ኦሮሚያ፡ ሙሐመድ ዴክሲሶ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቅ ይገባል
በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትእዛዝ አለመከበሩ አሁንም አሳሳቢ ነው
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከየካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወረዳ 1 ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የሚገኘውን ሙሐመድ ዴክሲሶ በተመለከተ የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋስ እንዲለቀቅ ያሳለፈውን ውሳኔ በመተላለፍ፤ ከእስር አለመለቀቁ እንዳሳሰበው ገልጾ፤ ሙሐመድ ዴክሲሶን ጨምሮ ሌሎችም በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ አሳስቧል።
የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የተማሪዎች የምረቃ መርኀ ግብር የዩኒቨርሲቲው ተመራቂ በመኾኑ ታዳሚ የነበረው ሙሐመድ ዴክሲሶ፣ በዝግጅቱ ላይ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን በማስመልከት መፈክሮችን ማሰማቱን ተከትሎ፤ በፌደራል ፖሊሶች ተይዞ በጅማ ከተማ ወረዳ 1 ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩን ሙሐመድ ዴክሲሶ ለኢሰመኮ አስረድቷል።
ኢሰመኮ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እስረኛውን በጎበኘበት ወቅት እስረኛው ለኢሰመኮ እንደገለጸው፤ በዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት በዓል ላይ የዘፈን ፕሮግራም ሲጀመር በመድረክ ላይ ኾኖ ከሚዘፍኑ ሌሎች ተመራቂዎች ጋር እየጨፈረ እንደነበረና ከዘፋኙ የድምፅ ማጉያ ተቀብሎ ‘ጃዋር መሐመድ ይፈታ’፣ ‘ፍትሕ ለሐጫሉ ሁንዴሳ’ በማለት ድምፁን ማሰማቱን፣ የምርቃት ፕሮግራሙ እንዳለቀ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ፖሊሶች በግቢው ውስጥ ወዳለው ካምፕ እንደወሰዱትና ፖሊሶቹ በጥፊ እንደመቱት፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከዩኒቨርስቲው ግቢ ውጪ ወስደውት በዱላ ሁለቱን እግሮቹን እንደደበደቡት፣ በጎኑ አካባቢም እንደመቱት አስረድቷል። ሙሐመድ ዴክሲሶ አክሎም ለኢሰመኮ እንደገለጸው “በጅማ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ ፖሊሶች ለአንድ ሰዓት ያክል ካቆዩኝና ከደበደቡኝ በኋላ ወደ ጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱኝ። በፖሊስ ጣቢያው ከደረስኩ በኋላ ግን የተፈጸመብኝ ድብደባ የለም፣ ፖሊሶች የተጠረጠርኩበትን ወንጀል ካስረዱኝ በኋላ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ጅማ ከተማ ፍርድ ቤት ወስደውኛል” ብሏል።
ኢሰመኮ እስረኛውን በጎበኘበት የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ. ም. በእግሮቹ ላይ መጠነኛ እብጠት የሚታይ መኾኑንና የሚያነክስ መኾኑን ተመልክቷል። ይህንኑ መሠረት በማድረግ አስረኛው ሕክምና እንዲያገኝ ለፖሊስ ጣቢያው ምክረ ሐሳብ ተሰጥቶ መግባባት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢኾንም፤ እስከ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ሕክምና ያላገኘ መኾኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።
የጅማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ሙሐመድ ዴክሲሶ በብር 2000 (ሁለት ሺሕ ብር) የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ የወሰነ እና እስረኛውም አስፈላጊውን የዋስትና መስፈርት ያሟላ ቢኾንም፣ እስከ የካቲት18 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በእስር ላይ የሚገኝ መኾኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል።
ሙሐመድ ዴክሲሶ በተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የፈጸመው ተግባር ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ምናልባት ሊነቀፍ ወይም ሊያስወቅስ ከሚችል በስተቀር፣ ከመነሻውም ለወንጀል ክስና እስር ምክንያት ሊኾን አይገባም ነበር። ፖሊስ ወይም ዓቃቤ ሕግ በበቂ ምክንያት ሊያስከስስ የሚገባ ነገር አለ ብለው ካመኑም፣ ማስረጃዎችን አሰባስቦ ክስ ከማቅረብ ውጪ፤ ተጠርጣሪውን ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ወይም በምርመራ ሰበብ ለማሰር የሚያበቃ ምክንያት አልነበረም። ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቅ ከወሰነና የዋስትናው መስፈርት ከተሟላ በኋላ ወዲያወኑ ከእስር ሊለቀቅ ሲገባ፤ ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ወቅት ድረስ በእስር ላይ የነበረ መኾኑ የተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው። ስለኾነም ኢሰመኮ እስረኛው ሙሐመድ ዴክሲሶ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቅ የሚገባ መኾኑን እያሳሰበ፤ እስረኛው ወደ ጅማ ፖሊስ መምሪያ ከመወሰዱ አስቀድሞ በፖሊሶች ተፈጽሞብኛል ያለውን ድብደባ በተመለከተ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ኢሰመኮ ያሳስባል። በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል እስር ቤቶች የዋስትና መስፈርቶችን አሟልተው አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች ከእስር እንዲለቀቁ ኮሚሽኑ በድጋሚ ያሳስባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ጉዳዩን አስመልክቶ “በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፍርድ ቤቶች ትእዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ በመኾኑ አፋጣኝ ትኩረትና እልባት ይሻል” ብለዋል።