ተስፋዬ ገብረአብ

ታሪካዊው የጎንደር ሰልፍ / People in Gonder are protesting against Ethiopia's ruling party and land grabs, 31 July 2016.

እነሆ! በቅፅል ስሙ "አምባሻው" ተብሎ የሚታወቀው "የኢትዮጵያ ባንዲራ" ባለፈው ሰንበት ማለትም ሐምሌ እሁድ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. (ኦገስት 31፣ 2016) ቄሶችና ሼኮች በተገኙበት፣ መቶ ሺህ በሚገመት ህዝብ ሸኚነት የቀብር ሥነሥርዓቱ በበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ተፈመ ማለት ይቻል ይሆን? "ምነው ተኛ?" በሚል በሐሜት ድቅቅ አድርገን እንደ ክትፎ ስንከትፈው የሰነበትነው የአማራ ህዝብ ተደራጅቶና ተዘጋጅቶ፣ የቴዎድሮስን ከተማ ሲያንቀጠቅጣት ዋለ።

መንጌ ቴክሱ እንዳለው፣ "በርግጥ አማራ አለ?" እያልን ስናጠያይቅ ሰንብተን ነበርና፤ ክስተቱ አነቃቂ ለመሆን በቅቷል። በቅርብ ከማውቃቸው የOLF ጓደኞቼ ጋር ቡና እየጠጣን የጎንደሩን የተቃውሞ ሰልፍ በትኩረት ተከታተልነው። ከሁለቱም ብሔሮች ጋር ባንድ ጊዜ መጋጨት እንደማያዋጣው ያወቀው ወያኔ ጥይት ሳይተኩስ የተቃውሞ ሰልፉ ተጠናቀቀ። ሰልፈኞቹ የያዟቸው መፈክሮች አነጋጋሪ ነበሩ።

· በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ የሚካሄደው ግድያ ይቁም!
· ስብሃት! ኢትዮጵያ አትፈርስም። በመቀበሪያችሁ ዋዜማ ላይ ናችሁ!!
· ወልቃይት ብረሳሽ አጥንቴ ይርሳኝ! እስረኞች ይፈቱ!!
· ወያኔ እንጂ ወልቃይት የሻዕቢያ ተላላኪ አይደለም!!
· የህወሓት የበላይነት ይቁም!
· የታገልነው ትግሬ ለመሆን አይደለም!!
· አማራ አሸባሪ አይደለም!!

ባንዲራ የለበሱ ጦረኞች እና ጎራዴኞች በሰልፉ ላይ በብዛት ይታዩ ነበር። የጎንደር አማራ በሰልፉ ላይ በቁጣ ታየ። 25 ዓመታት በተለየ መልኩ የወያኔን ንቀት ተሸክሞ የኖረው ጎንደሬ "አሁንስ በቃኝ!" ሲል ተሰማ። "ተከዜን ትግሬ እንጂ ትግራይ ተሻግሮት አያውቅም" ሲል ቅኔውን መዠረጠው። "አማራ ፈሪ ነው" የሚለውን የነ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ሽሙጥ የሚያከሽፍ እምቢታ ታየ። የጎንደር ተቃውሞ ለወያኔ ራስ ምታት የሚሆነው ግን አምባሻው ባንዲራ ተወግዶ፤ ነባሩ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጎንደር ከተማ ላይ ሲውለበለብ መዋሉ ነበር። ከፊሉን ጥያቄ ወያኔ አምኖ መቀበሉ መደናገጡን ይጠቁማል። ወያኔ አምኖ የተቀበለው "የህወሓት የበላይነት ይቁም!!" የሚለውን ሲሆን፤ ይህ ጥያቄ የብአዴን አባላት ነባር ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ ነው። ከአመጹ ጀርባ የአንዳንድ የብአዴን አመራር አባላት ትብብር ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠሩ አለምክንያት አይደለም።

ጎንደሬዎች ከጥንት ጀምሮ የሚታወቁባቸው ጥቂት ስንኞች አሉ።

እንዲህ ጨሶ ጨሶ - የነደደ እንደሆን
የአመዱ መጣያ - ስፍራው ወዴት ይሆን?

ወገራ አሳላፊ - ደንቢያ እንጀራ ጣይ
ተበላህ ጎንደሬ - አትነሳም ወይ?

