ቦጋለ ዳኜ - ከካሊፎርንያ

ለዶ/ር መስፍን አረጋ ሠላምታዬ ይድረሳቸው!

ዶ/ር መስፍን አረጋ ራማ ሉል በሚል ርዕስ ሰሞኑን በኢትዮሚዲያ ያወጡትን ጦማር አንብቤአለሁ። አማርኛን ብቁ የሳይንስ ማሰተማርያ ለማድረግ እንግሊዝኛን የሚተኩ ቃላት በራስ ቋንቋ ለመሰየም የሚያደርጉትን ጥረት አድናቂ ነኝ።

 

 

እስራኤሎች ሃብት፤ እውቀት፤ ሙሉ ፈቀደኝነትና ህብረት ስላላቸው ከነጻነታቸው በኋላ ወድቆ የኖረ እብራይስጥን በአጭር ጊዜ ውስጥ (አስር ዓመት ይመስለኛል) ለዩኒቨርሲቴ መማርያ አብቅተውታል። በአንጻሩ አማርኛ በዘመናዊ ትምህርት ማስተማርያነት ከአንድ ሰው ሙሉ እድሜ በላይ ቢያስቆጥርም ለሁለተኛ ደረጃ ማስተማርያ እንኳን እስካሁን አልበቃም።

 

ለመግቢያ ያህል ይህን ያህል ካልኩ፤ ‘ራማ ሉልን’ ወይም ሌሎች መሰል የዶ/ር መስፍን አረጋን ጦማሮች ያነበበ ሁሉ እሚለው እንደ ማያጣ ሁሉ እኔም የምለው አለኝ። ጸሐፊው ከዚህ በፊትም በተለያየ ጊዜ ተመሳሳይ ጦማር ማውጣታቸው ለዚህ ሥራ ምን ያህል እንደተጉ ያሳያል።በሳይንሱ በኵል ያላቸው ብቃት እንዳለ ሆኖ በስያሜ አሰጣጡ ም ብዙ ምርምር እንዳደረጉ ከጦማራቸው መረዳት ይቻላል። ከውጪው ቋንቋ በተጨማሪ ከአንድ በላይ ያገርኛ ቋንቋ መቻላቸውም የረዳቸው ይመስለኛል።

 

ዋናው ጥረታቸው በባእድ ቋንቋ ላለ መጠቀም በተቻለ መጠን ወይም ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ፅንሰ ሃሳቦችንና ስያሜዎችን (ተርሚኖሎጂዎችን) በአገርኛ ቋንቋ መተካት ሲሆን ይህንንም የሚያደርጉት በቃላት ሐረግ ሳይሆን ካስፈለገም ከአንድ በላይ የሆኑ አገርኛ ቋንቋ ቃላት ን ወይም ሆሄያትን በማጣመር አንድ ቃል በመሰየም ጭምር ነው። በዚህም ምክንያት የሴም ቋንቋ ከሆነውና የአማርኛ አባት ከሆነው ግዕዝ ተስማሚ ቃል ሲያጡ ከግእዝ ቋንቋ ብዙም ዝምድና ከሌላቸው አገርኛ ቋንቋዎች አገርኛ ስለሆኑ ብቻ ከኦሮምኛና ከወላይታ በመዋስ አንድ ቃል ሲቀርጹ ይታያል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ቃላቱን በቀላሉ ለመያዝ በውስጣቸው ያለው መነሻ ዘር ስለማይታወቅ ማሰታወስ ይቸግራል። ከአማርኛ ቋንቋ ሌላ የተባሉትን አሮምኛ ወይም ወላይትኛ ለማያውቅ ሰው ፤በተለይ ቃላቱን ከልጅነቱ ጀምሮ ላላጠና ሰው ማስታወሱ ይቸግረዋል።

 

