London Bridge Attack, on June 3, 2017.
የታጠቁ የእንግሊዝ ፖሊሶች አሸባሪዎችን ሲያድኑ። (የፎቶ ምንጭ: Daily Mail)

ኢዛ (እሁድ ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. June 4, 2017)፦ ቅዳሜ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ፣ በሎንዶን እምብርት በሚገኘው የሎንዶን ድልድይ አካባቢ ሦስት ጀሃዲስት አሸባሪዎች ሰባት ሰዎችን ገድለው አርባ ስምንት ሰዎችን ካቆሰሉ በኋላ፣ በእንግሊዝ ታጣቂ ፖሊሶች ተገደሉ።

የሎንዶን ጥቃት፣ ጁን ፫፣ ፳፻፲፯
በእንግሊዝ ፖሊሶች የተገደሉትና አሸባሪዎች ናቸው ከተባሉት ውስጥ የሁለቱ አስክሬን። (የፎቶ ምንጭ: Daily Mail)

እነዚህ ሦስት አሸባሪዎች ነጭ ቫን መኪና (ከኋላው መስታወት አልባ መለስተኛ አውቶቡስ፣ ዕቃ መጫኛ ሚኒባስ) ሎንደን ድልድይ አካባቢ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ መንገደኞች ላይ እየነዱ ጉዳት ካደረሱ በኃላ፣ ”ብራውት ገበያ” ሲደርሱ ከመኪናው በመውጣት አስራ ሁለት ኢንች በሚሆኑ ጩቤዎች በአካባቢው የነበሩ በርካታ ሰዎችን ወግተዋል።

የሎንዶን ጥቃት፣ ጁን ፫፣ ፳፻፲፯
የሽብርተኞች ጥቃት ሰለባ ከሆኑት ውስጥ በቃሬዛ ወደ አንቡላንስ እየተገፋ ሲወሰድ፣ እንዲሁም በጥቃቱ ሰዎች በከፍተኛ ድንጋጤ ተውጠው። (የፎቶ ምንጭ: Daily Mail)

በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረና የተጎዱ ሰዎችን በመርዳት ላይ የነበረ የእንግሊዝ ፖሊስ ባልደረባ በጩቤ ከተጎዱት መሃል ሲሆን፣ ጉዳቱ ለሕይወቱ እንደማያሰጋው ታውቋል።

የሎንዶን ጥቃት፣ ጁን ፫፣ ፳፻፲፯
ብራውት ገበያ ከሚገኘው ዊትሼፍ ፐብ ደጃፍ ላይ ከተገደሉት ጂሃዲስቶች ውስጥ አንዱ የአርሴናል የእግር ኳስ ማልያን የለበሰ እና የውሸት ቦምብ መታጠቁን የሚያሳይ ፎቶግራፍ። (የፎቶ ምንጭ: Instagram / fried_chicken)

ሦስቱ አሸባሪዎች በራሳቸው ላይ ቦንብ የሚመስል ታጥቀው የነበሩ ቢሆንም፣ ቦምቡ የውሸት (አርቲፊሺያል) እንደነበር የእንግሊዝ ፖሊስ ገልጧል።

በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት (፳፻፲፯) ውስጥ ይኽኛው በእንግሊዝ ላይ የተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ሦስተኛው እንደሆነ ይታወቃል። የመጀመሪያ ጥቃት ባለፈው ማርች ፳፪ በሎንዶን ዌስትሚንስትር የደረሰው ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ሜይ ፳፪ የተፈጸመው የማንቸስተሩ የቦምብ ጥቃት መሆናቸው አይዘነጋም። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