TPLF

ትሕነግ/ሕወሓት

ወረራውን ለመቀልበስ ጥሪ ተላልፏል

ኢዛ (ማክሰኞ ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 13, 2021)፦ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ በኢትዮጵያና በአማራ ሕዝብ ላይ መሠረተ ሰፊ የኾነ ወረራና ወታደራዊ ጥቃት ማድረግ መጀመሩን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አሁን ማምሻውን (ማክሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.) ከአማራ ክልላዊ መግሥት የወጣው መግለጫ፤ “ይህ አሸባሪ ቡድን የጀመረብንን ግልጽ ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያወዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን እንደሚቀጥል ፍጹም ጥርጣሬ የለንም” ብሎ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንዲያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ በዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛ እና የቅርብ ተጠቂ መኾኑንም በመግለጫው አመልክቷል።

በመኾኑም ለሕዝባችን ሕልውና እና ለአገር ሉዓላዊነት መኾኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላቶቻችንን እንድንፋለም ጥሪ እናቀርባለን ብሏል። የክልሉ ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

"አንድነታችንን ጠብቀን ያጋጠመንን የሕልውና አደጋ በትግላችን እንቀለብሰዋለን” የአማራ ክልል መንግሥት

የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ጠላት የኾነው ትሕነግ ወያኔ እንደአገር ባደረሰብን ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል እንዲሁም ለፈጸመብን አገራዊና ሕዝባዊ ክህደት የአገራችንን የግዛት አንድነት በመሸርሸር ሉዓላዊነቷ የማይከበር፣ ራሷን ችላ መቆም የማትችልና በሁሉም መስክ ተንበርካኪ አገር ባለቤቶች እንድንኾን በርካታ ደባ ፈጽሞብናል። በዓለም አደባባይ የምንኮራበት አገራዊና ሕዝባዊ የጋራ ታሪክ ባህልና እሴት እንዳይኖረን፤ አንድነታችንንና አብሮነታችንን በፈጠራ ታሪክ እየቦረቦረ እርቃናችንን እንድንቀር፤ አንዳችን ለሌላችን ጋሻና መከታ መኾን ሲገባን እርስ በእርስ በመጠራጠር አውሎ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንድንላጋና በጠላትነት እንድንፈራረጅ ከሰማይ በታች ያልፈጸመብን ግፍ የለም።

ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተባብረንና ተፈቃቅደን የፀረ ጭቆና ትግሉን አንድ ብለን ስንጀምር በጋራ ያነሳነው የፍትሕና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ በትሕነግ መንደር የቱን ያህል መራር የኾነ የመደፈር ስሜት እንደፈጠረ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። አሸባሪው ትሕነግ ከመንበረ ሥልጣኑ ተምዘግዝጎ ሲወድቅና መቀሌ ሲከትም የነበረው ብቸኛ ምክንያት ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ የሚል ፖለቲካዊ ቁማር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

በውሁድ ፓርቲ ደረጃ የተፈጠረውን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት የአህዳውያን ውጤት አድርጎ ያበሻቀጠው ፍላጎቱ፤ በለመደው የአድራጊ ፈጣሪና የአዛዥነት ሚና ያልተሳተፈበትን መዋቅር ለማጣጣል ከማለም ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተጠቃሚነት ባለው ከፍ ያለ ንቀትና ጥላቻ ምክንያት መኾኑ ለሁሉም ግልጽ ነው። ይህንን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ እንዳይንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ የልብ ልብ ሰጥቶት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውድ ልጆችን በግፍ ያለርህራሄ አሰቃቂ ግድያ ከፈጸመባቸው በኋላ የዕዙን ጠቅላላ ንብረት በመውረስ በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ማወጁ ይታወቃል። የአማራ ክልልን ወሰን ጥሶ በማለፍ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም በማይካድራ ንጹሐን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋ የሚዘነጋ አይደለም። ይህንን ተከትሎም መንግሥት በየደረጃው የሕግ የበላይነት ለማስከበር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል። በሒደቱም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸው የሚዘነጋ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ አረመኔና አሸባሪ ቡድን ዓይኑን በጨው አጥቦ ጥቃት የተፈጸመበት በማስመሰል ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በማጭበርበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ መሠረተ ሰፊ የኾነ ወረራና ጥቃት ማድረግ ጀምሯል። ይህ አሸባሪ ቡድን የጀመረብንን ግልጽ ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያወግዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፍጹም ጥርጣሬ የለንም። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ መኾኑን ነው። ስለኾነም ትግላችን ለሕዝባችን ሕልውናና ለአገር ሉዓላዊነት መኾኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ አረመኔና ጨካኝ ቡድን መኾኑ እንዲታወቅና ሁሉም የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከሕልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተውና ከዚህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ጋር ቀጣይ የምናደርገው ሁሉ አቀፍ ትግል የሕልውና ትግል መኾኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሕይወት መሥዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እንዲጠባበቅ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

አሸባሪው ትሕነግ የትግራይን ሕዝብ ከሕጻን እስከ አዋቂ በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግጋትን በመቃረን ሕጻናትንና ሴቶችን በጅምላ ጦርነት እየማገደና ያለ የሌለውን አቅሙን ተጠቅሞ ክልላችን ላይ ወረራ የፈጸመ ሲሆን፤ በተለይም ለዘመናት የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሑመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ አሁናዊ ሙከራ የጀመረ መኾኑ በአካባቢው የሚኖሩ አማራዎችንና የአማራ ክልል ተወላጆችን ፈጽሞ የማጥፋት ሕልሙን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ስለኾነም ይህንን አረመኔያዊ ድርጊትና ዳግም ወረራ የክልሉ መንግሥት በፍጹም የማይቀበለውና በጀመርነው የሕልውና ትግል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን የምናረጋግጥ መኾኑን አበክረን እንገልጻለን።

