Artist Manalmosh Dibo ድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦ ሼኽ አል-አሙዲ ለሕክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ ልከዋት ነበር

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም. November 21, 2009)፦ “ዓሣ በለው” በሚለው ዘፈኗ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂ የሆነችው ድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦ ዛሬ ማምሻውን (ቅዳሜ ኅዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም.) ለሕክምና ደቡብ አፍሪካ እንደደረሰች ማረፏን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለፁ።

 

ድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦ ከአንድ ዓመት በላይ በአንጀት ካንሰር ሕመም በከፍተኛ ሁኔታ ታማ በሀገር ውስጥ ሕክምናዋን ስትከታተል የቆየች ሲሆን፤ ከአንድ ወር በፊት በጥቁር አንበሳ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ ካልታከመች ሕይወቷ አስጊ ደረጃ ላይ እንደሆነ ገልፀውላት ነበር።

 

ለውጭ ሀገር ሕክምናው የሚውል በቂ ገንዘብ ስላልነበራትና ወጪዋን ሸፍኖ ውጭ ሀገር የሚያሳክማት ሳይገኝላት ቀርቶ ነበር። ባለፈው ጥቅምት 20 ወደተኛችበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የጠየቃትና የ20 ሺህ ብር እርዳታ የሰጣት ሲሆን፣ እሱን ተከትሎ የተለያዩ አርቲስቶች፣ ባለሀብቶችና ድርጅቶች እርዳታ አድርገውላት ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉና አዲካ ቱር ይገኙበታል። ከተለያዩ ወገኖች ለሕክምናዋ እርዳታ ያገኘችው አንድ መቶ ሺህ ብር አካባቢ የነበረ ቢሆንም፤ ለውጭ ሀገር ሕክምናዋ በቂ ሳይሆን ቀርቷል።

 

በመጨረሻም ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ ወጪዋን ሸፍነው ሊያሳክሟት ቃል በመግባት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማምራት የበቃች ቢሆንም፤ ደቡብ አፍሪካ እንደደረሰች ግን ሕይወቷ ማለፉን ለመረዳት ችለናል።

 

ድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦ በዘመናዊ የሀገር ባህል ሙዚቃዋ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ ነበረች። የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል ለመላው ቤተዘመዶችዋ፣ ለጓደኞችዋና ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ በሙሉ መጽናናትን ይመኛል።

 

ከዚህ በታች “ዓሣ በለው” የሚለውን የድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦን የቪዲዮ ክሊፕ ያገኛሉ። ለማየት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