብረብሔራዊ ፌደራሊዝም ሥርዓቱን ከአደጋ መታደግ ኢትዮጵያን እንደ አገር የማስቀጠል በመኾኑ፤ ሁሉም መንግሥታዊና የግል መገናኛ ብዙኀን፣ የፍትሕና የጸጥታ ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች፣ እንዲሁም መላ ኢትዮጵያውያን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚሉም ሐሳብ ይዟል። ይህ የመቐለው ስብሰባ የወጣው የአቋም መግለጫ ግን አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ያልተገናዘበ መኾኑን እንደ ትግራይ ዴሞክራቲክ ትብብር ፓርቲ ያሉ ኃይሎች የገለጸ ሲሆን፤ በተለይ አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ አኀዳዊ ሥርዓት ሊመሠርትና ብሔር ብሔረሰቦችን ሊጨፈልቅ ነው በሚለው ትርክት ላይ ሕወሓትና የመቐለ ተሳታፊዎች የሚያሰሙት ጩኸት መኾኑን ተገልጿል። ብልጽግና ይህ አመለካከት የሌለው መኾኑን ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በብልጽግና ፓርቲ ይዘት ላይ ተደጋጋሚ ማብራሪያዎች የተሠጡ ቢሆንም፤ የመቐለ ተሰብሳቢዎች ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ይዘዋል። ይህ የት ድረስ እንደሚያስኬድ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፤ በቅርቡ ይካሔዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የሕወሓት ጉባዔ በኋላ ብዙ አገሮች ነጥረው ሊወጡ ይችላሉ የሚለው ግን የብዙዎች ግምት ነው።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ከኦቢኤን ጋር ቃለምልልስ ያደጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው አስተያየት ሰንዝረዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሕወሓት ይዞ የቆየው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የኢትዮጵያን ችግር ሊፈታ ቀርቶ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይዞ እየተገዘተና እየማለ ባለበት ክልል ውስጥ ያለውን ችግር አይፈታም ብለዋል። ይህንንም የብልጽግና ፓርቲ የፈጠሩት ፓርቲዎች የሚስማሙበት እንደኾነም አመላክተዋል። ነገር ግን ሕወሓት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከቱን ይዞ መቀጠል የሚችል መኾኑንና ይህም መብቱ መኾኑን በማስታወስ ያመነበትን ይዞ መቀጠል እንደሚችልም ተናግረዋል።

“ያመነበትን ይዞ መቀጠሉ ስሕተት የለበትም። ሕወሓት ያመነበትን ይዞ ሲቀጥል፤ ሌላው ደግሞ ያመነበትን ይዞ እንዲቀጥል፣ ላለመስማማት መስማማት ነው” ማለት ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ተከቧል በሚለው ትርክት ላይ አቶ ገዱ ሰፊ ማብራሪያ የሠጡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ “የትግራይ ሕዝብ ሠርቶ ጥሮ በራሱ ላብ የሚኖር፣ አገሩን የሚወድ ነው። ይሄ ብዥታ መኖር የለበትም። ከሌላው ሕዝብ ጋር ጥላቻ የለውም። እንደ አለመታደል ሆኖ ይህንን ሕዝብ ሰፊ ተጐራባቹን ‘አማራ መጣብህ’ ብሎ ለማስፈራሪያነት ይጠቀምበታል” የሚለው ይጠቀሳል። አያይዘውም የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ቁጥር አንድ ወዳጅ ነው። የትግራይ ሕዝብ ለአማራ ሕዝብ ቁጥር አንድ ወዳጁ ነው። ነገር ግን ቁጥር አንድ የሆነውን የአማራ ሕዝብ ሕወሓት ቁጥር አንድ ጠላት አድርጐ የሚመለከትበት ሁኔታ አለ። ይህ እንዳለመታደል የሆነ ነው የሚሉት አቶ ገዱ፤ በተለይ ከአማራ ሕዝብ ጋር በብዙ የተቆራኘ ነው ብለዋል።

