Stockholm attack, April 7, 2017
የጭነት መኪናው ከተጋጨ በኋላ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ራሳቸውን ለማዳን ጥረት ሲያደረጉ (ፎቶ፣ Aftonbladet)

ኢዛ (ዓርብ መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. April 7, 2017) ዛሬ ረፋዱ ላይ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም አንድ የጭነት መኪና በመዲናዋ እምብርት ሕዝብ በብዛት በሚተላለፍበት አካባቢ በሰዎች ላይ በመንዳት እና በስተመጨረሻም ኦሊየንስ የሚባለው ሱቅ ከሚገኝበት ሕንጻ ጋር ተላትሞ ነድዷል። በአደጋው ሦስት ሰዎች ሲሞቱ፣ ስምንት ሰዎች ቆስለዋል። ፖሊስ በቦታው ላይ በሰዓቱ ታይቷል ብሎ ያለውን ሰው ፎቶግራፍ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

ዛሬ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት ከሃምሳ ሦስት ደቂቃ (14:53) ላይ ድሮትኒንግጋታን (የንግሥቲቱ መንገድ) የሚባለው መንገድ ላይ የደረሰው አደጋ ከሽብር ጥቃት ጋር ግንኙነት እንደሚኖረው የስዊድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፋን ሎቬን ለስዊድን መገናኛ ብዙኀን ገልጠዋ።

Stockholm attack, April 7, 2017
የሕክምና ባለሙያ በብርቱካናም ብርድ ልብሶች አስከሬኖችን ለመሸፈን ሲሯሯጥ (ፎቶ፣ TNS)

የጭነት መኪናው ተጠልፎ የተወሰደ ሲሆን፣ የመኪናው ባለቤት ስፔንድሩፕስ የተባለው የስዊድን የቢራ ፋብሪካ መሆኑ ታውቋል። መኪናው ቢራ ለምግብ ቤቶች በማከፋፈል ሥራ ላይ የነበረ ሲሆን፣ የድርጅቱ ሾፌር ቢራ ሊያራግፍ ሲል ጭምብል የለበሰ ሰው ዘሎ መኪና ውስጥ በመግባት መኪናውን ጠልፎ መሄዱን ሾፌሩ ገልጧል። ሾፌሩ መኪናውን ለማስጣል ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ከመሆኑም በላይ በሰውነቱ ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል።

ስቶክሆልምና ነዋሪዎችዋ ከአደጋው በኋላ

Stockholm attack, April 7, 2017
በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ሲሰጥ

አደጋው ከደረሰ በኋላ የስቶክሆልም ከተማ ባቡሮች በሙሉ የቆሙ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎች በመሬት ውስጥ የሚሄዱ ባቡሮች መንቀሳቀስ ባለመቻላቸውና መንገደኞች ከባቡሩ መውጣት ሳይችሉ ለሰዓታት መቆየታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ከስቶክሆልም ዘግቧል። በተለይም በከተማዋ እምብርት አካባቢ ያሉ የሕዝብ አውቶቡሶችና የመጓጓዣ አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች በማጣታቸው ምክንያት ወደቤታቸውም ሆነ ወድ ሥራ መሄድ ያልቻሉ ሲሆን፣ ውጭ የነበሩትም ባሉበት ቦታ ለበርካታ ሰዓታት ለመቆይተ ተገድደዋ።

አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ ሱቆች፣ የግል ድርጅቶች፣ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ተቆልፎባቸው መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። የስዊድን ፓርላማ ሕንጻ አደጋው ለደረሰበት ቦታ በጣም ቅርብ የሆነ በመሆኑ በወቅቱ ፓርላማ ውስጥ የነበሩ ሰዎች እንዳይወጡና ከውጭም የነበሩ እንዳይገቡ ተደርጓል።

የስቶክሆልም ከተማ መስተዳድር ወደቤታቸው መሄድ ላልቻሉ ወገኖች በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ጊዜያዊ መጠለያ ማዘጋጀቱን ገልጧል።

በከተማ ውስጥ የስልክ አገልግሎት ሲቆራረጥ የነበረ ሲሆን፣ የስዊድን ሚዲያዎች የከተማዋ ነዋሪዎች ሶሻል ሚዲያ በአማራጭ መገናኛነት እንዲጠቀሙ መክረዋል። የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር በበኩሉ በተለይም የሞባይል ስልክ ግንኙነት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ እንደነበር፣ አንዳንዴም የስልክ ጥሪ ማድረግ የማይቻል እንደነበር እና የስልክ ጥሪው ሲሠራ ደግሞ የድምጽ ጥራት እንደሚጎድለው ለማረጋገጥ ችሏል። ከተማዋ በስልክ ጥሪዎች በመጨናነቅዋ የስልክ ችግር መፈጠሩ ታውቋል።

የስዊድን ንጉሥ

በብራዚል በጉብኝት ላይ የሚገኘው የስዊድን ንጉሥ ካርል ጉስታፍ ፲፮ኛው ዛሬ በስቶክሆልም በደረሰው አደጋ ንጉሣዊ ቤተሰባቸው ማዘናቸውን እና ጉዳዩን እየተከታተሉ መሆኑ የገለጡ ሲሆን፣ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ብራዚል ውስጥ የሚያደርጉትን ጉብኝት በአደጋው ምክንያት ማቋረጣቸውን የንጉሣዊው ቃል አቀባይ ማርጋሬታ ቶርግሬን ገልጠዋል። ንጉሡና ንግሥቲቱ ቅዳሜ ወደ ስዊድን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፖሊስ

ፖሊስ ማምሻውን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቦታው ላይ በሰዓቱ ታይቷል ብሎ ያለውን ሰው ፎቶግራፍ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ግለሰቡን የሚያውቅ ካለ ለፖሊስ እንዲጠቁም፤ አልያ ራሱ ግለሰቡም ቢሆን ለፖሊስ እንዲያመለክት ፖሊስ ጥሪ አስተላልፏል።

Stockholm attack, April 7, 2017
ፖሊስ በአደጋው ቦታ ላይ በሰዓቱ ታይቷል ብሎ ያለው ሰው ፎቶግራፍ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