20210302 adwa

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና አቶ ለማ መገርሳ

ምሕረት ዘገዬ

መረጃ አይናቅም። መረጃ ሁሉ በግርድፉ እንደ እውነት አይወሰድም። መረጃዎች እንደየምንጫቸው ሰውን/ተቋምን ለማሳሳት፣ ለማደናገር፣ ለማስፈራራት፣ ለማስጠንቀቅ፣ ለማሳወቅ፣ ወዘተ ... ይለቀቃሉ። ጥንቃቄ ማድረግ የሚያሻው መረጃ ተጠቃሚው ወገን ነው።

ጠ/ሚ ዐቢይ ሥራው የተቃና ይሆን ዘንድ፣ እኛም ዜጎች የሚታየንን ባሉን ማስንተፈሻዎች እንጠቁማለን፤ ሰሚ ካገኘን እሰዬው። ሰሚ ባናገኝ ቢያንስ ከኅሊና ወቀሳ እንድናለን። የሚነገሩ ሁሉ እውነት ሊሆኑ እንደማይችሉ ሁሉ፤ የሚነገሩ ሁሉ ሐሰት ሊሆኑም አይችሉም። የአንድ መሪም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው ወገን ዋና ኃላፊነት እውነቱን ከውሸቱ አበጥሮ የመለየት ትልቅ ተግባር ነው።

ክቡር ጠ/ሚንስትር ዐቢይ፤

እግዚአብሔር “አንቱ” አይባልም። አባትን በአንቱታ መጥራት እምብዝም ስላልተለመደ። አንቱታ ፍቅርንና ቀረቤታን ያርቃል። ስለዚህ ከወጣትነትህም በተጨማሪ የአገርን እውነተኛ መሪ መውደድና ማፍቀር የነበረ በመሆኑ በአንቱታ ላርቅህ አልፈቅድም። ምሳሌ ቢያስፈልግ አፄ ምኒልክ ይበልጡን በአንተታ ነበር የሚጠሩት - ስለዕድሜያቸውና የኔ ዘመን መሪ ስላልነበሩ ነው “አንቱ” ያልኩት። ውድ ጠ/ሚ ዐቢይ - ልብ ልትላቸው የሚገቡህን አሳሳቢ ጉዳዮች ባጭሩ ቀጥዬ አስቀምጣለሁ።