ቋንቋዎች አንድን ሃሳብ ለመግለጽ የየራሳቸው ዘዬና መንገድ እያላቸው ይህን በመተው ቃል በቃል የመሰየም ሁኔታም ይታያል። ቃል የሚቀርጹትም ከአንድ ቃል የፈለጉትን ዘር ለመምዘዝ በሚያመቻቸው መልክ ነው ። የሚሰየመውም ቃል እንግዳ ከመሆኑም ሌላ አረባቡም ግራ የሚያጋባ ነው። ለምሳሌ “…ግሱም ሲረባ ፈለሸረ(become diaspora)፤ ፍልሸር፤ ፈልሸራ፤ ፍልሸራ እያለ ይሄዳል።” ይላል።(መስመር የተጨመረ ነው።) እሳቸው እንዳሉት ግሥ ብቻ ሳይሆን ግሡም ዘሩም የተደባለቀ ይመስላል። የማይዛመዱ ደባል ቃላቶች ስለገቡ አባትና ልጁም (ግዕዝና አማርኛ) ሊጣሉ ነው።

 

እንግሊዞችም ከሌሎች ማለት ከላቲን ወይም ከግሪክና ከመሳሰሉት የቋንቋ ቤተሰባቸው ታሪካዊ አመጣጣቸውን እየተከተሉ በመዋስ ነው ቋንቋቸውን ያበለጸጉት። እኛስ መሰል ቃል ሲጠፋ የተለመደውን ስም መዋሱ ምን ይከፋል? ተማሪው በትምህርት እየገፋ ሲሔድ በእንግሊዝኛ በተጻፉ መጻሕፍት መጠቀሙ ስለማይቀር እንግዳ አይሆኑበትም። ለማለት የፈለግሁትን ጥቂት ከጦማሩ እያጣቀስኩ ለማስረዳት ልሞክር።

 

*ራማዊ አካሎች (heavenly bodies) የግእዝ ቅጽል አንድና ብዙ ስለሚጠነቅቅ ራማውያን አካሎች ወይም ራማዊ አካል ማለት ያለበት ይመስለኛል።ራማ ማለት ሰማይ ነው --ሦስተኛው ሰማይ። ያ ከሆነ ራማ ከማለት የተለመደው ሰማይ አይሻልም? -- ሰማያውያን አካላት።

 

*ፊልጡፍ፤ እንደተረዳሁት ‘ፊልጡፍ’ የሚለው ቃል የተመረጠው እንግሊዘኛው (prefix) በቃል በቃል ትርጉሙ ፊት ለፊት ልጠፋን ስለሚየመለክት አማርኛው እሱን መምሰል አለበት በሚል እሳቤ ይመስለኛል። ‘ልጠፋ’ ባይኖርበትም የተለመደው የግዕዝ ቃል ‘ቅድመ ቃል’(prefix) [ለ‘ድህረ ቃል’ (suffix)] ጽንሰ ሃሳቡን ይገልጸው ይመስለኛል።

 

*ራቁት ዓይን (naked eye) ይህም ሌላው የቃል በቃል ትርጕም ነው። ለዚህ በአማርኛ የተለመደው ‘ባዶ ዓይን’ ስለሆነ ያማርኛውን አገላለጸ ቢከተል ይሻል ይመስለኛል።

 

