Ethiopia Zare's weekly news digest, week 14, 2012 Ethiopian calendar

ከኅዳር 29 - ታኅሣሥ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ አራተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከኅዳር 29 - ታኅሣሥ 5 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ከሳምንቱ ክንውኖች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሰላም የኖቬል ሽልማት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዚህ ሳምንት ከፍተኛ የዜና ሽፋን ያገኘውም ይኸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቬል ሽልማትና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ይደግፋሉ የተባሉ የገንዘብ ድጋፎች በጉልህ የታዩበት ሳምንት ነበር። ለኢኮኖሚው ሪፎርም ትግበራ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ካደረጉት ውስጥ የዓለእ አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ / IMF) የፈቀደው የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ትልቅ ዜና ሆኖ ይጠቀሳል።

ከአነጋጋሪ ክስተቶች መካከል ደግሞ በዋልታ ድረገጽ ላይ ለደቂቃዎች ተነቦ መልሶ ድርግም ያለው ዜና ነው። የትግራይ ክልልም ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አረፉ የሚለው ዜናው አነጋጋሪ ሆኖ ብቻ የሚቀር አይመስልም። በሕወሓትና በዋልታ መካከል ውዝግብ የሚፈጥር ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ለተፈጠረው ስሕተት ዋልታ ይቅርታ ቢጠይቅም፤ የክልሉ መንግሥት መስሚያ የለኝም እከሳለሁ ብሎ ተነስቷል። የክልሉ ሚዲያዎችም ዋልታን በሚያወግዙ ዘገባዎች እንደተወጠሩ ነው። እንዲህ ያሉና ሌሎች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ወሬዎች የተደመጡት ከቀዳሚው የሳምንቱ ክስተቶች ውስጥ የተወሰኑት እንዲህ ባለው መንገድ በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ተጠናክረዋል።

ሽልማቱ!

የሳምንቱ ዐቢይ ዜና ዐቢይ ነው። ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የኖቬል ሽልማት ርዕሰ ዜናነቱ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበረም። ኢትዮጵያን የሚመለከት ኾኖ የተገደበ አልነበረም። በኖርዌይ ርዕሰ ከተማ የኖቬል ሽልማቱ ዝግጅት ለዓለም የተላለፈ የዓለም ጉዳይ ነበር። የኖቬል ሽልማቱ ፕሮግራም በመላው ዓለም ከ1.5 ቢሊዮን ሕዝብ በላይ የተመለከተው እንደሆነ ተነግሯል። ስለዚህ ዶክተር ዐቢይ የሽልማት ፕሮግራም ዓለም አቀፍ ነበር። የዓለማችን ታላላቅ ሚዲያዎች ቦታ ሠጥተው ብዙ የዘገቡበት ጉዳይ ነው። ይህ መድረክ ዶክተር ዐቢይ በክብር ካገኙት ሽልማት በላይ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የተዋወቀችበት ነው።

በመድረኩ ኢትዮጵያ የታወቀችበት፣ ስለእርሷ የተነገረበት መንገድ ለየት ብሎ የሚታይ ነበር። በተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት ብቻ ሳይሆን፤ በፕሮግራሙ መሪ ወይም የሽልማት ኮሚቴው ሰብሳቢ ስለኢትዮጵያ ያሉት ሁሉ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረገ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህም ቀደም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዲህ ባለ ደረጃ ተዋውቃለች ብሎ ለመግለጽ ያስቸግራል።

የሽልማት ኮሚቴው ሰብሳቢ በዚያ መድረክ ስለኢትዮጵያና ስለ ዶክተር ዐቢይ ከገለጹት ውስጥ፤ ኢትዮጵያ በምዕራብያውያን ቅኝ ያልወደቀች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር መሆንዋን ስስት በሌለው ቃላት መግለጻቸው አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ስለመሆንዋም በሚገባ ተናግረዋል። አስደማሚው ነገር ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መኾንዋን በማመን መግለጻቸው ብቻ አልነበረም። ያስከተሉት ሌላው ከአንደበታቸው የወጣው ንግግር ነበር። ይህም “ስለዚህ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ከሆነች ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን” የሚለውን ማከላቸው ነበር። ይህንን አንደበታቸውን ተከትሎ በዚያ ባማረ አዳራሽ የታደመው ሁሉ የሞቀ ጭብጨባ መታጀቡ “እርግጥ ነው” ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን የሚለውን እንደማረጋገጥ የተቆጠረ ነበር።

