Ethiopia Zare's weekly news digest, week 50th, 2012 Ethiopian calendar

ከነኀሴ 11 - 17 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃምሳኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከነኀሴ 11 - 17 ቀን 2012 ዓ.ም.) ካሳለፍነው ሳምንት ቀዳሚ ዜናዎች ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለ10 የሥራ ኃላፊዎች ሹመት መስጠታቸው ነው። በተለይ የምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ስንብት ያልተጠበቀ ሲሆን፣ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ 32ኛዋ ከንቲባ ኾነዋል።

ከሳምንቱ ፖለቲካዊ ክንውኖች ውስጥ ከየአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ስብሰባ የመቀመጣቸው ጉዳይ ሲሆን፤ በመድረኩ በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የቀረበ ጽሑፍ ግን አነጋጋሪ ተብሏል። ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል የማዛወሩ ሒደት አሁንም አነጋጋሪ ቢኾንም፤ ሒደቱ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በአንድ ጊዜ አምስት መመሪያዎችን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማንም ሰው በቤቱ 1.5 ቢሊዮን ብር ማስቀመጥ የማይችል መኾኑን አስታውቆ፤ ይህንን የተላለፈ ይቀጣል ብሏል። የአገሪቱ ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች ብድር መውሰድ የሚችሉበትን መመሪያም ያወጣው በዚህ ሳምንት ነው። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አቋሜን እወቁልኝ ብሎ መግለጫ አውጥቷል። ከመቼውም ጊዜ እስር በርትቷል ብሎም አማሯል።

ከሳምንቱ አነጋጋሪ ዜናዎች የወላይታ ዞን አመራሮች መታገዳቸው ነው። የአገሪቱ ራስ ምታት የኾነውን የወጪ ንግድ አሁን ካለበት 3 ቢሊዮን ብር ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለማድረስ ያስችላል የተባለ መሪ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል። በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት 2.56 ቢሊዮን ብር ማትረፉን እወቁልኝ ያለው በዚህ ሳምንት ሲሆን፤ ከዕቅዴ በላይ አትርፌያለሁ ብሏል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት በቅርቡ በኹከት የወደሙ ንብረቶችን የመተካቱን ሥራ እናጠናክራለን ብለዋል። የሕግ ማስከበሩ ሥራ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ሕወሓት ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ለማካሔድ ላሰበው ምርጫ ነዋሪዎች ካርድ ውሰዱ ያለ ሲሆን፤ ይህንን የማያደርግ የስድስት ወር እስራትና 500 ብር እንደሚያስቀጣ አስታወቀ የተባለውም በዚህ ሳምንት ነበር።

በአዲስ አበባ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚወጣበት ግዙፍ የቤቶች ግንባታን ለማከናወን ውለታ ተገብቷል። እኒህንና ሌሎች ዜናዎች የተጠናከሩበት የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የሳምንቱ ምልከታችን እንደሚከተለው ይቀርባል። መልካም ንባብ!

ያልተጠበቀው ሹም ሽርና 32ኛዋ የአዲስ አበባ ከንቲባ

ከሳምንቱ ቀዳሚ ዜናዎች ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ10 ተሿሚዎች ሹመት መስጠታቸው ነው። በተለይ ከለውጡ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተነስተው፤ በወይዘሮ አዳነች አቤቤ መተካታቸው ያልተጠበቀ ነበር። ኾኖም ኢንጂነር ታከለ የነዳጅና ማዕድን ሚኒስቴር ኾነዋል።

በዚህ አዲስ ሹመት መሠረት ወይዘሮ አዳነች የአዲስ አበባ 32ተኛዋ ከንቲባ በመኾን ኃላፊነቱን ሲወስዱ የመጀመሪያዋ ሴት የከተማዋ ከንቲባ ለመኾን በቅተዋል። ከሰሞኑ እየተሰጡ ካሉ አስተያየቶች ደግሞ ካለፉት 29 ዓመታት አዲስ አበባን በከንቲባነት በመምራት እንደ ኢንጅነር ታከለ እና ዶ/ር አርከበ እቁባይ የተሻለ ተቀባይነት ያገኘ ያልነበረ መኾኑ ነው።