*ቀያኒ፤ ቀያኒ ከያኒን ስለሚመስል ስያሜው ደስ ይላል። ይሁን እንጂ የግዕዙ ግሥ ‘ተቀንየ’(ቀንየ) ስለሆነ ቃሉም ሆነ አረባቡ አልመሰለውም። ግዕዝማ ያለተናጋሪ በመጽሐፍ ብቻ ለብዙ ዘመናት ስለኖረ ሌላ ቃል ሲገባበት አይወድም። በስተርጅና ቅኔዬን ለመከለስ በዓታ ቅኔ ቤት ገብቼ ነበር። አንድ ቀን “ …ድምፀ ዶርሆ ኩኩሉ።” የሚል ጉባዔ ቃና ቆጥሬ ለቅኔ መምህሩ ብነግር ‘ኩኩሉ’ ምንድን ነው ብለው ተቆጡኝ። የዶሮ ድምፅ ነው ብልም ደስ ስላላላቸው ቃሉን አውጥተው አረሙት።ግዕዝ ንግግርነቱ ከቆመ ጀምሮ እንደ ጥቅሶች ያሉ ለምሳሌ ‘ላማ ሰበቅታኒ’ ከእብራይስጥ፤ አምንስቲቲ ሙኪሪያ/ ሙዳ ሱዳ ከግሪክ ከመሳሰሉት በስተቀር ብዙም ቃል ያስገባው ወይም የቀነሰው የለም። በንግግር ላይ ያለ ቋንቋ በዘመን ሂደት በራሱ ብዙ ይለወጣል። ግዕዝ ግን እንደዚያ አይደልም። አማርኛ፤ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመግለጽ ከእንግሊዝኛ ከወሰዳቸው ቃላት በተጨማሪ በሂደት ከሕዝብ በመጣ ቃል መደባለቁ ያለ ነው። ከህዝብ የመጣን ማገድ አይቻልም። ለምሳሌ አምቦና ጉደር ብትሔዱ አንድን ሴት በልጆቿ ስም ለመጥራት ‘ሀደ እገሌ’ (የእገሌ እናት) ወንዱን ደግሞ ‘አባእገሌ (የእገሌ አባት) ማለት የተለመደ ነው። (በኦሮምኛ ‘ሀደ’ እናት ሲሆን ‘አባ’ አባት ነው።) ሌላ ምሳሌ ልጅ ጡት መጥባት አልተው ሲል ጡቱን የሚቀቡት አንድ መራራ ዕፅ አለ። የዕፁ ስም በኦሮምኛ ‘አርማ ቡሳ’ (ጡት አስጥል) ነው ። በአማርኛ ስሙ ስለማይታወቅ ይሁን ወይም በኦሮምኛው ቋንቋ ተፅእኖ አማሮችም ‘አርማቡሳ’ ሲሉት እሰማ ነበር።

 

ወደ ቀያኒ ልመለስና ዶ/ር መስፍን ከወላይታና ከኦሮምኛ ቃል መዋሳቸው ግድ ከሆነ ባለ ቅኔ ለማለት ‘ቀያኒ’ (poet) ከማለት ኦሮምኛው አንድ ቃል ‘ወለልቱ’ ስለሚገልጸው ለምን እሱን አልተጠቀሙም?

 

*ፈላሸዘር፤ ፈላሻ አማርኛ ሲሆን ‘ፈለሰ’ ግዕዝ ነው። የፈለሰ ትርጉም ተሰደደ፤ ፈለሰ ሲሆን ከሱም ፈላሲ፤ ፈላስያን ፍሉስ ፍሉሳን ፍልሰት የተባሉ ቅጽሎችና ዘሮች ይገኛሉ ።ቃል በቃል ባይሆንም ለ(diaspora) ፈላስያን፤ ፍሉሳን ግዩራን፤ መጻተኛ ወዘተ. እንደሁኔታው ቅጽሎቹ ስሞቹ እየተለዩ ሊጠቅሙ ይችላሉ።

 

*አብሔር፤በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው እግዚእ ጌታ ሲሆን ብሔር ዓለም ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር ማለት የዓለም ጌታ ማለት ነው። ቃሉም ለአብ፤ ለወልድ፤ ለመንፈስ ቅዱስ ይስማማል።አብሔር አብ፤ አብሔር ወልድ፤ አብሔር መንፈስ ቅዱስ ከማለት እግዚአብሄር አብ … እያለ ይሔዳል። አንድ ቀን ብድግ ብሎ ከዛሬ ጀምር የእግዚአብሔር ስም ስለረዘመ ‘አብሔር’ ይባል ቢባል ተቀባዮቹ ብዙ አይሆኑም። ማሳጠርም ካሰፈለገ ሕዝብ በራሱ ያሳጠረው ‘እግዜር’ ይበቃ ይመስለኛል። ስሙን መለወጥ ካሰፈለገና ሰሚም ከተገኘ እግዚአብሔር ብዙ ስሞች ሞልተውታል። ቀደምት አባቶች ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲተረጕሙ የዓለም ሁሉ ጌታ መሆኑን ለማሳየት ከሁለት ቃል መሥርተው የሰየሙት ይመስለኛል።