በሁሉም ነገር የትግራይና የአማራ ሕዝብ በቅርብ የተሳሰሩ መሆናቸውንም በማስታወስ፤ የአማራ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ሲነካ አይወድም፤ የትግራይ ሕዝብ የአማራ ሕዝብ ሲነካ አይወድም። ነገር ግን ሕወሓት እየመጣብህ ነው በማለት በማስፈራሪያነት የተጠቀመበት መኾኑን በመግለጽ፤ ይህ ሁኔታ ግን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይሄ ረዥም ጊዜ ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

አሁን በሕወሓት የሚታየው አካሔድ ጊዜ ሊፈታው የሚችል ስለመኾኑ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ ሲሔዱም፤ ሁኔታዎች ይስተካከላሉ ብለው እንደሚያምኑም በዚሁ ቃለምልልሳቸው ላይ ገልጸዋል። በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነውና ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራ የኖረውን የትግራይ ሕዝብ ሊጠሩህ ነው ሊመጡብህ ነው በሚል ትርክት እያስፈራራና ሕዝቡን እንደመያዣ አድርጐ መቆየት እንደማይችል በመጠቆም፤ ይህ ነገር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ይፈታል የሚል እምነትም አላቸው።

ችግሩ የትግራይ ሕዝብ አለመኾኑን ለማጉላትም፤ የትግራይ ሕዝብ አገር ወዳድና ከሌሎች አብሮ መኖር የሚፈልግ ነው። ሕወሓት ደግሞ እያዘዘና እያናዘዘ በመኖር የበላይ መኾን እንደሚፈልግ ገልጸዋል። የትግራይ ሕዝብና የሕወሓት ፍላጐቶች የተለያዩ ናቸውም ብለዋል። በተለይም “ኢትዮጵያ ሙሉ የምትሆነው ትግራይን ስታካትት ነው። ትግራይን አርቆ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሚመኝ የለም” ብለዋል። (ኢዛ)

በተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ የሞቀው የባንኮች ትርፍ

የአገሪቱ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካለፈው ወር ጀምሮ የ2011 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን የሚያመለክቱ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው። በተለይ የአገሪቱ 16ቱ የግል ባንኮች በተከታታይ እያቀረቡዋቸው ያሉ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በአትራፊነታቸው እንደቀጠሉ ነው።

በአገር ደረጃ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተደክሟል በሚባልበት በዚህ ወቅት፤ የአገሪቱ ባንኮች ግን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ትርፋቸው እያደገ መምጣት የፋይናንስ ዘርፉን በተለየ እንዲታይ አድርጐታል።

ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች እንቅስቃሴያቸው ከመቀዝቀዝ አልፎ የትርፍ መጠናቸው ስለመቀነሱ እየተነገረ ባለበት ሰዓት፤ የባንኮች ትርፍ አሁንም እየጨመረ መሔዱ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሠጡበት ቢሆንም፤ በአገር ደረጃ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መቀዝቀዝ ግን እነሱን እንዴት ሊዳብስ አልቻለም የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ከኾነ ሰነባብቷል። ከሰሞኑ ካቀረቡዋቸው የ2011 ዓ.ም. በጀት ዓመት ሪፖርታቸው ላይ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበረባቸው ሳያመለክቱ አላለፉም። እነዚህ ተግዳሮቶች ባይኖሩ ዘርፉ አሁን እየተጠቀሰ ካለው በላይ ውጤት ያስመዘግብ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበረው አለመረጋጋት፣ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ መቀጠልና የመሳሰሉት ችግሮች ባይኖሩ አፈጻጸማቸው አሁን ከደረሱበት በላይ ውጤት የሚገኝበት ስለመኾኑም ይገልጻሉ።