ስለኾነም፡-

1ኛ. በየግንባሩ የምትገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልላችን ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት፣ ሕዝባዊ ፖሊስና ሰላም አስከባሪ አባላት እንዲሁም አገርና ሕዝብን ለማዳን የተግባር እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ የምትገኙ የየክልሉ የጸጥታ አካላት በዚህ ታሪካዊ መድረክ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ለአገራችሁ ሉዓላዊነትና ለሕዝባችሁ ሕልውና የምትከፍሉትን ክቡር መሥዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው ይኖራል። በቀጣይም የተሰጣችሁን ሕዝባዊና አገራዊ ተልዕኮ በጽናትና በቁርጠኝነት እንደምትወጡ እምነታችን የጸና ነው። ስለኾነም መላው የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ከጎናችሁ መኾኑን አውቃችሁ በጀግንነት ታሪካዊ ጠላታችንን በመደምሰስ ለአገራችሁ ዳግም የኩራት ምንጭ እንድትኾኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

2ኛ. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትሕነግ ወያኔ ላይ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ርብርብ ሁሉ ማድረግ አለበት ብለን እናምናለን። አሸባሪው ትሕነግ አገር ከማፍረስ እኩይ ተልዕኮው ሊታቀብ የሚችለው የአገራችንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በጽናትና በዓላማ ቁርጠኝነት በጋራ መጠበቅ ስንችል ስለኾነ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ በጋራ እንድንቆም የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

3ኛ. በየትኛውም ዘመን ሠልጥናችሁ፣ የአገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በማንኛውም የመንግሥት ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ተሰልፋችሁ ስታገለግሉ የቆያችሁና በታሪክ አጋጣሚ የሙያ ዘርፍ የቀየራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች ለሕልውናችን የምናደርገውን የትግል ጥሪ ተቀብላችሁ በክልሉ ጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እያቀረብን ከዛሬ ጀምሮ በየአካባቢያችሁ ሰላምና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት በአካል ተገኝታችሁ በፈቃደኝት እንድትመዘገቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።

4ኛ. መላው የክልላችን ወጣቶች ከፊት ለፊታችን የተደቀነብንን የሕልውና አደጋ ያለበቂ ዝግጅትና ደረጃውን ከጠበቀ ስልጠና ውጭ የምንጋፈጠው አይደለም። ስለኾነም ከማንኛውም ግብታዊ እንቅስቃሴ ታቅባችሁ በየደረጃው ለሚኖረው ምልመላና ስልጠና በመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጋችሁ የመንግሥትን ጥሪ እንድትጠባበቁ እናሳስባለን።

5ኛ. መላው የክልላችን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች የጀመርነው የሕልውና ትግል የሁላችንንም አንድነት፣ ህብረትና ተቀራርቦ መሥራት የሚጠይቅ ነው። በሩቅ ኾኖ ስህተት በመፈለግና እርስ በርስ በመነቋቆር ከጠላት መንጋጋ ፈልቅቀን የምንታደገው አንዳችም ሕልውና የለንም። በቂ መረጃ ባገኘንበትም ባላገኘንበትም ጉዳይ ላይ ተሳፍረን በተለያዩ አቅጣጫዎች መክነፍ ለጠላቶቻችን ተጨማሪ ጉልበት ከመኾን ባለፈ ለሕዝባችን የሚሰጠው ጥቅም የለም። ስለኾነም የጋራ ዕጣ ፋንታችንን በጋራ ጥረት የምናስከብርበትና አደጋ የተጋረጠበትን የሕዝባችንን ሕልውና ከጠላት ጥቃት የምንታደግበት የታሪክ መድረክ ላይ ስለምንገኝ ከመቸውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው የሕዝባችንን አንድነት ጠብቀን በጋራ እንድንረባረብ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

6ኛ. መላው የክልላችን ሕዝብ፣ በከተማና በገጠር የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎች፣ በአገር ውስጥም ኾነ ከአገር ውጭ የምትገኙ ምሁራንና የክልላችን ተወላጆች፣ በተለያየ ሙያ ተሰማርታችሁ አገርና ሕዝብ በማገልገል ላይ የምትገኙ የክልላችን ነዋሪዎችና ባለሀብቶች የጀመርነውን የሕልውና ትግል በማገዝ የትግል ሒደት አዎንታዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም የጀመርነው ትግል እልህ አስጨራሽ በጣም መራርና ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ እንደሚኾን ይጠበቃል። የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ የእኛ አንድ መኾንና ለጋራ ግብ በጋራ መተባበር በመድረኩ አሸናፊ ኾነን እንደምንወጣ ያለምንም ጥርጥር ልናረጋግጥልችሁ እንወዳለን። ሁልጊዜም ቢኾን የአማራ ክልል ሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ተጠቃሚነት ውጭ እንደማይሳካ ጠንቅቀን እናውቃለን። የምናደርገው ትግል ለአገራችን ሉዓላዊነት መከበርና የጭቁን ሕዝባችን የሕልውና ትግል እንጂ እላፊ ጥቅም ለማግኘት የምናደርው ትግል በፍጹም አይደለም።

የአማራ ሕዝብ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ከእብሪት ይልቅ ድርድርን የሚያስቀድም በፍትሕ ከሄደች በቅሎየ ያለፍትሕ ያጣኋት ጭብጦየ ትቆረቁረኛለች ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው። ስለኾነም ዛሬ የምናደርገው ትግል ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው የኩራትና የክብር ምንጭ እንደሚኾን አንጠራጠርም። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የወሰደው ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ የጠላት ኃይል አገርና ሕዝብ ለማዋረድ የሚያደርገውን እብሪተኛ እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት እናሳስባለን።

ትግላችን ለሕልውናችን!

ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