  • የኦሕዴድ አባላትንና ካድሬዎችን አስቸኳይ ጉባኤ ጥራና የዚህን ድርጅት አካሄድ ፈትሽ። እየሠራኸው ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ተግባር ኦሕዴድን በጠለፉ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በርግጠኝነት እየተበላሸብህ ነው። ጊዜ ልትሰጠው የማይገባህ ችግር በአገራችን እየተባባሰ መጥቷል። አንተ ከላይ ሆነህ “ፍቅር፣ ፍቅር” ስትል ከሥርህ ጠላቶችህና የዕቅድህ አጨናጋፊዎች ሕዝቡን በተለይም አማራውን በኦሮሞ፣ በጉሙዝ፣ በትግሬ ሚሊሻዎችና እነሱን በተጠለለ የመከላከያ ሠራዊት እያስጨረሱት ነው። በብዙ የኦሮሞ አካባቢዎች አማሮች እየተባረሩና እየተገደሉ ነው፤ በቤንሻንጉል አማሮች እየተገደሉ ነው፤ በወልቃይት የፋሲልን ቡድን ማሊያ በመልበሳቸውና አማርኛ በመናገራቸው ብቻ ሊያውም የአገዛዙ ኮለኔሎችና የ“ፌዴራሉ” መንግሥት ዋና ባለሥልጣኖች ልብስ እያስወለቁ ማቃጠልና ራቁትን ማሰር ቀጥለዋል። ያንተ የፍቅር ስብከትና የጋራ አገር ግንባታ ጥረት ሊገባቸው ቀርቶ ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ የማጥፋት ነባር ሤራቸውን አጧጡፈው ቀጥለውታል። እነዚህ ሰዎች የተለከፉበት የዘር ጥላቻ ሳያስቀብር የሚለቃቸው አይመስልም።
  • በተቃውሞ ጎራው ድረገፆችና ቴሌቪዥኖች፤ በየዕለቱ ምን እንደሚባል መረጃ ሰብስብ። ሁሉንም አንተ ማድረግ ስለማትችል የተማሩና ቀና ቀና ሰዎችን በመመደብ ጭምቅ መረጃዎችን በየቀኑ እንዲሰጡህ አድርግ። ኢሳትንም፣ ኦኤምኤንንም፣ ድረገፆችንም፣ … የሰይጣንም ሚዲያ ቢሆን ይጠቅምሃልና ተከታተል። ከዚያም የማይውል የማያድር እርምጃ ውሰድ። አመኔታና ግርማ ሞገስህ ይጨምራል።
  • ሕዝብ በቀጥታ ሊያገኝህ የሚችልበት የቀጥታ ስልክ ቁጥር ይኑርህ። ለዚያ ግንኙነት ብትችል አንተ ራስህ ባትችል የቅርብህ የሆነ ሰው እንዲያነሳና የሚቀርቡ ጥቆማዎችን፣ አስተያየቶችን፣ በደሎችን፣ … በማጣራት በወቅቱ ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አድርግ። የምትመድበው ሰው የሕዝብን ብሶትና ጥቆማ ወይም አስተያየት ይሰማና ከቻለ በራሱ፣ ከአቅሙ በላይ ከሆነ ደግሞ ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሆኖ ለችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥ ይደረግ - ለምሳሌ ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ ቤታቸው የፈረሰባቸው ብዙ ዜጎች አቤት የሚሉበት አጥተው እንደተቸገሩ በኢሳት ሰምተናል - አንተ እያለህ ችግራቸው ከቤት መውጣት አልነበረበትም። … በዚህ መልክ በተለይ የሙስና ወንጀሎችን፣ የፍትሕ መዛባትን፣ ኮንትሮባንድን፣ አስተዳደራዊ በደልን፣ የፆታ ትንኮሳን፣ ምዝበራንና የመሳሰሉትን ማኅበረሰብአዊ ነቀርሣዎች መታገልና ጉዳታቸውን መቀነስ ይቻላል። ሙሰኞችና የአስተዳደር ዋልጌዎች በሕዝብ ላይ የሚዘባነኑት የላይኛውና የታችኛው የሚገናኙበት ድልድይ እንደሌለ በማመን ስለሆነ፤ ይህን ዘዴ አሁኑኑ ተግባራዊ ብታደርግ ሰዎች ናቸውና ይፈራሉ፤ ይጠነቀቃሉም። ይህን የአሠራር ሥርዓት አሁኑኑ እውን አድርግ። ውጤቱን ታየዋለህ።
  • በኑሮ ውድነት ሕዝቡን ከበፊቱ ይበልጥ ለማሰቃየት ቆርጠው የተነሱ የዕቅድህ አሰናካዮች አሉ። እነዚህ ወገኖች የአንተን መንግሥት በሕዝብ ለማስጠላት እንዲህ እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ለዚህም አንዳች መፍትሔ ፈልግ። ነቀዞቹ አይጎዱም። የሚጎዳው ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ እንኳን መሆን ያልቻለው ከ90 ሚሊዮን የማይተናነሰው የ100 ሚሊዮኑ አጠቃላይ ሕዝብ አካል ነው። ያንተን ዓላማ የማይወዱ ወገኖች ዓላማህ እንዳይሳካ ዙሪያህን በእሾህ እያጠሩት ነው። የሌት እንቅልፍ የቀን እርፊት የላቸውም። ሃያ አራት ሰዓት ጠምደው ይዘውሃል። የፍየል ሥጋ ሆነህባቸው የሚያደርጉትን አጥተው ተቸግረዋል። እንዳያጠፉህም ዛሬ ዛሬ እነሱም ነፍስ አውቀው የሚከተለውን ነገር ስለተረዱ ይመስላል ፈርተውሃል። በኔ ግንዛቤና እምነት አንተ ዳዊት ነህ። የጎልያድን ክርኖች በተዓምረ እግዚአብሔር በሥውር እያደቀቅህ ትገኛለህ። የእግዚአብሔር ጥበብ ድንቅ ነው። ይመስገን። ግን ሰዎቹም ዓለም አቀፋዊና ጥቁር-መንፈሣዊ ተፅዕኗቸው ቀላል ስላልሆነ፤ የሚናቁ አይደሉም። ከእግር እግር እየተከታተሉ ሥራህን ለማፍረስ እንደሚሞክሩ ተገንዝበህ በርቀት እንዲከተሉ አድርግ። ያኔ ደክሟቸው ይቀራሉ። ያኔም ኢትዮጵያ ከነዚህ ጉግማንጉጎች በቀላል መስዋዕትነት ነፃ ትወጣለች።