በአንጻሩ ግን የባንኮች ከዓመት ዓመት ትርፋቸው እየተመነደገ፤ አሁንም ኢኮኖሚው በተቀዛቀዘበት ወቅት የትርፍ እድገታቸው የመቀጠሉ አንዱ ምክንያት፤ ባንኮች የብድር ወለድ መጠናቸው ከፍ ከማለቱ ጋር የሚያያዝ መኾኑን አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲጠቅሱም ይሰማል። በዚህ ረገድ የሚሠጡ አስተያየቶች የተለያዩ ቢሆኑም፤ መሬት ላይ ያለው እውነት የሚያሳየው ግን የኢትዮጵያ ባንኮች ከዓመት ዓመት የትርፍ መጠናቸውን እያሳደጉ ከመሔድ የገታቸው ያለመኾኑን ከሰሞኑ እያቀረቡት ያለው የሒሳብ ሪፖርታቸው ቁልጭ አድርጐ እያሳየ ነው።

“የኢትዮጵየ ዛሬ” ድረገጽ ጥቅል ቅኝትም የኢትዮጵያ ባንክች ከሌሎች ቢዝነሶች በተለየ ከማትረፋቸውም በላይ፤ የየባንኮቹ ባለአክሲዮኖችም የትርፍ ድርሻቸው እንዲል ያስቻለ መኾኑ ነው።

ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ኦዲት በማስደረግና የ2011 የበጀት ዓመት ክንውናቸውን ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ያሳወቁ የግል ባንኮች ስድስት ባንኮች ናቸው።

ከስድስት ባንኮች ሪፖርት መገንዘብ እንደሚቻለው አዋሽ ባንክ ከግብር በፊት 3.4 ቢሊዮን ብር ማትረፉን ነው። በባንኩ ሪፖርት መሠረት በ2011 ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ በ2010 አግኝቶ ከነበረው ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ነው።

አዋሽ ባንክ በ2011 ያገኘው ዓመታዊ ትርፍ በአገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ሆኖ ተመዝግቧል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በሪፖርታቸው የጠቀሱትም እስካሁን በዚህን ያህል ደረጃ ያተረፈ የግል ባንክ ያለመኖሩን ነው። ከአዋሽ ባንክ 2011 ዓ.ም. በሌሎች አፈጻጸሞቹም ከሌሎች ባንኮች ከፍ ያለ ውጤት እንዳገኘ ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል። በተለይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ ያለና እስካሁን በአንድ የግል ባንክ ያልተመዘገበ ነው ተብሏል። ባንክ በ2011 ዓ.ም. ከ980 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አግኝቷል። እስካሁን ከግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ አንጻር አንድም ባንክ በአንድ ዓመት ይህንን ያህል የውል ምንዛሪ ያገኘ የለም። በአሁኑ ወቅት ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ንግድ ባንክ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የዘለለ ሲሆን፣ ከግል ባንኮች ግን አዋሽ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዟል። አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የሀብት መጠኑ 74.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ከአዋሽ ሌላ ዓመታዊ ሪፖርቱን ያቀረበው አቢሲንያ ባንክ ነው። አቢሲንያ ባንክ በ2011 በጀት ዓመት ከግብር በፊት 1.02 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል። አቢሲንያ ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ የቻለበት ዘመን ሆኖለታል። ከ20 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ባንክ ከ2011 ያገኘው ትርፍ ከፍተኛ የሚባል ነው። ከአቢሲኒያ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው በ2011 በጀት ዓመት ያገኘው ትርፍ ከ2010 ጋር ሲነፃፀር የ258 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው። ባንኩ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሀብቱ መጠን ደግሞ 39.4 ቢሊዮን የደረሰ መኾኑ ታውቋል።

በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ ያለው ሕብረት ባንክም ከታክስ በፊት 928 ሚሊዮን ብር በማትረፍ 2011 በጀት ዓመትን ማጠናቀቁን አስታውቋል። ሕብረት ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ከ2010 አንጻር ሲታይ የ2011 ትርፉ ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መኾኑን የባንኩ ሪፖርት አሳይቷል።