እንዲህ ባለው መንገድ ኢትዮጵያ የተዋወቀችበት መንገድ አለ ተብሎ አይገመትም። ስለዚህ ይህ መድረክ አንድ የኢትዮጵያ መሪ የኖቬል ተሸላሚ ከመኾን በላይ አገርን በሰፊው ያስተዋወቀ መድረክ እንዲሆን አስችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ ከእርሳቸው አንደበት ይጠበቅ ነበርና ለ21 ደቂቃ የፈጀ ንግግራቸውም ቢሆን (ኖቤል ሌክቸር)፤ ብዙዎችን የመሰጠ ስለመኾኑ በተለያዩ ሚዲያዎች በተለያዩ መንገዶች ገልጸውታል።

ስለሽልማቱ ከተለያዩ ግለሰቦች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲስተጋባ የተሰማውም ይህ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ደግሞ አንዱ ናቸው። “አፄ ኃይለሥላሴ ከነግርማ ሞገሳቸው ከዙፋናቸው ከወረዱ በኋላ የኢትዮጵያ ስም እንዲህ በገናናነት ተሠምቶ አያውቅም” በማለት አስተያየታቸውን ይጀምራሉ።

የኢትዮጵያውያን ልብ በኩራት አበጥ ብሎ እንደማያውቅና ኢትዮጵያዊነት ቀና ብሎ እንደማያውቅ ጭምር በማስታወስ ስለሽልማቱ አስተያየታቸውን ሠጥተዋል። አያይዘውም ሽልማቱ ትልቅ ነገር መኾኑንና “ቁም ነገሩ ዐቢይ ሽልማቱን መቀበሉ አልነበረም፣ ከዐቢይ ጋር ተቆራኝቶ እንደሚቀርም እርግጥ ነውም” ብለዋል።

ለእርሳቸው ግን ትልቁ ቁም ነገር ሽልማቱ ምክንያት ለኾነለት የዐቢይ ንግግር እንደሆነ ጠቅሰዋል። የዐቢይ ንግግር በእንግሊዘኛ ከመኾኑ ሌላ ድንቅ፣ ልብን የሚነካና ኢትዮጵያዊ ሰውነትን ያጐላ እንደነበር በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል። ማሳረጊያቸውንም “ዶክተር ዐቢይ እግዚአብሔር ይባርክህ መንገድህን ያቅናልህ!” በማለት ነበር አስተያየታቸውን የሠጡት።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ዶክተር አረጋዊ በርሄም ሽልማቱ የሁሉም መኾኑን የገለጹ ሲሆን፣ ለዶክተር ዐቢይ እንደሚገባ፣ እንዲሁም ላደረጉት ጥረት የተገኘ ሽልማት እንደሆነ በመጥቀስ ሽልማቱን አወድሰዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሴክረተሪያት አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ ሽልማቱ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረገ ነው ብለው ገልጽውታል። እንዲህ ያሉ አስተያየቶች ብዙ ናቸው ሲሠጡ የሰነበቱት። ሌላው ቀርቶ ጃዋር መሐመድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንኳን ደስ አለዎት ወንድሜ የሚል መልእክት በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

ከኦስሎ መልስ በቤተመንግሥት በተደረገ ግዥ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ሽልማቱ ትልቅ ክብር የሚሠጠው ስለመኾኑ አስታውሰዋል። አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም የሰላም ኖቬል አሸናፊው መኾን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ መኾኑን ተናግረዋል። “ኖቬል ሽልማቱ የተበረከተው ለተሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን፤ ለሚቀሩ ሥራዎችም የተሠጠ በመኾኑ፤ ይህንን ታላቅ የደስታ ቀን ተባብረን ተደጋግፈን አገራችንን በጋራ ማልማት አለብን” ብለዋል።

መጨረሻ ላይ በንግግራቸው የገለጹት ደግሞ “ኢትዮጵያውያን የተጋረጠብንን ችግር በጋራ ከመፍታት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም በማለት፤ የተለየ አስተሳሰብና አማራጭ ማቅረብ የዴሞክራሲ ገጽ እንጂ በአስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት በጠላትነት መፈራረጅ አይገባም” ብለዋል።

በዚህ እራት ግብዣ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሥራ ከሚል መልእክታቸው ባሻገር፤ ይህ ሽልማት በር ከፋች መኾኑን በሚገልጽ ነበር። በተለይ ለዚህ ሽልማት እንዲበቁ የበኩላቸውን ላበረከቱት ኢሳይያስ አፈወርቂ ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዜጐች በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ መሥራት እንደሚገባ በማመልከት፤ “ዜጐች ምክንያታዊ ባልኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ እርስ በርስ መናቆርን በማስወገድ ለአገር እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