ዶ/ር ዓለሙ ስሜ፣ አቶ አሰግድ ጌታቸው እና ረሻድ ከማል የተባሉት የብልጽግና አመራሮች ለቦታው ታጭተው የነበሩ መኾኑ የተደመጠ ሲሆን፤ ኾኖም ሦስቱም ፍላጎት ባለማሳየታቸው አዲስ አበባን ለመምራት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተመርጠው አዲስ አበባን ማስተዳደር ጀምረዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ምርጫ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ ለማድረግ ከወሰነ በኋላ የምርጫ ቀኑን (ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) በመወሰን ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል። በዚህም ሳምንት የመራጮች ምዝገባ የጀመረ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ግን የምርጫ ካርድ አለመውሰድ የሚያስቀጣ መኾኑን እያስታወቀ ነው።

የሕወሓት ካድሬዎች በተለይ በወልቃይት፣ በራያና መሰል የማንነት ጥያቄ የሚጠየቅባቸው አካባቢዎች በመሔድ ምርጫ ካርድ ያለመውሰድ፤ ስድስት ወርና 500 ብር ያስቀጣል በማለት ነዋሪውን እያስጨነቁት ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኞችም ምርጫ ካርድ ሳይዙ ወደ ሥራ አትምጡ እየተባለ ስለመኾኑ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።

ሕገ መንግሥታዊ እንዳልኾነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየው የትግራይ ክልል ምርጫ ከተካሔደ ፌዴራል መንግሥቱን ያስጠይቀዋል የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው። በዚህ ሳምንት የወጣው የትግራይ ትብብር ፓርቲ መግለጫ፤ በክልሉ የሚካሔደውን ሕገወጥ ምርጫ ፌዴራል መንግሥቱ ማስቆም አለበት ብሏል። አያይዞም ይህ የማይደረግ ከኾነ የፌዴራል መንግሥቱ በታሪክ የሚጠየቅበት ይኾናል ሲል አሳስቧል። (ኢዛ)

የአምስት የሕወሓት አባላት የፍርድ ቤት ውሎ

ከሰሞኑ የፍርድ ቤት ውሎ መካከል በአዲስ አበባ የሕወሓት ጽሕፈት ቤት የተለያዩ ኃላፊዎች ላይ የተከፈተውን ክስ የሚመለከተው አንዱ ነው። የአዲስ አበባ ሕወሓት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃዲቅ፣ የሕግና ፍትሕ ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም ይደጉ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የደኅንነት ኃላፊ አቶ አጽብሃ አለማየሁን ጨምሮ አምስት ተጠርጣሪዎች በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል፣ የመንግሥትን የደኅንነት ሚስጥር በውጭ ላለ የሽብር ቡድን አሳልፈው ሰጥተዋል ተብለው ምርመራ ሲደረግባቸው የነበሩ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ ጉዳያቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት በተጠረጠርንበት ወንጀል ተመርምሮ የወንጀል ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ታይቶ የቀረበ ማስረጃ የለም፤ ስለዚህ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም የሚሉ መቃወሚያዎችን አቅርበዋል። ኾኖም ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው ከግምት ውስጥ ያስገባው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ10 ቀን ጊዜ ፈቅዷል። (ኢዛ)

በሕይወት እና በንብረት ላይ የሚቆምር ፖለቲካ ይቁም

ባሳለፍነው ሳምንት ፖለቲካዊ ክንውኖች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የአገሪቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ያደጉት ስብሰባ ነው። የስብሰባው ዋና ዓላማ በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ለመምከር ሲሆን፤ የተለያዩ ጽሑፎችም የቀረቡበት ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ንግግረ ያደረጉት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም፤ “በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ቁማር ከሚጫወት የፖለቲካ አካሔድ በመውጣት፤ የኢትዮጵያን ደኅንነታዊ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።

እንደ አገር በአንድነት ለመቆም መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሕዝቡ የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ሚና እንዲወጡ የጠየቁት አቶ ሙሳ፤ ፓርቲዎች መቀራረብና የሐሳብ መሸናነፍን ያስቀደመ የፖለቲካ ባህል በማዳበር ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱ መኾን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
“ያለችን አንድ አገር ናት” ያሉት አቶ ሙሳ፤ መንግሥት የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከጥፋትና ውድመት የሚታደግ፤ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የዜጎችን መንግሥትን በሐሳብና በሰላማዊ ሰልፍ የመቃወም መብትንም ማክበር እንደሚኖርበትም በስብሰባው መክፈቻ ተናግረዋል።