የሕብረት ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠንም ከ35.74 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። ከአገሪቱ ባንኮች በተለየ ሴቶችን መሠረት በማድረግ የተመሠረተውና የሰባት ዓመታት ዕድሜ ያለው እናት ባንክ፤ በ2011 በጀት ዓመት ከግብር በፊት 232 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አሳውቋል። የትርፉ እድገትም 18 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የገለጸው ባለፈው ሳምንት ነው። ከ64 በመቶ በላይ ሴቶች ባለአክሲዮኖች የኾኑበት እናት ባንክ፤ ከ17 ሺሕ በላይ ባለአከሲዮኖችን የያዘም ነው። አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተጠቅሷል።

እናት ባንክ በተመሠረተበት አካባቢ የተመሠረተው ሌላው ባንክ አዲስ ኢንተርናሽናል ነው። አዲስ ኢንተርናሽናል በ2011 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 205.1 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ባንክ ነው። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ከ2010 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ57.1 ሚሊዮን ብር በላይ መኾኑን ከዓመታዊ ሪፖርቱ መረዳት ተችሏል። የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ ከተቀላቀለ 20 ዓመታትን ያስቆጠረው ንብ ኢንተርሽናል ባንክም 2011 በጀት ዓመትን ከቀደሙ ዓመታት የበለጠ ትርፍ ያስመዘገበበት ዓመት መኾኑን አሳውቋል።

ከባንኩ ሪፖርት መረዳት የሚቻለው ባንኩ ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ 928 ሚሊዮን ብር ነው። ይህ ትርፍ ከ2010 በጀት ዓመት ካገኘው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ270 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው። በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ ተብሎ የተመዘገበ ትርፍ ነው።

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠንም 33.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ለማወቅ ተችሏል። ሌሎች የግል ባንኮችም በዚህ አንድ ወር ውስጥ ሪፖርታቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃሉ።

እስካሁን ሪፖርታቸውን ያቀረቡት ስድስቱ ባንኮች በጥቅል ከታክስ በፊት 6.76 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፤ እነዚህ ስድስቱ ባንኮች በጥቅል ዓመታዊ ትርፋቸውን በ2.7 ቢሊዮን ብር እንደጨመሩ ያሳየ ነው። ቀሪዎቹ አሥሩ የግል ባንኮችስ? የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ በሚቀጥሉት ሳምንታት አፈጻጸማቸው በተከታታይ ይዞ ይቀርባል። (ኢዛ)

አደንዛዥ እፅና ኮንትሮባንድ

በኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎችና የኮንትሮባንድ ንግድ ኢኮኖማውን እየተፈታተኑ ስለመኾኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። በተለይ መንግሥት የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠሩ ረገድ ውጤት እያገኘሁ ነው ቢልም፤ በዚያው አንጻር ሾልከው የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች አሁንም በየቦታው ይታያሉ።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በግብረ ኃይል ደረጃ በመንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች እንደሚያመለክቱት የኮንትሮባንድ ዝውውር ከፍ ማለቱን ነው።

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ዓመት (አራት ወሮች) የተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መጠንም ይህንኑ የሚያሳይ ነው። በሚኒስቴሩ መረጃ መሠረት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ግምታቸው ከ786 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘዋል።

ከዚህ ሪፖርት በኋላም በተከታታይ በሚሊዮን ብሮች የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ለማወቅ ተችሏል። በኮንትሮባንድ መልክ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከሚያዙት ውስጥ መድሃኒት፣ የጦር መሣሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የተለያዩ አገር ገንዘቦች፣ ልባሽ ጨርቆች፣ ምግብ ነክ ምርቶች ይገኙበታል።

እንዲህ ካሉትና ቀድሞም ከሚታወቁ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሌላ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል ተብሎ የሚታመነው የአደንዛዥ እፅ ዝውውር ነው።

በዚህ ሳምንትም በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ከተያዙ ምርቶች ውስጥ አንዱ ይኸው አደንዛዥ እፅ ነው። ይህም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ አደንዛዥ እፅ መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ግምታቸው 28.38 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የአደንዛዥ እፅ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ይህንን ያህል ግምት ያለው አደንዛዥ እፅ የተያዘው ኅዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መኾኑን አሳውቋል። በዕለቱ የተያዘውን አደንዛዥ እፅ ሲያዘዋውሩ የተያዙት ሁለት የውጭ አገር ዜጐች ሲሆኑ፤ የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያላት ሴት ላይ 7.4 ኪሎ ግራም፣ የአዘርባጃን ዜግነት ያላት ሌላ ሴት እጅ ላይ ደግሞ 4 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እፅ ሊያዝ ችሏል።

