በኦሮሚያ የፍርድ ቤቶች ትእዛዝ አለመከበሩ እንዳሳሰብው ኢሰመኮ አስታወቀ
ዶ/ር ዳንኤል በቀለ (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሽን ዋና ኮሚሽነር)
ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መባሱንም ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል
ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 25, 2021)፦ በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፍርድ ቤቶች ትእዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ መኾኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ዛሬ ሐሙስ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ መነሻ በጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በዋስትና ይለቀቅ የተባለ አንድ ግለሰብ እና ሌሎች በፍርድ ቤት በዋስትና መብት ይከበርላቸው ተብሎ ትእዛዝ ተሰጥቶ፤ ትእዛዙ መከበር ባለመቻሉ ነው።
እንደ ኮሚሽነሩ መግለጫ፤ በዋስ ይለቀቅ የተባለው ግለሰብ እስካሁን በእስር ላይ መቆየቱንና የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በመተላለፍ የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወረዳ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ሊለቅቀው እንዳልቻለ ገልጿል።
በፖሊስ ጣቢያው የዋስትና መብቱ ሊከበርለት ያልቻለው ሙሐመድ ዴክሲሶ የተባለው ግለሰብ፤ በዋስትና ይለቀቅ ተብሎ በፍርድ ቤት ተወስኖ የነበረው የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደነበር ታውቋል። ሙሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በጅማ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ምርቃት ዝግጅት ላይ በቀረበ ሙዚቃ ላይ ከዘፋኙ የድምፅ ማጉያ ተቀብሎ “ጃዋር መሐመድ ይፈታ”፣ “ፍትሕ ለሐጫሉ ሁንዴሳ” በማለት ባለሥልጣናት በተገኙበት የተቃውሞ ድምፁን በማሰማቱ ነው።
ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ አለመፈጸሙና ግለሰቡ ከእስር አለመለቀቁ እንዳሳሰበው የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሙሐመድ ዴክሲሶን ጨምሮ ሌሎች በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በአፋጣን እንዲለቀቁም አሳስቧል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪይ የሰጡት የኢሰመኮን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፍርድ ቤቶች ትእዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ በመኾኑ፤ አፋጣኝ ትኩረትና እልባት ይሻል” በማለት ተናግረዋል። የኢሰመኮን የዛሬውን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)