 

*ቅርበዛ፤ (approximately) ‘ነሲብ’ ይተካው ይመስለኛል።

 

*መዱስ፤በንግሊዘኛው ሙሉ ስሙ (The Holy Bible) ነው።ለማሳጠር Holyን ትተው ባጭሩBible ብቻ ይሉታል። በኛ ግን ቅዱስን ትተን ባጭሩ መጽሐፍ ብቻ ብንል ብዙ መጻሕፍት ስላሉ ከነሱ ለመለየት ቅዱስን መጨመር ግዴታ ነው። ስም ረዘመ ብሎ አይቀነስም።

 

*መዝቀል፤ ‘መዝገበ ቃልን’ (መዝገብ እና ቃል) ተናባቢ ስለሆነ ለያይቶ ከመጻፍ በጥቅልል ‘መዝገበቃል’ ቢባል ይመረጣል።

 

*ከላይ እንደ ምሳሌ እነዚህን ጠቀስኩ እንጂ ቃላቱ በርካቶች ናቸው። ምሳሌ፤

ሩፓይፋ telescope

ወልፈክ constant

ገድራሚ variable

ፈነገነ detect

በረበረ discover

ደክፋን pattern

ደበደ fix

ወነመነ assume

ፎቸክ model

ሱርፍክ figure ወዘተ.

 

እያንዳንዳቸው የየራሳቸው እርባታ ስላላቸው ሁሉን መዘርዘሩ አንባቢን ማሰልቸት ይሆናል። ሀሉም ለአማርኛ እንግዳ ቃል ነው የሆኑት።ለኔ ባገራችን በደቡብ አዲሰ ቋንቋ ለመፍጠር ከተሞከረው የወጋዱጉ ቋንቋ ጋር ተመሳሰለብኝ። ጸሐፊው ሁሉንም ባንድ ጊዜ ስለነገሩን መሰለኝ። ከነዚህ ከተዘረዘሩት እንግዳ ቃሎች ‘ደበደ’ ከኦሮምኛው ‘ዳበዳ( = ቁም/ቁሙ) የተመሰረተ ነው። እንደዚያም ሆኖ የ’ደ’ ሆሄ ድምፅ ለማለት የተፈለገውን የአሮምኛውን ድምፅ አይገልጸውም። ሌላ ፊደል መቅረጽ ሊያሰፈልግ ነው።

 

ልጅ ሆኜ ሰላሌ ውስጥ ከአንድ አማራ የቄስ ሚሰት፤ጋር በሆነ ጉዳይ ላይ በአማርኛ ስንጨዋወት ‘አንተሌ ምንም አትል’ አሉኝ።በኋላም ‘አንተሌ’ ምንድነው? ብዬ ሳሰላስል መልሱን አገኘሁት። ‘አንተ’ አማርኛ ነው ። ‘ሌ’ በኦሮምኛ ‘እንኳን’ ማለት ነው። ሴትዮዋ በኦሮሞ መካከል በዙ ዘመን በመኖራቸው በሁለት ቋንቋዎች ግጭት የተናገሩት ነው። ማለት የፈለጉትም ‘አንተ እንኳን’ ነው። ኦሮምኛው ‘አቲሌ’ ነው።እንደዚህ ለብዙ ዘመን የሚፈጠረውን ቃል መቀበል ላካባቢው ሰው አያሰቸገርም። ለነገሩ በኦሮምኛ አንተ ‘አቲ’ እኔ ‘አና’ ሲሆን ግዕዙም ‘አንተ፤ አነ ስለሆን ሁሉም አንድ ነው። አንድ ቃል ከየትም ይምጣ ሕዝብ ከለመደው ማሰተዉ ይቸገራል። ‘ካልሲ’ ከየትም ይምጣ የተለመደ ቃል ሆኗል። ከሰባ ከሰማንያ ዓመት በፊት አይታወቅም ነበር።