በአጠቃላይ በቦሌ ኤርፖርት የተያዘው የአደንዛዥ እፅ 11.4 ኪሎ ግራም ነው። ይህ በዚህ ሳምንት የተያዘ ሲሆን፣ ከዚህም ቀደም እንዲህ ያሉ ተደጋጋሚ ዜናዎች ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተሰምቷል። ነገር ግን የአደንዛዥ እፅ የመያዝ ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቀደመው ጊዜ ከፍ ባለ ሁኔታ መሰማቱ ሁኔታውን አሳሳቢ ቢያደርገውም፤ በአንጻሩ ደግሞ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው የሚለውን የሚያመለክት ሆኗል።

በዚህ ሳምንት ከተያዘው የአደንዛዥ እፅ ቀደም ብሎ ኅዳር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በዚሁ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ ውስጥ 12.06 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ኮኬይን የተባለው አደንዛዥ እፅ ተይዟል። በአንድ አሜሪካዊ የተያዘው እፅ መጠኑ 5.2 ኪሎ ግራም እንደነበር መገለጹ አይዘነጋም። በተመሳሳይ ኅዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በጉምሩክ የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ ክትትልና ከብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች በጋራ በመሆን 47.4 ኪሎ ግራም ኮኬይን ተይዟል። አምስት የውጭ ዜጐች በዕለቱ በተለያዩ ሰዓታት በአንድ ቀን የተያዘው ይህ 47.4 ኪሎ ግራም የአደንዛዥ እፅ ጠቅላላ ግምቱ ከ109 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል። (ይህንን አስመልክቶ በዕለቱ በኢትዮጵያ ዛሬ የተዘገበውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

ይህም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሦስት ቀናቶች በቦሌ ብቻ ወደ 150 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አደንዛዥ እፆች መያዛቸውን የሚያሳይ ነው። ይህ አኀዝ በአነስተኛ ደረጃ ሊዘዋወሩ የሚችሉን የማይጨምር በመኾኑ፤ የጉዳዩን አሳሳቢነት አመላካች ነው። (ኢዛ)

የአሥሩ ፓርቲዎች ውሕደት

ከሳምንቱ ዐበይት ፖለቲካዊ ጉዳይ ኾኖ የሚጠቀሰው የአሥር የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ማሳወቃቸው ነው። ከአሥሩ ፓርቲዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ዕድሜ ያላቸው እንደ ኦነግና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የተካተቱበት መኾኑ ታውቋል።

በኦነግ አስተባባሪነት የተፈጠረው የእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሔደው እንቅስቃሴያቸው በጋራ ለመሥራት እንደኾነ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ ከአሥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ስምምነቱ ተፈረመ በተባለበት ወቅት ፊርማቸውን በዕለቱ ያኖሩት ሰባቱ ብቻ መኾናቸው ታውቋል።

ኅዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የተፈረሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው ይገለጽ እንጂ፤ በዝርዝር የሚሠሩት ሥራ አልተገለጸም።

በአብዛኛው በነፃ አውጨነት ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ፓርቲዎችን በያዘው በዚህ ስብስብ ውስጥ ከኦነግና ከኦብነግ ሌላ ስምምነቱን የፈረሙት ቀሪዎቹ ስምንት ፓርቲዎች የአፋር ሕዝቦች ነፃነት ፓርቲ፣ የሲዳማ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአገው አገር አቀፍ ሸንጐ፣ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ናቸው። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ፓርቲዎቹ ስምምነት አድርገዋል ከተባለ በኋላ፤ የአገው አገር አቀፍ ሸንጐ ከስብሰባው መውጣቱ እየተነገረ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንዲህ ባለው ደረጃ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በጥምረት የሚፈጠሩ ፓርቲዎች ቁጥር ከፍ ብሎ በአሁኑ ወቅት ቅጥ ባጣ ደረጃ ከ110 በላይ ደርሰዋል የተባሉ ፓርቲዎች ቁጥር እንዲቀንስ ይረዳል የሚል እምነት አሳድሯል።