በትናንቱ የጎንደር አመጽ ደግሞ አዲስ ግጥም ተፈጥሮ አድሯል፣

ከባልንጀራው - ማታ የተለየ
የአበሻው ሰንደቅ - ጎንደር ላይ ታየ

የጎንደር የሰንበት ውሎ በኢሳት ቴሌቪዥን (ESAT) እና በሶሺያል ሜድያዎች ሲዘገብ ውሏል። ወያኔም ማታ በሁለት ሰዓት ዜናው ሳይወድ ተገዶ ሰልፉን ከነቅሬታው በቴሌቪዠን አሳይቷል። "የጎንደር ህዝብ አምባሻውን ባንዲራ ትቶ፤ አበሻውን ባንዲራ ማውለብለቡ ሕገመንግሥቱን የጣሰ ነው" ሲሉም ተናገሩ። ለመሆኑ ህዝቡ አምባሻውን ባንዲራ ካልፈለገ ለምን ይገደዳል? ወያኔ ራሱም አንብቦት የማያውቀውን ሕገመንግሥት በተመቸው ጊዜ ብቻ እያገላበጠ ይጠቀምበታል። የOLFን ባንዲራ በመላ ኦሮሚያ ማውለብለብ ስጋት መሆኑ በቀረበት በዚህ ዘመን፤ ወያኔ "አረንጓዴ - ቢጫ - ቀይ ባንዲራ አታሳዩኝ" እያለ አለቃቀሰ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሕብረቱ ጦር ወደ በርሊን ሲገሰግስ ሂትለር ተቆጥቶ፣ "በርሊንን እንኳ አናስነካም" ስለማለቱ ይወሳል። ወያኔ በኦሮሚያ በዝረራ ተሸንፎ፣ አሁን ደግሞ ጎንደርን ለቆ ወደ ተከዜ ሲያፈገፍግ፤ "ትግራይን እንኳ አናስነካም" የሚል መሰለ። ጊዜ ሲከዳ ብብት ይጋለጣል። በዘመነ ደርግ "ከተማ ሲያረጅ ደሴን ይመስላል" የሚል አባባል ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ መንግሥት ሲያረጅ ለማየት በቃሁ።

ከዚህ በኋላ የወያኔ ሥርዓት ያበቃለት መሆኑን ለመተንበይ ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልግም። የኦሮሚያ አመፅ በየአቅጣጫውና በየዕለቱ ስለሚፈነዳዳ ዜና መሆኑ እንኳ እየቀረ ሄዷል። ወያኔ ከመዳከሙ ብዛት የአዲሳባን ቆሻሻ እንኳ የሚጥልበት ቦታ ተቸገረ። "ድንገት ትግራይ ሪፖብሊክ የሚቋቋም ከሆነ በአማራና በኤርትራ መካከሉ ላይ እንዳንጨፈለቅ የሱዳን ድንበር ያስፈልገናል" በሚል ከአማራ ክልል ቆርጠው የወሰዱት የወልቃይትና የሁመራ መሬትም ይኸው አደጋ ላይ ወደቀ።

ሥርዓት ሲያረጅ ሁሉም ነገር ቀስ በቀስ ከእጅ ይሾልካል።

ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ገብቶታል። የወያኔ ሥርዓት እንዳለቀለት አሳምሮ ገብቶታል። ስጋትም ሰንጎ ይዞታል። ማለትም ወያኔ ከወደቀ የሚመጣው መንግሥት ስሙን ከወንጀለኞች ተርታ እንዳይፅፈው ሰግቷል። በቅርቡ የለቀቀውን መጣጥፍ የሚያነብ ይህንኑ በቀላሉ መረዳት ይችላል። መጪው መንግሥት ጄኔራሉን ጠርቶ፣ "የራያ ቢራ ፋብሪካን የገነባኸው ገንዘቡን ከየት አምጥተህ ነው?" ብሎ እንዲጠይቀው አይፈልግም። "የደቡብ ሱዳን መንግሥት የጦር መሣሪያ ሲገዛ ደላላ ሆኜ ያገኘሁት ገንዘብ ነው" ብሎ ለማሳመን ስለመቻሉ እርግጠኛ አይመስልም። ጄኔራል ፃድቃን ከግል ስጋቱ አንፃር ጭምር የህወሓትን ግማሽ አካል ከመሞት ለማዳን ቢነሳሳ አይደንቅም። የህወሓት ሰዎች ያለምንም ግርግር ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡ ከሆነ ግን፤ የያዙትን ይዘው የግል ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ መተው ይሻላል። ቂምን በቂም መመለስ አንድ ቦታ ላይ ካልተቋረጠ አዙሪቱ መቸም ቢሆን ማቋረጫ አይኖረውም።

ትናንት ያገኘሁት የውስጥ መረጃ እንደሚጠቁመው በጎንደር አመጽ ምክንያት ማምሻውን የተወሰኑ የህወሓት ሰዎች አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበው ሲመክሩ ነበር። ነገሩ እንኳ ትልቅ ጉዳይ አይደለም። ብቻ በውይይቱ ላይ፣ "በኃይለማርያም በኩል በተዘዋዋሪ ሀገሩን መምራት አልተቻለም። ኃይለማርያም ተወግዶ አንድ ጠንካራ የኛ ሰው በቀጥታ አመራር ቢሰጥ ይሻላል።" የሚል አሳብ መነሳቱ ነው። ከጎንደር አመጽ ጋር በተያያዘ የብአዴን አመራር አባላት ከአርበኞች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል መጠርጠራቸውም ሌላው ነጥብ ነው።

