ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

ታሪካዊው የጎንደር ሰልፍ / People in Gonder are protesting against Ethiopia's ruling party and land grabs, 31 July 2016.

ነፍጠኛነት ባህላችን ነው፤ ፖለቲከኛነት አዲስና ባዕድ የትግል ዘዴ ነው፤ ፖለቲከኛነትና ነፍጠኛነት ተቃራኒ ተግባሮችን ያመለክታሉ፤ ተቃራኒ ተግባሮች አብዛኛውን ጊዜ ተቃራኒ ዘዴዎች ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ መፍጨትና ማቡካት ተቃራኒ ተግባሮች ናቸው፤ መፍጨት ሲበታትን፣ ማቡካት ሰብስቦ ያያይዛል፤ የሚፈጭ ሰው ማቡካት ይችላል፤ እንዲሁም ማቡካት የሚችል ሰው መፍጨት ይችላል። ፈጪ አቡኪ መሆን የሚችለውን ያህል ወይም አቡኪ ፈጪ መሆን የሚችለውን ያህል፤ ነፍጠኛ ፖለቲከኛ ወይም ፖለቲከኛ ነፍጠኛ መሆን ይችላል ወይ? መልሱ ግልጽ ነው፤ አይችልም። የነፍጠኛ ትግል በጠመንጃ ነው፤ የፖለቲከኛው ትግል በቃላት፣ በንግግር ነው። በሌላ አነጋገር የነፍጠኛ በዱላ፣ የፖለቲከኛ ትግሉ በመላ ነው።

የፖለቲካ ሥልጣንን ነክሶ ይዞ ህዝብን በህዝብ በዱላ እያደባደቡ በማሸነፍም ሆነ በመሸነፍ የሥልጣንን ክብር ማግኘት በጭራሽ አይቻልም፤ በዱላ ትግል በሁለቱም ወገን ያሉ ወጣቶች ይጎዳሉ። በተሸናፊው በኩል የተሰለፉ ወጣቶች የመረረ ኑሮአቸውን የሚጀምሩት ወዲያው ነው፤ መቃብራቸውም ሆነ ቁስላቸው ክብር የለውም፤ የየግሉ አበሳና ለቅሶ ሆኖ ይቀራል።

በድል አድራጊው በኩል የተሰለፉ ወጣቶችም ቢሆኑ ማርና ወተት የሚያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ አብዛኛዎቹ ያለ ማጋነን ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ጠመንጃ ተሸክመው በወገናቸው ደረት ላይ ሳንጃ ደቅነው እየወጉና እያሰቃዩ በየዕለቱ ከርሳቸውን ለመሙላት ያለፈ ኑሮ የላቸውም፤ ወይም እውነቱን ፍርጥ አድርጎ ለመግለጽ ዘጠና ከመቶ የሚሆነው ከአሸናፊው ወገን ያለ ወጣት አሥር ከመቶ ለሚሆነው አሽከር ወይም ሎሌ ሆኖ ወገኑን በስቃይ እየጠበሰ ለሆዱ የሚያድር ይሆናል ማለት ነው።

አብዛኛውን አሸናፊንም ሆነ ተሸናፊውን የሚያዋርደው ወይም ክብርን የሚነሣው የአሸናፊና የተሸናፊ ትግልም ሆነ የትግሉ ውጤት ከአብዛኛው የሀገሩ ህዝብ ፈቃድ ውጭ የተደረገ የጉልበተኞች ግብግብ ነው። እንዲህ ያለ ግብግብ የሚደረገው ከህዝቡ ጋር ሳይሆን በህዝቡ ላይ ነው፤ ሁለቱም ተደባዳቢ ወገኖች የህዝብ ወገን መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ሆኖም ተፎካካሪዎቹ እርስ በርሳቸው የሚታገሉት በዱላ እንደሆነ ሁሉ ከህዝብም ጋር ያላቸው ግንኙነት በዱላ ነው። የሁለቱም መሠረታዊ እምነትም ሆነ ዓላማ፣ መሣሪያም ሆነ ዘዴ ዱላ ብቻ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዴ ዱለኛነታቸው ድንበር እየጣሰ የሌሎች ሀገሮችን ሉዓላዊነት ይነካል። በዛሬው ጊዜ በዓለም ውስጥ ዋና ዱለኛ ሀገር አሜሪካ ነው፤ በሱ ጥገኝነትና በሱ ጥላ ስር ያሉ አምባ-ገነን አገዛዞች በበኩላቸው ዱለኛነትን ይለምዳሉ።

የህዝብን የገነፈለ ዓመጽ ከዱለኛነት ጋር እንዳናዛምደው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ አንድ ህዝብ በማይሰማ ደነዝ አገዛዝ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሲቆይ ተደብቆ የነበረው ሁሉ ገሀድ ይወጣል፤ በእንግሊዝኛ አንድ የአነጋገር ፈሊጥ አለ፤ የግመሉን ወገብ የሰበረው ሰንበሌጥ ይባላል (the straw that broke the camel’s back)፤ ሰንበሌጥ በእውነት የግመልን ወገብ የመስበር አቅም ኖሮት አይደለም፤ ነገር ግን ጭነቱ ተከምሮ፣ ተከምሮ በመጨረሻ የግመሉ ወገብ ሊሸከመው የማይችለው ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚጨመር ሰንበሌጥ የተከመረውን ሸክም ከመጠን በላይ ያደርገውና የግመሉን ወገብ ይሰብረዋል።

አበሳና ግፍም ከዓመት ዓመት እየተከመረ፣ ኑሮ እየከረረ፣ ከሞት ይልቅ ስቃይ እየመረረ፣ የግመሉን ወገብ እንደሰበረው ሰንበሌጥ ለዘመናት በህዝብ ላይ በተከመረ ግፍ ላይ አንድ ግፍ ጣል ማድረግ የግፍ ግንፋሎትን ይፈጥራል፤ ትእግስት ይደርቃል፤ ጨዋነት ዋጋ ያጣል፤ እንኳን ሰው ድንጋይም ይገነፍላል። እሳተ ገሞራ የሚባለው በመሬት ውስጥ ያለው ድንጋይ ሙቀት ሲበዛበት እየቀለጠ መሬትን ሰንጥቆ ሲገነፍል ነው። ህዝብም እንዲሁ ነው፤ ግፍ ሲበዛበት፣ ዙሪያው ገደል ሲሆንበት ይገነፍላል!

መገንፈል በሞት ውስጥና በሞት መሀከል መተራመስ ነው፤ ልዩ ኢላማ የለውም፤ በመንገዱ ላይ የሚያገኘውን ሁሉ ይጠብሳል፤ ሃሳብም፣ ስሜትም የለበትም፤ ንዴት ብቻ ነው፤ አደጋውም ያለው እዚያ ላይ ነው።

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

ሐምሌ 2008 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