20210302 adwa

Dr. Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ምሕረት ዘገዬ

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፣

ሰላምታየን ላስቀድም። ሰላም!

የጀመርከው የለውጥ እንቅስቃሴ ከሕወሓትና ሕወሓታውያን በስተቀር ጤነኛ ነኝ የሚልን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ በማስደሰት ላይ የሚገኝ ማንም ከማንም ያልጠበቀው ታላቅ አገራዊ በረከት ነው፤ ለአንዳንዶቻችን እንደገና የመፈጠር ያህልም ነው - በሕይወት እያለን እናያዋለን ብለን ያላሰብነው በመሆናችን። ይህ መለኮታዊ የሚመስል ፀጋና ቸርነት ምን ዓይነት ውጤት እያመጣ እንደሆነ አንተም ሆንክ እኛ እናውቃለን። አንድዬ ይህን አንተ የጀመርከውን ለውጥ እውነት አድርጎት እስከመጨረሻው እንዲያዘልቅንና ወደ ቀደመው ኢትዮጵያዊ የአንድትነትና የመተሳሰብ ዐውድ እንዲመልሰን ሁላችንም በአንድ ልብ ሆነን እንጸልይ። እግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና አሁን እዚህ ካደረሰን “ነገም ሌላ ቀን ነው”ና ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰናል።

አሁን ብዕሬን ያነሳሁት አንድ ዐቢይ ቁም ነገር ላስታውስህ ነው። በነካ እጅህ ይህን የሰይጣን ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያ ስም ሲውለበለብ ከማየት አድነን - በምታምነው ይሁንብህ። ባንዲራችንንም ከታሰረበት ፍታና በደስታ አስቦርቀን። ይህን ባንዲራ ከሰይጣናዊ ትዕምርት (ምልክት) ነፃ ማድረግ ማለት በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ ከእሥራት እንደመፍታት ያህል ነው። ንጹሑ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያችን ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ አሳየን። እነዚህ እርጉማን ወያኔዎች በሠርግና በበዓላት ቀናት እኛ የምንወደውንና ደባደቦ የሌለበትን ንጹሕ ባንዲራ ስንይዝ ያስሩናል፤ ይገርፉናል።

በቀድሞ ሥርዓት ናፋቂነትም ከስሰው በታዛዥ ፍርድ ቤቶቻቸው በኩል ያሰቃዩናል። ይህችን የምንወዳትንና ሚሊዮኖች የተሰውላትን ባንዲራ እንዳንይዝ እንኳን ለዚችም ሕግ አውጥተው ያንገላቱናል። በሠለጠነው ዓለም አንድ ዜጋ የውስጥ ግለገል ሱሪውንና ከናቴራውን ሳይቀር ባንዲራየ ነው ብሎ ቢያውለበልብ ምናልባት “ዕብድ ነው!” ብለው ይስቁበት እንደሆነ እንጂ በሕግ ስም ውጣ ውረድ አይደርስበትም። አንድ ዜጋ ሌላው ቀርቶ የአገሩን ባንዲራ እስከማቃጠል ቢደርስ እንዳይጠየቅ የሚያደርገው ህገ መንግሥታዊ የሕግ ከለላ ይደረግለታል - ባንዴራ ማቃጠልን መደገፌ ግን አይደለም። ወያኔዎች ግን የጠላነውን ጨርቅ ትተን የወደድነውን ባንዲራ እንኳን ማውለብለብ እንዳንችል የሚገድብ ዐዋጅና ሕግ የሚደነግጉ እስከዚህን የወረዱ ዝቃጮች ናቸው። ምን ዓይነት ጉዶች ናቸው! እግዚአብሔር በዚህ መልክ እንደኛ አምርሮ የቀጣው ሕዝብ በታሪክ ይኖር ይሆን?