በኦነግ መሪነት የተሰባሰቡ ናቸው የተባሉት ከእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ አራቱ ፓርቲዎች ከዚህም ቀደም አልያንስ (ጥምረት) ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይነገራል። እነዚህም የኦነግ፣ የጋምቤላ ነፃ አውጭና የሲዳማ ንቅናቄ ፓርቲዎች ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ውጭ በነበሩበት ሰዓት በመደጋገፍ ሲሠሩ እንደነበር ይነገራል። አሁን ተጨማሪ ፓርቲዎች በማከል ሕብረት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው። (ኢዛ)

ለሃያ ደቂቃ የተቋረጠው ኢንተርኔት የሳይበር ጥቃት

በፋይናንስ ተቋማት ሊደርስ የነበረ ጥቃትን ለማክሸፍ ሲባል የአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ለ20 ደቂቃዎች አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር አይዘነጋም።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ኅዳር 25 ቀን ማምሻውን እንዳስታወቀው በፋይናንስ ተቋማት ላይ ሊደርስ የነበረ ጥቃት ማክሸፍ ችሏል። ይህ መረጃ ጥቃቱ ሊደርስ የነበረው በየትኞቹ ይፋይናንስ ተቋማት ላይ እንደነበር ባይገልጽም በመላ አገሪቱ ለ20 ደቂቃዎች የኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ሆኗል።

ጥቃቱ በከሸፈበት ወቅት ከተሠጠው መግለጫ በኋላ በተሠጠ ተጨማሪ መግለጫ፤ ጥቃቱ ሊፈጸም የነበረው የሳይበር ጥቃት ከ200 በላይ ብዛት ባላቸው የጥቃት አድራሽ ሲስተሞች መነሻ ያደረገ እንደሆነ ኤጀንሲው ገልጿል።

የፋይናንስ ተቋማትን ዒላማ ያደገው የሳየበር ጥቃት ለመቀነስ ሁሉን አቀፍ የሳይበር ደኅነነት ማስጠበቂያ አማራጮችን መተግበር ቀዳሚ እርምጃ መኾን እንዳለበትም ኤጀንሲው አሳስቧል። (ኢዛ)

የዓለም ሰላም የኖቤል ሽልማት

ሌላው በሳምንቱ ጆሮ ከተሰጣቸው ወሬዎች መከከል በቅርቡ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሽልማታቸውን ማክሰኞ እንደሚረከቡ ይጠበቃል። ከዚህ ሽልማት አሰጣጥ ጐን ለጐን ተፈጠረ የተባለው ብዥታ ነው። ብዥታው የተፈጠረውና እንደ ችግር አነጋጋሪ የኾነው ጉዳይ የኖቤል ሽልማቱ አካል ነው በተባለው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የማይሳተፉ መኾኑን ማሳወቃቸው ነው።

ለምን እንደሆነ ባይታወቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሰዱ የተባለው እርምጃ ግን በተለያዩ ሚዲያዎች ትችት እያሰነዘረ ሲሆን፣ ለምን? የሚል ጥያቄ እስከማስነሳት ደርሷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዜጣ መግለጫ ላይ ላለመገኘት መብት ያላቸው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ አሸናፊ የሆኑ ግለሰቦች በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተሳታፊ እንዳልነበሩ በማስታወስ፤ ጉዳይ አዲስ አለመኾኑን የሚጠቅሱ ወገኖች አሉ። በአንጻሩ ደግሞ፤ መግለጫውን ያለመሥጠት አግባብ አይደለም በሚል ይሟገታሉ።

የጉዳዩ በዚህ ሁኔታ ያለ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኖርዌይ በመሔድ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!