በዚህ ሽልማት ዙሪያ የተለያዩ ሐሳቦች የተሸንራሸሩበት ሳምንት ነበር። ዓርብ ዕለት ደግሞ የኖቬል ሽልማቱ በብሔራዊ ሙዚየም እንዲቀመጥ መወሰኑም ተያያዥ ዜና ነበር።

እንዲህ ያሉ እውቅናዎች ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ሰፋ ብሎ የተተነተነበት ሲሆን፣ የሽልማቱን መገኘት አስመልክቶ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች የእንኳን ደስ ያላችሁ ዝግጅቶች ተካሒደዋል። በተለይ በአዲስ አበባ የከተማው ነዋሪ ማልዶ ወጥቶ ዶ/ር ዐቢይን መቀበሉ ይጠቀሳል። (ኢዛ)

ዋልታ እና ሕወሓት

ባሳለፍነው ሳምንት ዓርብ ወደ አሥር ሰዓት አካባቢ የተሰማው አንድ ወሬ ደግሞ በተለየ የሚታይ ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው፤ በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ስም ካላቸው ከሚባሉ ሚዲያዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ዋልታ በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው አንድ አጭር “ዜና”፤ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባልታወቀ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን የሚገልጽ ነው። ይህንን መረጃ ያወጣው ዋልታ ነበርና ዜናውን ላለማመን ከባድ ነበር። ነገር ግን በፌስቡክ ገጹ ላይ የተነበበው ይህ ዜና ከደቂቃዎች በኋላ ተነሳ።

ወዲያው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ሴንተር ይህ በዋልታ ፌስቡክ ገጹ ላይ የታየው “መረጃ” ከእርሱ እውቅና ውጭ የኾነ መኾኑንና ለተፈጠረው ስሕተት ይቅርታ እንዲጠይቅ ያስገደደበት ነበር።

በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ በከፍተኛ ካፒታልና በጠንካራ አደረጃጀቱ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ የኾነው ዋልታ እንዲህ ያለው ስሕተት መፈጠሩ ብዙ አግራሞት የፈጠረ ሲሆን፣ የዋልታዎችንም ያስደነገጠ ነበር ተብሏል። ይህ መረጃ ለምን እንዴት በዚህ መልክ እንዲሠራጭ ተፈለገ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ዋልታዎች ማጣራት ውስጥ ገብተዋል። አፅእኖት ሠጥተው የገለጹትም ከድርጅቱ እውቅና ውጭ የተፈጸመ መኾኑን ነው። የዋልታ ሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ንጉሤ መሸሻ በቴሌቪዥናቸው ላይ ወጥተው ይህንኑ ይቅርታ ደግመዋል። ኾኖም እንዲህ ያለ ነገር ከማጋጠሙ በፊት ከዚህ ቀደም ዋልታ በሚሠራቸው ሥራዎች ያልተደሰቱ ወገኖች ድርጅቱ ቢሮ ድረስ በመሔድ ተቃውሞ ያሰሙ መኾኑን አስታውሰዋል። ከዶክተር ደብረጽዮን ጋር ተያይዞ የተደረገው ድርጊትም ከጀርባው ሌላ አካል ያለ መኾኑን ለማመላከት ሞክረዋል። ዋልታ በሚሠራቸው ዶክመንተሪዎች ደስታ ያልፈጠረባቸው የሠሩት ሊሆን ይችላል የሚልም አስተያየት አላቸው።

ይህ ግርታ የፈጠረ ጉዳይ ውጤቱ ምን ያስገኛል? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ኾኖ፤ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግን ጉዳዩ ኾን ተብሎ የተፈጸመ ነው በማለት በክልሉ ሚዲያዎች ተቃውሞ ማሠማት የጀመረው ጉዳዩ ተፈጸመ በተባለ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ነበር። በተለይ የትግራይ ሚዲያዎች ይህንኑ ጉዳይ ሰፊ ሽፋን ሠጥተው ነገሩ ኾን ተብሎ የተፈጸመ መኾኑን የሚገልጹ አስተያየቶችን በማስተናገድ ሰፊ ዘገባ እየሠጡበት ይገኛሉ።