 

ሌላው አንድ እቃ ወይም ነገር ካንዱ አገር ወደሌላው ሲዟዟር ስሙን ይዞ መሄዱ ያለ ነው። መሰል ቃል ሲገኝ መተርጕሙ ጥሩ ነው። አለበለዚያ እንዲሁ እኛም በራሳችን ቃል ለውጠናል ለማለት ብቻ አዲስ ቋንቋ መፍጠሩ የባሰ መደነጋገር ያስከትላል። ለምሳሌ፤

 

ስኳር በግዕዙም ‘ሶከር’ ሲሆን በእንግሊዘኛም ‘ሹገር’ ነው።

 

ፈረስ በግዕዝም ፈረስ ነው። በኦሮምኛ ‘ፈርዳ ’ሲሆን በእንግሊዝኛ ‘ሆርስ ነው።

 

ውሻ በእንግሊዝኛ(በላቲን) canine ነው በወላይታም ‘ካናይ’ ይመስለኛል።

 

ስኳሩ ወይም እንስሳቱ መጀመርያ ከታዩበት ወደሌላው ሲሄዱ ስማቸውን ይዘው ሄደው ነው የሚል ግምት አለኝ። በዘመን ብዛትና ከቦታ ቦታ ሲዞር አንዳንድ ፊደል ተለውጦ ስሙ ተለውጦ ነው ብየ አስባለሁ።ታድያ መሰል ቋንቋ ካላገኘን አሁንስ ከነስሙ ብንወስድ ምን ችግር አለ? አንቴናን አንቴና ብንለው ምንድን ነው ችግሩ? ለምሳሌ በግዕዝ ‘አቅራብ’ ጊንጥ ነው። እንግሊዘኛውም crab ነው።ምናልባት በመጻሕፍት ትርጕማ ጊዜ ከግሪክ ወይም ከእብራይስጥ (በነሱም እንደእንግሊዘኛው ከሆነ) ተውሰውት ይሆናል። ወይም እነሱ ከኛ ወስደውት ይሆናል። ምርምር ባላደረግሁት ነገር ትክክለኛውን መናገር ስለማልችል ነው። ወይም እንዳባቶቻችን እምነት የመጀመርያው የአዳም ቋንቋ ግዕዝ ስለነበር መመሳሰሉ በዚያ ምክንአት ሊሆን ይችላል። እንግሊዞች ከኛ ጤፍን (teff) እንዳለ ወስደው በመዝገበ ቃላቸው ጨምረዋል። ቡናን (coffee) ብለው በከፋ ስም ሰይመውታል።እነዚህን ቃላት ከኛ መዋሳቸው ያስንቃቸዋል? ቀድሞም መዋዋስ ያለ ነገር መሆኑን ለማሳየት ነው። እንደ አማኝ ከህንፃ ሰናዖር በፊት ዓለምኮ አንድ ቋንቋ ነበራት። በተጨማሪ እስቲ እነዚህን የቃላት መመሳሰል ተመልከቱ፤

 

አማርኛ እንግሊዝኛ

ብሩህ bright

ሎሚ lemon

መተረ (ሜትር) meter

ዐይን eye

ምህረት mercy

ጋለበ gallop

ቂንጥር clitoris

ፈራ fear

ምስጢር mystery

ደረቅ dry

ሁሉ all

አየር air

ግመል camel

ን ? (ን ባማርኛም መጠየቅያ ነው። ምሳሌ በላህን

 

