Ethiopian Orthodox Synodos

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሠጠ መግለጫ (የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም.)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያኒቱና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ ከየካቲት 9 -11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተነጋግሮ በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ የሆኑ ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ በመነጋገር እና ውሳኔ በማሳለፍ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።

1. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በቀድሞው ቀበሌ 24/18/16 እና 15 ነዋሪዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት አቤቱታ እንደተገለጸው በ24/5/2012 ዓ.ም. ለ25 አጥቢያ በውድቅት ሌሊት በቦሌ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሆኑ ምእመናን በምሕላና በጸሎት ላይ እያሉ በተኩስና አስለቃሽ የመርዝ ጋዝ ጭስ በመጠቀም በጥይትና በዱላ በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ሁለት የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ወጣቶች መገደላቸውን ቤተ ክርስቲያኑ ፈርሶ ክቡር የሆነውና በአባቶች ተባርኮ የነበረው የቃል ኪዳን ጽላት መወሰዱ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸውን የሰማው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በድርጊቱ እጅግ ከማዘኑም በላይ ይህን ክፉና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት አውግዟል።

በቤተ ክርስቲያናችንም ላይ እንዲህ ዐይነት ክፉ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ ምርመራ በማድረግ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና ውጤቱ ለምእመናኖቻችን በሚዲያ እንዲገለጽ እንጠይቃለን።

2. የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታ በተመለከተ ቤተ ክርስቲያናችን ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ቦታው ለአካባቢው ምእመናን ማምለኪያ እንዲሆን ከመንግሥት በመነጋገርና በመጻጻፍ የቆየችበት ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳት የከበሩበት ከመሆኑም ባሻገር ሁለቱ የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ወጣቶች በግፍ ጨለማን ተገን ባደረጉ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ደማቸው የፈሰሰበትና ሕይወታቸው ያለፈበት ቅዱስ ቦታ እንደመሆኑ መጠን ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ምእመናን በሰላም መንገድ አምልኮአቸውን እንዲፈጽሙ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የበኩሉን መመሪያ እንዲሰጥልን ቅዱስ ሲኖዶስ ይጠይቃል።

ይህ ደም የማፍሰስና ሕይወትን የማጥፋት ተልዕኮ አልበቃ ብሎ በየምክንያቱ የታሠሩ ካህናትና ምእመናን ወጣቶችም ጭምር በእስር ላይ መሆናቸው ስለሚታወቅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስራት እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይጠይቃል።

3. ሀ. ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ደንብ ውጭ በመነሳሳት የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እናቋቁማለን በማለት በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ ጽላት ተሠጥቶናል በሚል በምድረ አሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን አቋቁመናል የሚሉት፡-

1. ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን

2. አባ ገ/ማርያም ነጋሳ

3. መምህር ኃ/ሚካኤል ታደሰ

4. ቄስ በዳሳ ቶላ

እነዚህ ግለሰቦች ቤተ ክርስቲያናችን በማታውቀው መንገድ በአመጽ በመነሳሳት ምእመናንን ግራ እያጋቡና እያሳሳቱ መሆኑን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ የክህደት ትምህርት ማስተማራቸው በመረጃ ተደግፎ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ የቀረበ በመሆኑ እነዚሁ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰ የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጆች ነን የሚሉ ከድርጊታቸው ተቆጥበው በንስሐ እስኪመለሱ ድረስ ከየካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያናችን የተሠጣቸው ክህነት ተይዟል። በቤተ ክርስቲናያናችንም ስም ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉና መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሠጡ ታግደዋል። ግለሰቦቹ ከጥፋት ድርጊታቸው ተጸጽተው ለመመለስ ከፈቀዱ ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

ለ. እነዚሁ ካህናት ነን የሚሉ ግለሰቦች በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ የተሰጠን ጽላት አለ በሚል ምእመናንን እያደናገሩ ቢሆንም እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ደንብ መሠረት ጽላት እንዲሰጣቸው ያልጠየቁ ከቤተ ክርስቲያናችንም የሰጣቸውም አካል አለመኖሩ በጉባኤው የተረጋገጠ በመሆኑ ምእምናን ከእንደዚህ ዐይነት ተሳስተው ከሚያሳስቱ ግለሰቦች ራሳቸውን ሃይማኖታቸውንና የቤተ ክርስቲያን ሥርዓታቸውን ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠብቁ ጉባኤው አሳስቧል።

4. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ቅዱሳንና መናንያን ለአገርና ለወገን የሚጸልዩባቸው ታላላቅ ገዳማት እንዳሏት ይታወቃል። ሆኖም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ገዳማት ላይ ግለሰቦች እያደረሱ ያለው ፈተናና ችግር ያለ መሆኑ ሲታወቅ በተለይም በአሁኑ ጊዜ፡-

ሀ. በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊበን ዝቋላ ወረዳ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣

ለ. በሰላሌ ሀገረ ስብከት በታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሆን ተብሎ በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካኝነት እየደረሰ ያለው ችግር እና ታሪክን የማጠልሸት ሂደታቸው በአስቸኳይ እንዲቆም የሚመለከተውም የመንግሥት አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግር ፈጣሪዎችን እንዲያስቆም ለገዳማቱም የአገር ቅርስ እንደመሆናቸው ሁሉ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ መንግሥት እንዲያስፈጽምልን እንጠይቃለን።

5. በዐረብ ኤምሬቶችና በዱባይ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ወገኖቻችን ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የአገሪቱ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያናችን የቦታ ጥያቄ እየቀረበለት ምላሽ ሳናገኝ እስከአሁን ቆይተን ነበር።

በአሁኑ ጊዜ ግን የአገራችን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ዐቢይ አህመድ በአረብ ኤምሬቶች ባደረጉት የሥራ ጉብኝት በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጐቻቸውን ከማነጋገርና ከማጽናናት ባሻገር ከአገሪቱ መንግሥት በመነጋገር ለክርስቲያን ወገኖቻችን የማምለኪያ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ በማስፈቀዳቸው ከዚህም ጋር በዐረቡ ዓለም በስደት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከስደት እንዲመለሱና ለአገራቸው እንዲበቁ በማድረጋቸው ስደተኛ የሆኑ ክርስቲያን ወገኖቻችን በእጅጉ ያስደሰተና ቤተ ክርስቲያናችንም ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን እንድታስፋፋ የሚያግዝ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በእጅጉ ከመደሰቱም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደዚህ አገራዊ መንበረ ሥልጣን ከተጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው እየፈጸሙት ያለ አኩሪ መንፈሳዊ ተግባር ሁኖ ስላገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የከበረ ምስጋናውን አቅርቧል።

6. ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን፡-

በOMN

በLTV

በOBS

ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በጥንታዊትና ሐዋርያዊት በሆነችዋ ለአገርና ለወገን ባለውለታና ባለታሪክ በሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን የከፈቱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄዳቸው ታሪክን እያበላሹ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ ማስተላለፋቸው ከዚህም የተነሳ ከ60 ሚሊዮን ያላነሰ ተከታይ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ክብሯንና ልዕልናዋን ዝቅ ባደረገ መልኩ የሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ቀውስ ለማምጣት እየተደረገ ያለ ጥረት በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ የጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ከብዙኃን መገናኛ ሕግ እና ደንብ አኳያ በሕግ እንዲጠየቁ ለወደፊቱም ከእንዲህ ዐይነት ሕገወጥ ድርጊት እንዲታቀቡ መንግሥትም በዚሁ ላይ አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያሳልፍልን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከየካቲት 9-11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለ3 ተከታታይ ቀናት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከዚህ በላይ በተገለፁት ነጥቦች ላይ ከመከረና ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በኢትዮጵያ አገራችን በመንግሥትና በሕዝቡ ጭምር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ማለትም ሕዝባዊ አንድነት እንዲጐለብት፣ ማህበራዊና ልማታዊ ተግባራት እንዲፋጠኑ፣ በአጠቃላይ በአገራችን ሰላምና አንድነት ሰፍኖ አገራችን ኢትዮጵያ መላው ዜጋ ከሚመኝላት የእድገት ጫፍ እንድትደርስ እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ ለአገሩና ለሕዝባዊ አንድነቱ ፀንቶ እንዲቆም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪውን በማስተላለፍ ጉባኤውን በዛሬው እለት በጸሎት ዘግቷል።

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ!
ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ!
ለሕዝባችንም አንድነቱንና ሰላሙን ይስጥልን!
አሜን፤
አባ ማትያስ
ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