ይህ የኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ስሜትና ፍላጎት ነው። ባንዲራው የተጫነብን አለፍላጎታችን ከመሆኑም በላይ ምናልባትም ጃዝ ብለው የላኩትን ሰይናጣናውያን ለማስደሰት ሲል አቶ መለስ ዜናዊ የዛሬ 27 ዓመታት ገደማ በጫካ ውስጥ ፈጥሮ የጫነብን ሸክም ነው። በአገራችን 30 ባንዲራ የፈለሰፈውና ሳይገባንና ሳናውቀው እንድናውለበልብ የተደረገውም በዚሁ እርጉም ሰው ተንኮል ነው። ለኔም በጎሣየ ስም ቤተ ሙከራ ውስጥ መለስ ዜናዊ ጠፍጥፎ የተሠራልኝ ባንዲራ አለ። ግን አንድም ቀን ይዤውም ሆነ የኔ ነው ብዬው አላውቅም። ባንዲራ በአንድ ግለሰብ ተፈብርኮ ለሕዝብ የሚሠራጭ ሸቀጥ አይደለም - በዚህ ሁኔታ ተፈብርኮ የሚታደልን ባንዴራ ከቁም ነገር ቆጥሮ መቀበልና በወረት ፍቅር መነዳትም ጤናማነትን አያሳይም። ከዚህ አንጻር ውድ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ወያኔ ሕዝብን ለመከፋፈል የፈበረካቸውን ባንዲራዎች በተመለከተ አንድ ነገር አድርግ። በሩቅም ሆነ በቅርብ ከሚገኙ የለውጥ ኃይሎች ጋርም ተመካከር። እውነቴን ነው - አንተን የመሰለ ደግና ይስሃቅ-አቤላዊ የመስዋዕት በግ በጀርባህ ወይም በፊት ለፊትህ አሊያም በጎንህ ይህን የዲያቢሎስ ዓርማ ያለበትን የዕኩያን ሥሪት ባንዲራ አስቀምጦ መታየት አሣፋሪ ነው። ችግርህ ቢገባኝም አንተን በዚህ የወያኔ ባንዲራ አጠገብ ማየት ካለውዴታህ በግድና በሽጉጥ እያስፈራሩ ቆሻሻ ገንዳ አጠገብ ያስቀመጡህ ያህል ይሰማኛልና በቶሎ እርምጃ ውሰድ። የብዙ ሰዎችን ስሜት ስከታተል ተመሳሳይ ነን።

በእግረ መንገድ ደግሞ - ወያኔዎች የሚፈነጩባቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሰው ኃይል አደረጃጀት አስተካክል። አየር መንገድ፣ ባንኮች፣ መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ መምሪያ፣ ፍትሕ ሚንስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣የመሬት ይዞታ አስተዳደር፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ … ባጭሩ ሁሉም የሚንስቴርና የኮሚሽን፣ የማዕድንና ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው የአስተዳደር መ/ቤቶች ድረስ ዋና ዋናውን የሥልጣንና የጥቅም ቦታዎች እነሱ ስለያዟቸው ሌሎቻችን መፈናፈኛ አጥተናል፤ ፍትሕ ይዛባብናል፤ መድሎ ይፈጸምብናል፤ ለአንዲት አገር ዜጎች የተለያዩ አፓርታዳዊ ህጎች ተግባራዊ ይደረጉብናል፤ ኑሯችን ሽቅብ እንዲወነጨፍ ያለ የሌለ ሻጥር በየፈርጁ ይፈጸምብናል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሁሉንም ነገር እነሱ ስለተቆጣጠሩት ነው። “ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ ፖለቲካውንም ይቆጣጠራል” በሚል ፈሊጥ የሚመሩት ወያኔዎች መቆጣጠር ያልቻሉት የሚነፍሰውን አየር ብቻ ነው። በተረፈ ነፍሳችንን ሳይቀር ተቆጣጥረውታል።

ጨረስኩ። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን። ፈጣሪ አንተንም ኢትዮጵያንም ይባርክ። ውጥንህን ጨርሰህ እፎይ እንድትልና እኛና የምትማስንላት አገርህም በትግልህ ፍሬ ተደሳቾች እንድንሆን ያብቃን። ገደሉን ወጥተን ወደሜዳው ልንዘልቅ ጥቂት ጊዜ የቀረን ያህል ይሰማኛልና ፈጣሪ ቀሪውን ጨለማ በአፋጣኝ ይግፈፍልን። የእባቡን መርዝ ደግሞ ጨርሶ ያስተፋልን። ….

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!