ሁላችሁም ብትሞክሩ በዚህ ዓይነት የሚመሳሰሉ ብዙ ቃላት ታገኛላችሁ። ባጋጣሚም ሆነ አንዱ ከሌላው ተውሶት እንደዚህ ያለው የቋንቋ መመሳሰል ደስ ነው የሚለኝ። ሊተካው የሚችል ቃል እያለ መዋሱንም አልፈልግም። አንድ ወዳጄ ከላይ የዘረዘርኩትን ዓይነት ቃላት ከዚህ በበለጡ ቋንቋዎች በማመሳሰል ያሰባስብ እንደነበር አሰታውሳለሁ። ምን እንዳደረሰው ወይም ለምን ጉዳይ እንደሚያሰባስብ ግን አላውቅም።

 

ሃሳቤን ለማጠቃለል የቋንቋ ነገር ሁሉንም ስለሚመለከት የድርሻዬን ሃሳብ ጣል ለማድረግ ነው እንጂ በመስኩ በቂ ዝግጅት ስለሌለኝ በጦማሩ ላይ ሙሉ ትችት ለመስጠት አይደለም።ሊዋጡልኝ ያልቻሉትን ብቻ እንደምሳሌ ጥቂቶቹን እየጠቀስኩ ብተችም ጸሐፊው እንደ ‘ፈለክ’ (planets) እንደ እመርታ (time interval) እንደ ነጻሪ (observer) ያሉትን ትርጕሜዎች በሚገባ በመሰየማቸው የሚመሰገኑ ናቸው። እነ ደስታ ተክለ ወልድ ያማርኛ መዝገበቃላት ቢጽፉ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ከመጻሕፍትም ከቃላቸውም አጠናቅረው መልክና ቅርጽ ሰጥተው ስርአት ባለው መልክ አዘጋጁ እንጂ የሌለ ቃል አዲስ ስያሜ እየሰጡ የጻፉት ስለሌለ በራሳቸው መጻፋቸው መልካም ነው።የዶ/ር መስፍን ግን አዳዲስ ስያሜ ሰላለበት ለቋንቋ አካዳሚ ጥሩ ግብአት ይሆናል እንጂ በራሱ እንዳለ ተቀባይነት ያገኛል አልልም። እሳቸው በተለይ በመልክዓ ምድር ስያሜያቸው ላይ ሰው ባይቀበለውም እኔ እንደዚያ መጥራቴን አልተውም ማለታቸው ምን ያህል በዚህ ነገር እንዳሰቡበት ይገልጻል። ቋንቋ ማለት ሁሉ የተስማማበት መሆኑንም ለመቀበል የፈቀዱ አይመስለኝም። ሁሉ ካልተስማማ ደግሞ እንደባቢሎኑ ዘመን መደማመጥ ይጠፋል።

 

ማሳሰብያ፤ ይህን ጦማሬን ‘ራማ ሉል’ በተጻፈበት በኢትዮ ሚድያ እንዲወጣ ከሳምንት በፊት ልኬው እስካሁን አልተለጠፈም። የተለየ ሃሳብ ለማሰተናገድ ባለመፍቀድ ይሁን ወይም ጸሐፊው ላወጡት ጦማር አይመጥንም በሚል፤ ምክንያቱን ባላወቅሁት ነገር አልወጣም። ጸሐፊው ሁሉም እንዳቅሙ የየራሱን ቢል ቋንቋ የጋራ ስለሆነ የሚከፉ አይመስለኝም። ለኢትዮሚዲያ ከላክሁት በኋላ ስላላረፍኩ ከዚያ በኋላ ጥቂት የጨመርኩት አለ። ከእንግዲህ በኋላ ባያወጣው ይሻላል። ካወጣውም ልዩነቱ በዚህ ምክንያት መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።


ቦጋለ ዳኜ

 

ከካሊፎርንያ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!