Shashemene

ሻሸመኔ

ወለላዬ ከስዊድን

“አዎን! ኢትዮጵያዊ ነኝ!” በለኝ

መቼም አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም

ካልኾንክም ግድ የለም

እቅጩን ሐቁን ንገረኝ

ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ።

የኔነቴን የአገሬን ትዝታ

የቀዬው የአድባሩን ሽታ

የፍቅሬን የአንድነት ጥላ

ለዘመናት ያኖረኝን ከለላ

ወዲያ ጥለኸው ሰባብረህ

ከናት ካባትህ ቃል ኪዳን ርቀህ

እንዲህ ኾነህ ያገኘሁህ

ማነህ?

እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?!

 

በመልክማ፣ ትመስለኛለህ አንድ ነን

በቀለምስ፣ በቁመትስ ምን ለየን

ግን አንተ፣ ምድረ አገርህን ክደሓት

በአደባባይ አዋርደሃት

እውን ኢትዮጵያዊ ነህ?

ኢትዮጵያስ ያንተ ናት?

ማነህ?

እውነት አንተ ምንድነህ?

አገር እናቴን ፍቅሬን

የደስታ የኀዘን ገበናዬን

የኔነቴን ቅርስ መጠሪያዬን

የነፃነት ብርሃን ኩታዬን

የጣልክብኝ ያገር ክብሬን

ማን ነው ልበልህ? ማነህ ንገረኝ ማነህ?!

እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?

መቼም፣ አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም

ካልኾንክም ግድ የለም

እቅጩን ሐቁን ንገረኝ

ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ

እናት ከልጅ አስገድደህ ደፍረህ

ወገንህን ዘቅዝቀህ ገድለህ

ሃይማኖት እምነትህን የሻርክ

በተንኮል ፖለቲካ የዳከርክ

ማነህ?

እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?

 

ያንን መተዛዘን ደግነት

የፍቅረ ሰላም አንድነት

የአብሮ መኖርን እሴት

ለዘመናት የኖረን ትውፊት

የት አደረስከው?

እንዴት አድርገህ ደፈጠጥከው

ምን ያህል አውጥቶልህ ሸጥከው

በል ንገረኝ እውነት እውነቱን እናውራ

አንተም በኢትዮጵያዊነት ትጠራ?!

መቼም አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም

ካልኾንክም ግድ የለም

እቅጩን ሐቁን ንገረኝ

ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ

 

ለመልኩማ፣ መልክህ መልኬን ወርሷል

እትብትህ በኔው ቀዬ ተቀብሯል

ዜግነትህ በዜግነቴ ተጠርቷል

ወዝህ ከወዜ ተነካክቷል

ዘርህ ከዘሬ ተጋምዷል

ግብርህ ግን ይኼን ሁሉ ሽሮ

አመለካከትህ ተጠናብሮ

እያየሁህ እያየኸኝ

ማነኝ ነው የምትለኝ?!

መቼም አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም

ግድ የለም

እቅጩን ሐቁን ንገረኝ

ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ

ማነህ?

እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?!

ሐምሌ ፳፻፲፪ ዓ.ም. ስዊድን

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