  • ቢሮህን፣ መኖሪያ ቤትህን፣ ግቢህን፣ መኪናህን፣ አጃቢዎችህን፣ ቤተሰቦችህን፣ ጓደኞችህን፣ የምትበላውን፣ የምትጠጣውን፣ … ሁሉንም ነገርህን ከኤሌክትሮኒክስ ወጥመዶች ነፃ አድርግ፤ የተማሩና የሠለጠኑ ታማኝ ሰዎችን አስጠጋ። እነዚህ ክፉ ወያኔዎች በ bugging እና በሥውር ክትትል (surveillance) እንዲሁም በሤራ ፖለቲካ (conspiracy) እጅግ የተካኑ ናቸው - ፈጣሪ ጨርሶ አይበድልምና በሌላው ዕውቀት ባይታደሉ በሸርና በተንኮል አንደኛ ናቸው - በአፍሪካ ቢያንስ። ያለአንዳች እንቅልፍ ሌት ተቀን የሚማስኑት በነዚህ ነገሮች ተጠምደው ነው። በዓለም የሚታወቁ ወያኔን መሰል ጠባብ ዘረኞች የሚታወቁባቸው ባሕርያትም እነዚህ ናቸው። ጥቂት ሆነው ሳለ ብዙኃንን ማንበርከክና የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ መቆጣጠር የቻሉት ለሌሎች ዝግ በሆነ ምሥጢራዊነታቸው በሚዶልቱት የጥፋትና የተንኮል ዕቅዳቸው አማካይነት ነው። ሕወሓትም የነዚህ ምሥጢራውያን ተቋማት አካል እንደመሆኑ በጥንቃቄ ካልተያዘ ሊያደርሰው የሚችለው ጥፋት ወደር የለውም። መሸነፉን ሲያውቅ በተለይ ለማንም የማይራራ ጨካኝ ነው። ስለሆነም የለውም እንጂ ቢኖረው ኒኩሌር ለቆ መላ ኢትዮጵያን ከማጥፋት አይመለስም። መጠንቀቅ ያለባቸው እንግዲህ የሰውነት ደረጃቸውን ያልተቀሙና ገና በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የነሱ የጥንካሬ ምንጭም - እንደሚመስለኝ - ኢትዮጵያውያን እንደሰው የማሰባቸውና እነሱ እንደጭራቅ የማሰባቸው ክፍተት የፈጠረው የርህራሄና የጭካኔ ልዩነት መበላለጥ ነው። ብዛት ዋጋ የለውም። ብልጠትና ጭካኔ ግን መጨረሻቸው አያምርም እንጂ ዋጋ አላቸው። ለከት የለሽ ጭካኔና ያልተገራ ብልጠት በሀብትና በሥልጣን ለተወሰነ ጊዜ ያቆያሉ።
  • በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃና የሥራ ልምድ ሥራ የያዙ ባለሥልጣናትንና ሠራተኞችን የሚያጣራ ኹነኛ ሰው/ቡድን አሁኑኑ መድብ። አገር እየጠፋች ያለችው ባልተማሩ ግን በሐሰት ዲግሪዎች በተንበሸበሹ ሆዳም ዜጎች ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ካለሆዳቸው አያስቡም። በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ይህን ነገር ማጣራት አይከብድምና ይህ ሥራ ባፋጣኝ ይሠራ። ደግሞም ተገቢው ሥራ ለተገቢው ባለሙያ ይሰጥ። ስለእንጨት ስንጠቃ ተምሮ ዶሮ ዕርባታ ላይ ቢመደብ ምንም አይሠራም። ኪሣራው ብዙ ነው። የተማረበት ገንዘብ፣ ያጠፋው ጊዜ፣ ሥራው ላይ የሚያደርሰው ጥፋትና የመሳሰለው ሲታሰብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ይሄ ችግር ዘላቂ መፍትሔ የሚያሻው ትልቅ ችግራችን ነው። በደርግ ዘመን ጓድ ዶክተር አለሙ አበበ በእንስሳት ሕክምና በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቆ ሲያበቃ፤ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከንቲባ ነበር - የሚያስቅ ምደባ። አሁንም ይህ ጉራማይሌ ሞልቷል። አገር ታዲያ እንዴት ትደግ? የአሁኑ የወያኔ ምደባማ ከማሳቅና ከማስገረም ያለፈ ነው። ለክርፋታሙ ዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት ታማኝ ይሁን እንጂ ያልተማረ ዘበኛም ተነስቶ የጠቅላይ ፍርድ ቤት መሃል ዳኛ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ስሟ እስካሁን መኖሩ በራሱ የሚደንቅ ነው።
  • የኤምባሲ ሠራተኞች ዘውጋዊ ተመጣጥኖ አሁኑኑ ይስተካከል። የተሞላው በአንድ ብሔር ሰዎች ነው ይባላል። ለዚያውም ሙያው የላቸውም አሉ። በትውውቅና በዘር መሥፈርት የተሠራ ሁሉ ዛሬውኑ ይፍረስ - እርግጥ ነው እየተጠናና በምክንያት። ለዛሬ እዚህ ላቁም፤ ግን መመለሴ አይቀርም። እኔ አልሰለችም - አንተም አትሰልች። ከዚህች ምሥኪን አገር ሌላ ምን አለኝ/ን?

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!