ዶክተር ደብረጽዮንም ምን ተፈልጐ እንደተደረገ ባይገባኝም፤ የትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ታስቦ የተሠራ ነው በሚል ድርጊቱን አውግዘዋል። የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮም በይፋ ክስ እንደሚመሠርት አስታውቋል። ዋልታ በተደጋጋሚ እያጠፋ ነውም ብሏል።

ዋልታ በክልሉ ላይ ተደጋጋሚ የኾነ ችግር እየፈጠረ ስለመኾኑም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ግን የዚህ ድርጊት መፈጸም ምን ለማግኘት ታስቦ የተፈጸመ ነው? ለሚለው ጥያቄ ላይ ብዥታው አልጠራም።

በተለይም የዋልታ አመሠራረት በአብዛኛው ከሕወሓት ጋር የተያያዘ ከመኾኑ አንጻር የትግራይ ክልል በዋልታ ላይ የከፈተው የውግዘት ዘመቻን አነጋጋሪ አድርጐታል። የትግራይ ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ እያስተጋቡ ያሉት ምሬት ያዘሉ ዘገባዎችም ለየት ብለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። ዋልታ ከእርሱ ቁጥጥር ውጭ በኾነ መንገድ የተፈጠረ ስሕተት መኾኑን በመግለጽና ሁኔታውንም እያጣራሁ ነው ቢልም፤ የትግራይ ቢሮ ኃላፊ እንዴት ተደርጐ ነው በይቅርታ የሚተላለፈው በማለት ክስ እንመሠርታለን ብለዋል።

ዋልታ በሕወሓት እጅ የነበረ ሚዲያ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህንን ሚዲያ በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩት እንደ ወይዘሮ አዜብ ያሉ ከፍተኛ የሕወሓት አባላት መሆናቸው ሲታወስ “ነገሩ ምንድነው?” የሚል ከበድ ያለ ጥያቄ አስከትሏል።

ዋልታ አሁን ከቀደመው አሠራር ወጣ ብሎ ከለውጡ በኋላ የሚያቀርባቸው ዝግጅቶች የተለዩ መኾናቸውም ይታወቃል። (ኢዛ)

የቢሊዮን ዶላሮች ሳምንት

ከፋይናንስና ኢኮኖሚ አንጻር ያሳለፍነው ሳምንትን በተለየ የምናስበው ኢትዮጵያ ከጀመረችው ሪፎርም አንጻር ተግባራዊ ለምታደርገው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያስፈልገው ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቃል ስለመገባቱ የተወሳበት ነው።

አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማድረግ የተቀረው ፖሊሲ ከዚህ ቀደም ውይይቶች የተደረገባቸው ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ገልጸው ነበር። ይህ ከተሰማ በኋላ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅቱ (IMF) ለኢትዮጵያ ፈቅዶ የማያውቀውን 2.9 ቢሊዮን ብር ለማበደር ቃል ገብቷል። በተመሳሳይ የዓለም ባንክም ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለመደገፍ ቃል መግባቱ ታውቋል። ይህ ገንዘብ የአገሪቱ የአንድ ዓመት አንድ ከፍተኛ በጀት የሚያክል ከመኾኑ አንጻር፤ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት የራሱ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል።

ጉዳዩ ትልቅ ነውና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የተሰማውን መልካም ዜና ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ “እንዲህ ያለው ድጋፍ ለማክሮ ኢኮኖሚ፣ መዋቅራዊና ለሴክተር ማሻሻያዎች የሚል ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም ባንክና IMF ቃል ከገቡት ውጭ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክም ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚሠጥ ተናግረዋል።

የIMF ዜና ከመሰማቱ ቀደም ብሎ ከተለዩ አገሮችና ተቋማት ኢትዮጵያ ያገኘችው የገንዘብ ድጋፍ የቀዳሚዎቹን ሁለት ሳምንታት የተለየ አድርጓቸዋል ተብሎ ሊታይ ይቻላል።

ከይፋዊ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ጀርመን 320 ሚሊዮን ይሮ ለመሥጠት ተስማምታለች። ከተመረጡ በኋላ የመጀመሪያ ጉዟቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉት የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሶላ ቮንዳር ባዶ እጃቸውን አልወጡም። 170 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ሠጥተዋል። የቤልጅየም መንግሥት ደግሞ ለምርጫ ማስፈጸሚያ ብሎ ወደ 800 ሺሕ ዩሮ አበርክቷል።

የእነዚህ አምስት አገሮችና ተቋማት በሁለት ሳምንት ውስጥ የሠጡት ድጋፍ በጥቅል ከታየ 186 ቢሊዮን ብር በላይ ይኾናል። (ኢዛ)