በመጨረሻ "ቀጥሎ ምን ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ይነሳል።

ጄኔራል ፃድቃን በቅርቡ ለንባብ ባበቃው ጽሁፉ ያቀረበው "ይሆናል" (Scenario) ሃሰት አዘል ስህተት ነው። ለአብነት "የኦሮሞ አመጽ መቆሙ" ሲል ይገልፃል። መቼ ቆመ? በመቀጠል ደግሞ፣ "የወያኔ ችግር ሕገመንግሥቱን አለማክበሩ ነው" ይላል። ለመሆኑ በዓለም ላይ መጥፎ ሕገ መንግሥት የፃፈ አለ እንዴ? እናወዳድር ቢባልስ ከወያኔ ያልተሻለ ሕገመንግሥት ማግኘት ይቻላል? የደርግ ሕገመንግሥትም እኮ የመናገርና የመፃፍ መብትን ይፈቅድ ነበር። አንድ መንግሥት ከሕገመንግሥቱ አንድ ነጥብ እንኳ ከጣሰ ማድረግ ያለበት በሚቀጥለው ቀን ከሥልጣን መውረድ ብቻ ነው። ጄኔራል ፃድቃን ግን ሃያ ዓመታት ሙሉ ሕገመንግሥቱን ሲጥስ የነበረው ሥርዓት እንደገና አዲስ የሽግግር ሥርዓት እንዲዘረጋ ዕድል እንዲሰጠው ይመክራል።

ዞረም ቀረ "ቀጥሎ ምን ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ከፊታችን አለ።

በጎንደር የተጀመረው አመጽ ወደ ባህርዳር እና አዲስ አበባ ሊስፋፋ የመቻል ዕድሉ ሰፊ ነው። የኦሮሚያ ወጣቶች በተለያየ ስልት አጻቸውን ይቀጥላሉ። የአዲሳባ ቆሻሻ ወደ ኦሮሚያ እንዳይደፋ ከልክለዋል። የወያኔ አውቶብሶችን ከማቃጠል ድርጊቶች ባሻገር፤ ሌላም አይነት እንቅፋቶች መፍጠሩ ሊቀጥል ይችላል። ምናልባት ቀጣዩ እርምጃ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ውሃ እንዳታገኝ ቧንቧዎችን መቁረጥ ሊሆን ይችላል። እንዲህ በአመጽ እየተናጠ የሚሄደው ሥርዓት የመጨረሻ ዕድሉ ሀገሪቱን አዘረክርኮና ለሕገወጥ ተግባራት አጋልጦ መውደቅ ነው።

ከመውደቁ በፊት ግን ወያኔ አንዳንድ ሙከራዎችን ማድረጉ አይቀርም።

ለአብነት ወያኔ በራሱ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሊያካሂድ ይችላል። ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ቤተመንግሥት ሊገባ ይችላል። ፃድቃንም ተመሳሳይ ነገር ቢመኝ አያስደንቅም። መቸም ሳሞራና ፃድቃን ሀገር ለመምራት ከመንግሥቱ ኃይለማርያም አያንሱም። መንግሥቱ ምናልባት በሀገር ፍቅር ስሜቱ ሊበልጣቸው ይችላል። "ቢወዳት ነው ቢጠላት አንቆ የገደላት?" እንዲሉ።

መሰንበቻውን የወያኔ የጎበዝ አለቆች ንብረት ወደ ትግራይ ሲያጓጉዙ እንደነበር ሲሰማ ቆይቷል። በተለይ ሰነዶች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ጥቆማ አለ። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የጦር መሣሪያዎች በአብዛኛው ትግራይ ናቸው። ለአብነት በመሃል ሀገር የተተኳሽ ማከማቻ መጋዘን የለም። ውቅሮ ተራራ ስር በተቀበረ ዋሻ ውስጥ ይገኛሉ። የደብረዘይት አየር ኃይል ቀፎውን ከቀረ ዓመታት አልፈውታል። ክምችቱ መቐለና አክሱም ነው። የህወሓት ደጋፊዎች የሰሯቸው ህንፃዎች በአብዛኛው በባንክ ብድር በመሆኑ ጥለው ለመሄድ አያሳስባቸውም ይሆናል። ቤተሰባቸውን ማሸሸት ከጀመሩም ሰነባብተዋል።

እንግዲህ የአዲሳባ ነገር የማያዋጣ ከሆነ የወያኔ ሰዎች ወደ መቀሌ አፈግፍገው የሚሆነውን ለማየት መሞከራቸው አይቀርም። በተለይም ወያኔ ሹልክ ብሎ ከአዲሳባ በመውጣት ኦሮሞና አማራ በቆንጨራ ሲጨራረስ ለማየት ሊመኝ ይችላል። ይህ እንዳይሆን በተለይ የፖለቲካው አክተሮች አስተዋይና ብልህ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የመጀመሪያው ጥበብ ሌላው ወገን ልክ እንደራሱ ለሀገሪቱና ለህዝቡ ፍቅር እንዳለው፤ ኃላፊነት እንደሚሰማው ማመን ነው። ጣሊያን ሲተርት፣ "በድሮ ትራክተር ያረሰ መለዋወጫ አያገኝም" ይል ነበር።

ተስፋዬ ገብረአብ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