ምክር ቤታቸው ለአሳዳጅ ተሳዳጅ የፖለቲካ ፍጻሜ ለማበጀት እንደሚሠራና ከሁሉ በፊት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ቁማር ከሚጫወት የፖለቲካ ሥርዓት መውጣት እንደሚያስፈልግም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ይሁንና በዚህ መድረክ ጽሑፍ አቅራቢ ከነበሩት አንዱ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ያቀረቡት ጽሑፍ ከትብብር የበለጠ መለያየትን የሚያቀነቅን ነው በሚል በፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሳይቀር ተኮንኗል። (ኢዛ)

የተስተባበለው የግድያ ሙከራ በአማራ ክልል

ከሰሞኑ ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ዜና በአማራ ክልል ሊደረግ በነበረው የባለሥልጣኖች ግድያ ከሽፏል የሚል ሲሆን፤ ግድያውም የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህን፣ የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ አዛዥ አቶ አበረ አዳሙን፣ አቶ አገኘው ተሻገር እና ሌሎችም የክልሉ ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የሚጠቅስ ነው። ኾኖም የክልሉ መንግሥት ይህንን ዘገባ አስተባብሎ መግለጫ አውጥቷል። (ኢዛ)

የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ጉብኝት

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ ቡድን በቅርቡ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች በተከሰተው ኹከትና ግርግር የተጎዳውን ንብረት መልሶ ለማቋቋም እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች ለመቃኘት የመስክ ጉብኝት አድርገዋል። ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ኪዋይ ከተማ የተጀመረው ጉብኝት፤ አርሲ ነገሌና ሻሸመኔን ጨምሮ የምዕራብ አርሲ፣ አርሲ እንዲሁም ባሌን ያካተተ ነበር።

የተፈናቀሉ ወገኖችና የወደመውን ንብረት ፈጠኖ ወደ ቦታው ለመመለስና ቋሚ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ፤ ብሎም የንግድ ተቋማቱ ጥገና ተደርጎላቸው ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችል ግብዓት ታስቦ የተደረገ ፕሮግራም ሲሆን፤ በየከተሞቹም ከነዋሪዎች ጋር ተነጋግረዋል። በእነዚህ የውይይት መድረኮች ላይ ከተሰብሳቢዎች ጐልቶ የተነሳው፤ “ሕግ ይከበር! የመኖር ዋስትናችንን አስጠብቁልን!” የሚል ነው። (ኢዛ)

ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር በአዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ መንደር ለመሥረት ያስችላል የተባለውና ከሦስት ቢሊዮን ብር በተለይ እንደሚፈጅ የተነገረለትን ግዙፍ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን ለማስጀመር የቤቶች ኮርፖሬሽን ከአገር ውስጥና ከውጭ ተቋራጮች ጋር ስምምነት ያደረገው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ነበር።

ይህ ከአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ የሚገነባው፤ “የገርጂ መኖሪያ መንደር” በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ 510 መኖሪያ ቤቶች የያዙ ባለ 10 ወለል እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

የመኖሪያ መንደሩ ሲጠናቀቅ በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር በተወሰነ መልኩ የሚያቃልል ይኾናል ተብሏል። በሦስት ሔክታር ላይ የሚገነባው ይህ መንደር ሲጠናቀቅ፤ ዘመናዊነትን የተላበሰ ቅንጡ የመኖሪያ መንደር ይኾናል ብሎ እንደሚታመንም የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች አመልክተዋል። (ኢዛ)

የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭና የውጭ ኩባንያዎች ምዘና መጠናቀቅ

ከአገሪቱ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የኾነውን ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ዘርፍ ለማዞር እና ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጐት አሳይተዋል የተባሉ የውጭ ኩባንያዎች ምዘና ስለመጠናቀቁ የተሰማው በዚህ ሳምንት ነው።

ኢትዮ ቴሌኮምን ለውጭ ኩባንያ በከፊል ለመሸጥ እየተደረገ ነው የተባለው እንቅስቃሴ የተለያዩ ተቃውሞዎችን ያስነሳ ሲሆን፤ ወደ ግል የማዛወሩ ሒደትም ብዥታ አለው እየተባለ ቢኾንም፤ በአሁኑ ወቅት ለውጭ ኩባንያ ለመሸጥ ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ ምዘናዎች እየተጠናቀቁ ነው ተብሏል።

የቴሌኮም ሥራ እንዲሠሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ኩባንያዎች የሚሰጣቸው ፈቃድ ብዙ ዋጋ የተሰጠበትና ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዞር ሥራዎች ተጠናቅቀው ተወዳድሮ ያሸነፈው አማካሪ ድርጅት ወደ ሥራ እንደሚገባም ተጠቅሷል። (ኢዛ)

የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ዓመቱን 2.5 ቢሊዮን ብር በማትረፍ አጠናቀቀ

የ2012 በጀት ዓመት መጠናቀቅን ተከትሎ ዓመታዊ አፈጻጸማቸውን ይፋ እያደረጉ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት ዓመታዊ አፈጻጸሙን ይፋ ያደረገው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 2 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ አስታውቋል። እንደ ድርጅቱ መረጃ በ2012 አተርፋለሁ ብሎ ዐቅዶ የነበረው 2 ነጥብ 44 ነበር። ኾኖም ከዕቅዱ በላይ በማትረፉ አፈፃፀሙ 105 በመቶ ሆኗል።

ድርጅቱ ይህን ትርፍ ሊያገኝ የቻለው ገቢ ዕቃዎች በባሕር በማጓጓዝ፣ በውጭ አገር ወደቦች መካከል የጭነት አገልግሎት በመስጠት፣ በመልቲ ሞዳል ወደ አገር ውስጥ ኮንቴይነርና ተሽከርካሪዎችን በመጓጓዝ ነው። ከዚህም ሌላ በዩኒሞዳል ገቢ እና ወጪ ዕቃዎችን በማስተላለፍ፣ በአገር ውስጥ ደረቅ ወደቦች ኮንቴይነርና ገቢ ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ እና ወጪ ጭነት በአገር ውስጥ በማሸግ አገልግሎት ከፍተኛ ገቢ አግኝቷል። (ኢዛ)

የወጪ ንግድን ከ3 ወደ 9 ቢሊዮን የማሳደግ ውጥን

አገሪቱ በአስር ዓመት ትደርስበታለች ተብሎ የተሰናዳው መሪ የልማት ዕቅድ በየዘርፉ ያሉ ተቋማት ውጥናቸውን እያስታወቁ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት የአሥር ዓመት የልማት መሪ ዕቅዱን ያስታወቀው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፤ በተለይ የወጪ ንግድን ለማሳደግና ለመሥራት የታሰበውን እና የልማት መሪ ዕቅዱ አካል የኾነው መረጃ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ 9 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ለማግኘት መታቀዱን ነው።

ሚኒስቴሩ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ዙሪያ ይፋ ባደረገው በዚሁ መረጃው፤ በቀጣይ 10 ዓመታት በአምራች ኢንዲስትሪው ዘርፍ አምስት ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ስለመታቀዱ አመልክቷል። ኢትየጵያ የወጪ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገኘበት ተብሎ የሚጠቀሰው የቀጠናቀቀው የገቢ በጀት ዓመት ነው። በዚህ በጀት ዓመት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መኾኑ መጠቀሱ ይታወሳል። (ኢዛ)

የአትክልትና ፍራፍሬን የወጪ ንግድ በአዲስ መልክ

ከሰሞኑ ለየት ብሎ ሊነሳ የሚችለው የቢዝነስ ዜና፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዝቃዛ የአትልክትና ፍራፍሬ ምርቶችን በባቡር በማጓጓዝ ከወደብ በመርከብ ወደተለያዩ አገሮች ገበያ መሸጥ መጀመሯ ነው።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት፤ አቮካዶ የጫነ የመጀመሪያው ኮንቴነር ባሳለፈነው ሳምንት ከሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ አውሮፓ አገሮች ለሙከራ ተልኳል።

እንዲህ ባለው መንገድ ምርቶቹ ለውጭ ገበያ መቅረባቸውን በተያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲኾኑና ለአገሪቱ የወጪ ንግድ እድገት እገዛ ይኖረዋል። (ኢዛ)

የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውል ተወሰነ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ነኀሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው 88ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፤ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ፖሊስ ላይ ነው።

የብሮድካስት ባለሥልጣን የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚመራበት ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ባለመኖሩ፤ ዘርፉን በብቃትና በጥራት ማስፋፋትና ሁሉንም ዜጎች የመረጃ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን በመግለጽ፤ የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን የሚመራበትና የሚደገፍበት ፖሊሲ እንዲኖር የሚያስችል ውሳኔ ነው።

አገሪቱ ከምትከተለው የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ከመሠረታዊ የሰው ልጅ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ሕግጋት፣ ከሕብረተሰቡ ባህል፣ እሴት፣ አመለካከትና ፍላጎት፤ እንደዚሁም በዘርፉ ካጋጠሙ መሠረታዊ ተግዳሮቶች፣ ከቴክኖሎጂ ውጤቶችና መሰል ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ነው የተባለውን የፖሊሲ ሰነድ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!