ባንኮችና አፈጻጸማቸው

ኢትዮጵያ ውስጥ በፋይናንስ ዘርፍ ከተሰማሩ የግል ባንኮች ውስጥ የስድስት ባንኮች የ2011 አፈጻጸንም የተመለከተ ዋና ዋና መረጃዎቻቸውን በድረገጻችን ላይ ማቅረባችን አይዘነጋም። ከዚያ ወዲህ የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸማቸውን ይፋ ካደረጉት ባንኮች ውስጥ ደግሞ የሦስቱን ሪፖርት በዚህ ዘገባችን እንዳስሳለን። በቀዳሚዎቹ የሳምንቱ ቀናት ሪፖርታቸውን ካቀረቡት ባንኮች አንዱ ብርሃን ባንክ ነው። ብርሃን ባንክ በሪፖርቱ እንዳሰፈረው በ2011 የበጀት ዓመት 580 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ነው። የባንኩ ዓመታዊ ትርፍ ከ2010 የ28 በመቶ ብልጫ አለው።

ሁለተኛው ዓባይ ባንክ ሲሆን፣ ዓባይ ባንክ የ2011 ትርፉን 63 መቶ አሳድጐ 680 ብር ማትረፉን ገልጿል። ይህ ትርፍ በ2010 ካስመዘገበው ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ይበልጣል። አጠቃላይ የሀብት መጠኑም 29 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጿል።

ደቡብ ግሎባል ባንክም በ2011 የበጀት ዓመት 284 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈና ይህም ትርፍ በ2010 አስመዝግቦት ከነበረው ከ110 ሚሊዮን ብር እንደሚበልጥ ገልጿል። የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 5.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጿል። ባንኩ በ2010 በጀት ዓመት ከነበረው 3.3 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት ጋር ሲነጻጸር የ68 በመቶ እድገት አሳይቷል። (ኢዛ)

የግል ባንኮች ወለድ እየቀነሱ ነው

16ቱ የአገሪቱ ባንኮች ለብድር የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን ይቀንሳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ እስካሁን ሁለት ባንኮች ለብድር ይጠይቁ የነበረውን የወለድ መጠን መቀነሳቸውን አስታውቀዋል።

ባንኮች ወደዚህ እርምጃ እየገቡ ያሉት፣ በቅርቡ መንግሥት የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመሪያን በማንሳቱ ነው። ይህ ለዓመታት በአስገዳጅነት ሲፈጸም የነበረ መመሪያ ባንኮች የብድር ወለድ ተመናቸውን ከፍ አድርጐት እንደቆየ ይታወሳል። አሁን ግን ይህ መመሪያ መነሳት ባንኮቹ የብድር ወለድ ተመናቸውን እንዲቀንሱ እያደረገ ነው። እስካሁን ካሉ መረጃዎች ማወቅ እንደሚቻለው፤ አዋሽ ባንክና አቢሲንያ ባንክ እስካሁን ለብድር ሲያስከፍሉ ከነበረውን የወለድ ምጣኔ ላይ እንደየብድር ዐይነቶቹ የሚታይ ቅናሽ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

አዋሽ ባንክ እስከ 4.5 በመቶ የብድር ወለድ ቅናሽ ሲያደርግ፤ አቢሲንያ ደግሞ እስከ ስድስት በመቶ ለመቀነስ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል። ይህም ውሳኔ ባንኮቹ እስከ 17 በመቶ ይጠይቁበት የነበረው የወለድ ምጣኔ እንደ ብድሩ ሁኔታ ይቀንሳሉ ማለት ነው። ይህ ውሳኔ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። (ኢዛ)

አሳሳቢው የዋጋ ግሽበት

ከሳምንቱ ወሬዎች እንደመልካም ያልታየው ዜና የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት አሁንም እያሻቀበ መኾኑ ነው። በተለይ የዋጋ ግሽበቱ ምግብ ነክ የኾኑ ምርቶች ላይ ማየሉ ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።

የኅዳር ወር የዋጋ ግሽበት 21 በመቶ ስለመድረሱ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገልጿል። ይህ በገበያ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ እድገት እየታየ መኾኑን አመላክቷል።

በቀዳሚው ዓመት 16 በመቶ የዋጋ ግሽበት የታየ ቢሆንም፤ አሁን ግን በዚህን ያህል መጨመሩ አሳሳቢ ስለመኾኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!